ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን - ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦አገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የአገሪቱን እድገትና ብልጽግና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የወልቂጤና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን አሁን ላይም በአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፉን እያካሄደ ነው።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) እንደተናገሩት የአገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይም ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሰርቷል።

በተለይም ለአገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና መሥራት እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም ተመካክሮ፣ ኃሳብ አዋጥቶና ተግባብቶ መሄድ እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ ሲያስገነዝብ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ኮሚሽኑን የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ያሉት ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ናቸው።

ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች አገር ለማስረከብ ምክክሩን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ስኬት የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም