የጡት ካንሰርን ለመከላከል … - ኢዜአ አማርኛ
የጡት ካንሰርን ለመከላከል …
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
የጡት ካንሰርን ለመከላከል …
ለጡት ካንሰር ላለመጋለጥ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ፣ ስለ አጋላጭ ምክንያቶቹ እንዲሁም ምልክቶቹና ሕክምናው የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቢኒያም ተፈራ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
መነሻ - ካንሰር እንዴት ይከሰታል?
እንደ ዶክተር ቢኒያም ገለጻ፤ ጤናማ የሰው ልጅ በሕይዎት ዑደት ሲያልፍ በሰውነቱ ውስጥ ያሉ ኅዋሶች (ሴሎች) በመደበኛ ሁኔታ ይራባሉ፤ ጊዜያቸውን ጠብቀውም ይሞታሉ። ይህን ሂደት በተፈጥሮ መቆጣጠር የሚቻልና የራሱ የሆነ የመቆጣጠሪያ መንገድ ያለው መሆኑንም ያስረዳሉ።
ነገር ግን ይላሉ በአንዳንድ ምክንያቶች (በዘረመል ለውጥ ወይም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ሊሆን ይችላል)፤ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ መራባት ሲጀምሩና ወይም መሞት ባለባቸው ጊዜ ሳይሞቱ ሲቀሩ፣ በራሳቸው አካባቢ ከመጠን በላይ በማደግ እንደ ዕጢ ያለ ነገር ሲፈጥሩ፤ ከዚህ አልፎ በአካባቢያቸው ያሉ ኦርጋኖችን መያዝ ሲጀምሩ እንዲሁም ወደ ሌላ የሰውነት አካል በመሄድ ባልተፈቀደላቸው ቦታ ላይ ማደግና ያለቁጥጥር መራባት የሚጀምሩበት ሂደት ካንሰር ተብሎ ይጠራል።
ካንሰር ስሙ የሚሰየመው እንደተከሰተበት የሰውነት ክፍል መሆኑን አስገንዝበው፤ የጡት ካንሰር፣ የአንጀት ካንሰር፣ የቆዳ ካንሰር … እየተባለ የሚጠራው በዚሁ አግባብ መሆኑን አስረድተዋል።
የጡት ካንሰር ምልክቶች
በጡት ውስጥ ቀደም ሲል ያልነበረ (አዲስ) ዕብጠት መከሰት፣ የጡት ቆዳ ቀለም መለወጥ፣ ቁስለት መኖር፣ ከጡት ጫፍ ላይ መግል ወይም ደም መሰል ፈሳሽ መውጣት፣ በብብት ሥር አካባቢ የሚከሰት ዕብጠት በአብዛኛው የጡት ካንሰር ምልክቶች መሆናቸውን አብራርተዋል። እነዚህ ምልክቶች ኬዙ አድጎ መታየት ሲጀምር የሚስተዋሉ መሆናቸውን በመጠቆም፤ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ምልክቶች ሳይኖሩ የጡት ካንሰር የመያዝ ዕድል መኖሩን አመላክተዋል።
ወደ ጤና ተቋም መቼ መሄድ ይመከራል?
የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት፤ በአጠቃላይ አንዲት ሴት ጡቷ ላይ ቀደም ሲል ያልነበረ አዲስ ለውጥ ካለ ካንሰር ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል በመገመት ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይጠበቅባታል።
ነገር ግን ከካንሰር ጋር በተያያዘ ጥርጣሬን ሊጨምሩ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመው ከነዚህም አንዱ በጡት ውስጥ ዕብጠት መኖርና ዕብጠቱም ምንም ዓይነት ህመም የሌለው መሆንን ጠቅሰዋል። አክለውም እስከ 80 በመቶ የሚሆነው በዕብጠት የሚመጣ የጡት ካንሰር ህመም እንደሌለው አንስተዋል። ህመም የለውም ብሎ ዕብጠትን ችላ ማለት እንደማይገባም በመምከር።
በአጠቃላይ አንዲት ሴት ከላይ የጡት ካንሰር ምልክቶች ተብለው የተዘረዘሩትን ካየች በአፋጣች ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚጠበቅባት በአጽንዖት ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአጠቃላይ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ጡታቸውን እየዳበሱ ከወትሮው የተለየ አዲስ ምልክት መኖሩን ማየት እንዳለባቸው መክረው፤ የተለየ (አዲስ) ነገር ሲኖር ወደ ሕክምና እንዲሄዱ አሳስበዋል።
የአሳሳቢነት ደረጃ
የጡት ካንሰር በጣም አሳሳቢ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ቢኒያም፤ ከካንሰር ዓይነቶች ሁሉ በሀገራችን በቀዳሚነት ይቀመጣል ብለዋል።
በተለይም ይላሉ፤ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች 1/3ኛ (31 በመቶ ገደማ) ያህሉ የጡት ካንሰር ነው። በእርግጥ ወንድንም ሴትንም ብንደምረው በብዛትም ሆነ በሽታ በማስከተል ረገድ በአንደኝነት የሚቀመጥ ነው ይላሉ።
ስለ ጡት ካንሰር ያለ ግንዛቤ
በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለ ጡት ካንሰር አጠቃላይ ሁኔታዎች ሰፊ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ገልጸው፤ ለአብነትም ከ2/3ኛ በላይ የሚሆነው ታማሚ ወደ ሕክምና ተቋም የሚመጣው በሽታው በጣም ሥር ከሰደደ በኋላና ችግር መፍጠር ሲጀምር መሆኑን አንስተዋል።
በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋም የሚሄዱት ሴቶች ቁጥር በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን (ከ30 በመቶ በታች) መሆኑንም አመላክተዋል። ይህ ሁሉ የሆነው በግንዛቤ እጥረት እንደሆነ ይታመናል ብለዋል።
በመንግሥታዊና በግል ተቋማት ጭምር ለአብነት የጥቅምት ወርን የጡት ካንሰር ወር አድርጎ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ስለጡት ካንሰር በአግባቡ አለማወቅ እንዲሁም በጡት ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶችን ልብ አለማለት (ቀለል አድርጎ በማሰብ ሥር እንዲሰድ ዕድል መስጠት) እንዳለ አብራርተዋል።
በጡት ካንሰር የሚከሰት ሞትን ከፍ ከሚያደርጉት አንዱ የግንዛቤ እጥረት እንደሆነ ይታመናል ይላሉ።
በወንዶች ላይ የጡት ካንሰር
በወንዶች ላይም የጡት ካንሰር ሊከሰት እንደሚችል የሚናገሩት የሕክምና ባለሙያው፤ የሚከሰትበት መጠን (ቁጥር) ግን በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ላይ ቁጥሩ በዛ ቢልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 በመቶ በታች መሆኑንም ገልጸዋል።
ዕድሜያቸው ከፍ ባሉ ወንዶች ላይ እንደሚከሰት በመግለጽ፤ ወንዶች በጡታቸው ላይ የተለየ ምልክትና ህመም ሲሰማቸው ወደ ሕክምና መሄድ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
የጡት ካንሰር በሕጻናትና አዳጊዎች ላይ አይከሰትም ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ የመከሰት ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ዶክተር ቢኒያም አስረድተዋል። እዚህ ላይ ብዙም አያሳስብም ይላሉ።
ዕድሜና የጡት ካንሰር
በአብዛኛው የጡት ካንሰር የሚከሰተው ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ቢኒያም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ከ50 ዓመት በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ የመከሰት ዕድሉ ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አብዛኛው ሕዝብ ወጣት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ከ70 እስከ 80 የሚሆኑት የጡት ካንሰር ታማሚዎች ከ30 እስከ 50 ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ስለዚህ ዕድሜያቸው ገፋ ባሉም ሆነ በወጣቶች ጡት ላይ አዲስ ህመም ሲስተዋልና ምልክት ሲታይ ቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ እንጅ፤ ከ50 ዓመት በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው ብሎ ችላ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ለጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች
እንደ ሕክምና ባለሙያው ማብራሪያ፤ የጡት ካንሰር እኛ ቀድመን ብንሠራባቸው ተጋላጭነትን የምንቀንስባቸው እና ከቁጥጥራችን ውጭ በሆኑ (ተፈጥሯዊ) ሁኔታዎች የምንጋለጥባቸው ጉዳዮች አሉ።
ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች
የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ (ፕሮሰስ የተደረጉ) ምግቦችን ማዘውተር፣ አትክልትና ፍራፍሬ አለመመገብ ተጋላጭነቱን እንደሚጨምሩ አንስተዋል። እነዚህን በማስተካከል ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች
የዕድሜ መጨመር፣ ሴት መሆን፣ በዘረመል (በጀኔቲክ) ለውጥ (በቤተሰብ ወይም በሕይዎት አጋጣሚ ከአካባቢያዊ ሁኔታ የሚመጡ የዘር መለወጦች) ለጡት ካንሰር ሊያጋልጡ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
እነዚህን ምንም ማድረግ እንደማይቻል በመግለጽ መፍትሔው ምልክት (ጥርጣሬ) ሲኖር ጊዜ ሳያባክኑ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ነው ይላሉ።
ሕክምና እና የመዳን ተስፋ
የጡት ካንሰር የመዳን ተስፋው ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የሚወሰነው ግን ህመሙ እንደተገኘበት ደረጃ (ስቴጅ) ነው ይላሉ።
[6/16/2026 9:29 AM] awe: በአጠቃላይ ሲታይም፤ ቶሎ ወደ ሕክምና በመሄድ የታከመ ካንሰር የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ባብዛኛው የሚሰጡ የሕክምና አማራጮችም፤ ኦፕሬሽን፣ ኬሞቴራፒ፣ የጨረር ሕክምና፣ የሆርሞን ሕክምና ሲሆኑ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ እንደሁኔታው ታርጌትድ ቴራፒ እና ሚኖቴራፒ የሚባሉ የሕክምና አማራጮች መኖራቸውን ዘርዝረዋል።
የሕክምና አማራጩን የሚወስነው በሽታው የተገኘበት ደረጃ (ስቴጅ) መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ምክረ ሐሳብ
ሕብረተሰቡ እንዲገነዘበው የምንፈልገው ቶሎ ከታወቀ የጡት ካንሰር ታክሞ ይድናል፤ ለዚህ ደግሞ በጡት ላይ አዲስ ነገር ሲስተዋል ቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ አዋጭ መሆኑን ነው ብለዋል።
በጡት ላይ የሚስተዋል ዕብጠትና ህመም ሁሌም ካንሰር ነው ማለት ስላልሆነ ሴቶች ሳይደናገጡ ምርመራ እንዲያደርጉ መክረው፤ የምርመራ ውጤቱ ካንሰር መሆኑን ቢያሳይ እንኳ ቶሎ ወደ ሕክምና እስከሄዱ ድረስ በቀላሉ መዳን እንደሚችል መገንዘብ እንዳለባቸውም መክረዋል።
ሕብረተሰቡ በአጠቃላይ ከጡት ካንሰር ጋር በተያያዘ ከሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች መቆጠብ እንደሚገባውም ይመክራሉ።
ቢያንስ ዕድሜያዋ ከ20 ዓመት በላይ የሆናት ሴት በወር አንድ ጊዜ ጡቷን በመዳበስ (ዕብጠትም ካለ እንዲታያት በመስታዎት ፊት ሆና በመመልከት) ቀደም ሲል ያልነበረ አዲስ ነገር መኖሩን መከታተል ይጠበቅባታል። ይህም ኬዙ ቢከሰት እንኳ ቶሎ ለመዳን ስለሚያግዝ ይላሉ።
ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ደግሞ ቢቻል በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የጡት ቅድመ ምርመራ እንዲደርጉ መክረዋል።
#ኢዜአ #የጡት_ካንሰር #የጤና_ነገር