የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በይፋ ተጀምሯል፡፡


 

ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሂደት የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፉን በስኬት አጠናቆ የምክክር ምዕራፉን የጀመረ ሲሆን በሂደቱ የአጀንዳ ግብአት የሚዘጋጅበትና በሀገራዊ ጉባዔ የሚወከሉ ተሳታፊዎች የሚመርጡበት ይሆናል። 

በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች መካከል ያብባል ባሳዝን፤ ምክክሩ የሀገር መፃኢ ተስፋ የተጣለበት፣ የምንፈልገውን ሰላም የምናረጋግጥበት ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ በንቃት እየተሳተፍን ነው ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ኤልያስ ገድሉ፤ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በመሆኑ በባለቤትነት ስሜት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።


 

አቶ እንዳለ ደነቀ እና አቶ መዝገቡ አብዩ፤ በበኩላቸው ለችግሮቻችን የመፍትሄው አካል ለመሆን ውይይትን አማራጭ ማድረግ የግድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን ሂደቱ በአካታችነት፣ ግልጽነት፣ አሳታፊነት የሚቀጥል መሆኑን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም