የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የገንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሙሉጌታ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት ለአገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ችግሮቿን በንግግር መፍታት እንዳለባት ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች ላይ አጀንዳ ለመለየትና አጀንዳ የሚለዩ ሰዎችን ለማስመረጥ የሚያግዙ ሰዎችን ምክር ቤቱ ወክሎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀምና ውይይትን ልምድ በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመሆኑም በጋራ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች አለን የምንለውን ነገር በምክክር ኮሚሽን ተወያይተን ለአገር ሥጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን እናሻሽላለን የሚል ተስፋ አለን ብለዋል።
አገራዊ ምክክሩ ከታችኛው ማህበረሰብ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ያለው ሂደት የሚስተዋሉ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
በምክር ቤትም ሆነ በፓርቲ ለምክክሩ መሳካት እያደረገ ያለውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በባለቤትነት ስሜት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን የክልላዊና ከተማ አስተዳደሮች የሚደረገው የምክክር ምዕራፍ በኅብረተሰብ ክፍሎች ውይይት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መጀመሩን አውስተዋል።
ይህ ሂደት የምክክር ሃሳብን ማዳበር፣ ማዳመጥ፣ መከባበር፣ የሌሎችን ሃሳብ ማክበር የሚንጸባረቅበት ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት በእቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ከነገ ጀምሮ ከኅብረተሰብ ክፍል፣ ከመንግሥት፣ ከተለያዩ ማኅበራትና ተቋማት በአንድ ላይ በሚያደርጉት ውይይት የሃሳብ ብዝሃነትን በማክበርና በመደማመጥ በአጀንዳዎች ላይ እንዲመክሩ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡና ወቅታዊ ችግሮች መፍቻ ምክረ ኃሳቦችን ለማውጣት መመካከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሯ በአጽኖት አንስተዋል።
ውጤታማ የሆነ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች መለየትና በአጀንዳዎች ላይ ከመግባባት መድረስ እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።