በድሬዳዋ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአስተዳደሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናገሩ

ድሬዳዋ  ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት ተናገሩ።

በድሬዳዋ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ከአስተዳደሩ ከንቲባና የአመራር አባላት ጋር ለውጡን ተከትሎ እየተካሄዱ በሚገኙ ተግባራት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደገለጹት፤ ድሬዳዋን የተሻለችና የበለፀገች ለማድረግ ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት ይኖርበታል።

ድሬዳዋን የመለወጥና ወደ ከፍታ የማሻገር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎና ርብርብ እንደሚጠይቅም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የዘጠኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር አባላቱ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት በድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ አስተባባሪ እና የድሬዳዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዮናስ በትሩ እንደገለፁት፤ በድሬዳዋ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በድሬዳዋ የልማት እና የለውጥ ስራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።


 

"በድሬደዋ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል፤ እኛም በአስተዳደሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንድንሳተፍ መደላድል ተፈጥሮልናል" ብለዋል።

በድሬዳዋ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ዘለቀ በበኩላቸው በከንቲባ ከድር ጁሃር የሚመራው የለውጡ አመራር የድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ በዘለለ የወጣቶችን ጥያቄዎች ለማቃለል የጀመራቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተጀመሩትን ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

አስተዳደሩ ለገበያ መረጋጋት እና ለስራ አጥነት ጥያቄዎች የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የበለጠ መስራት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፀሐፊ አቶ ገብረስላሴ ሳዕልሶ ናቸው።

አክለውም በአስተዳደሩ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ የተጀመሩትን የልማት እና የአሳታፊነት ሂደቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በድሬዳዋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ኃላፊ አቶ የሺጥላ ሞላ በበኩላቸው አስተዳደሩ የጀመራቸው ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከመሬት አስተዳደር ጋር ለተያያዙ ችግሮች እና የመኖሪያ ቤቶች ዕጥረት መፍትሄ መስጠት እንዳለበት አንስተዋል።

 

የመኢአድ የድሬዳዋ የሴቶች አስተባባሪ ወይዘሮ ሀና ቢሆነኝ እንዳሉት በድሬዳዋና በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያካሄዱት ውይይት የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።

ድሬዳዋን በአገር አቀፍ ደረጃ በሰላም እና በልማት ተጠቃሽ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የድርሻችንን እንወጣለን በማለትም አክለዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም