የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ።
ሁለተኛው የቀይ ባሕር ቀጣና ጂኦ-ፖለቲካል ለውጥና የባሕር ደኅንነት እንዲሁም ኢትዮጵያን አማራጭ ወደብ ማግኘት የሚያስችሏትን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚዳስስ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ በኢትዮጵያ የሀገራት አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ምሁራንና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።
በዚሁ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን፤ የቀይ ባሕርን ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካል ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲካል የምክክር መድረክም ኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው ቀጣናዊ ትብብር የሚኖራትን ሚና በማጉላት የጋራ አረዳድ ለመያዝ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው የጋራ ጥረት ጉልህ ድርሻ እንዳላት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን ማስተናገድ የሚችል የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የሚደረገው ጥረት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የሰላምና ደኅንነት ዘርፍም በታሪክ የሚታወስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደኅንነት በማስጠበቅ ቀጣናዊ ትርምስን ለማርገብ የማይተካ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካል እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ይመለከታል ያሉት አቶ ጃፋር፤ የቀጣናው ሀገራት የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ያገለለ የሰላምና ደኅንነት አካሄድም ውጤታማ እንደማይሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቁርኝትና ህልውና ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚደረገው ኢትዮጵያን የሚያገል ሂደትም አንድም በውስጥ አርቆ አለማሰብ አሊያም ከታሪካዊ ጠላቶች የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ ያለውን ወሳኝነት ታሳቢ በማድረግ ቀጣናዊ ፈጣንና ተለዋዋጭ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
2ኛው የቀይ ባሕር ጉዳይ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ስትራቴጂክ ሚና በማስገንዘብ ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
በመድረኩም ከላይኛው የቀይ ባሕር ቀጣና እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ድረስ የተውጣጡ ምሁራንና የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት መካሄዱ ደግሞ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን ለማስከበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በዚህ መነሻነትም ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን የህልውናዋ አካል በመሆኑ በሚደረጉ ትርክቶች፣ ምክክር፣ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ በቀይ ባሕር ቀጣና የሚስተዋለው የሰላምና ደኅንነት ሥጋት፤ በመርከብ አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖና በፍትሃዊ የወደብ አገልግሎት የዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮን የሚዳስሱ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው መድረክ በቀይ ባሕር ቀጣና አዳዲስ የደኅንነት ሥጋቶችን፣ ፍትሃዊ የወደብ አጠቃቀምና የዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮዎች ላይ መፍትሔ አመላካች ኃሳቦች ቀርበዋል።