ለአስም በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለአስም በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
ለአስም በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ሐኪም ዶክተር ፍጹም አሸብር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለአስም ስለሚያጋልጡ መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄና ሕክምናው አብራርተዋል።
• ምንድንነት
የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት፤ አስም ለረጅም ጊዜ የሚኖር የመተንፈሻ አካላት ህመም ነው።
የመተንፈሻ አካላት በቀላሉ፣ በተለያየ ሁኔታና መጠን መዘጋት ሲያጋጥም ‘አስም’ እንደሚባልም አስረድተዋል።
• ምልክቶች
የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት መጨናነቅ እና ሳል ከአስም ምልክቶች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ምልክቶቹም በአብዛኛው በሌሊት ወይም በማለዳ እንደሚባባሱ አስገንዝበዋል።
• የአስም ዓይነቶች
1. የአለርጂ አስም፡- ይህ የአስም ዓይነት በአለርጂዎች የሚቀሰቀስ መሆኑን ገልጸዋል። ለምሳሌ አቧራ፣ የአበባ ዱቄት (ዘር)፣ የእንስሳት አይነ ምድር ሽታዎች ለዚህኛው አስም አጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
2. አለርጂ ያልሆነ አስም፡- ይህ ደግሞ በኢንፌክሽን፣ በቀዝቃዛ አየር እንዲሁም በተበከለ አየር የሚነሳ የአስም ዓይነት መሆኑን ነው ያስረዱት።
3. በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምክንያት የሚመጣ አስም፡- አካላዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት እንዲሁም ከሥራ በኋላ የሚከሰት የአስም ዓይነት መሆኑን ገልጸዋል።
4. ከሥራ ጋር የተያያዘ አስም፡- በሥራ ቦታ ተጋላጭነት ምክንያት የሚቀሰቀስ የአስም ህመም ዓይነት መሆኑን አስረድተዋል።
5. ከባድ የአስም በሽታ፡- ይህኛው የአስም ህመም ዓይነት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እና ባብዛኛው ባዮሎጂካል ሕክምናን የሚፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል።
• አጋላጭ (ለህመሙ መባባስ) መንስዔዎች
አለርጂዎች (የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ የዓየር ብክለት፣ ጭስ)፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ቀዝቃዛ የዓየር ሁኔታ፣ ጭንቀት እንዲሁም የጄኔቲክ ቅድመ-ዝንባሌ ለአስም ህመም ከሚያጋልጡ እና ህመሙን ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።
• አስም ያለባቸው ሰዎች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ያድርጉ?
👉ከአቧራ፣ ጭስ፣ አለርጂዎችዎች መራቅና መጠንቀቅ፤
👉 በኢንፍሉዌንዛ እና በኒሞኮካል ክትባቶች ወቅታዊ ክትባቶችን መውሰድ፤
👉 በቀዝቃዛ የዓየር ሁኔታ ሙቀት የሚሰጡ መከላከያ ልብሶችን መልበስ፤
👉 ጥሩ እንቅልፍ መተኛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የተመጣጠነ አመጋገብን ማዘውተር እና መሰል ተግባራት የአስም ህመም እንዳይባባስ ያግዛሉ ብለዋል ባለሙያው።
• ሕክምናው
የአስም ህመም የማስታገሻ እና የመቆጣጠሪያ (የረዥም ጊዜ) ሕክምናዎች እንዳሉት ያስታወቁት ባለሙያው እንደ ህመሙ ሁኔታ ስለሚወሰን ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባ መክረዋል።
በተለይም ምልክቶቹ በተባባሱበት ወቅት ከፍተኛ የዓየር ትቦ መዘጋት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ በጊዜ ሕክምናውን ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።
ከ 3 እስከ 10 በመቶ ያህሉ የዓለም ሕዝብ በአስም ተጠቂ መሆኑንም ጠቁመዋል።
#Ethiopian_News_Agency #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት
#ኢዜአ #የጤና_ነገር