ሕጻናትን ለውስብስብ ችግር እየዳረገ ያለው የስኳር ህመም (Diabetes) - ኢዜአ አማርኛ
ሕጻናትን ለውስብስብ ችግር እየዳረገ ያለው የስኳር ህመም (Diabetes)
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
· ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሕጻናት ላይ የትኛው የስኳር ህመም ነው በስፋት እየተከሰተ ያለው?
በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ የስኳር ህመም ዓይነቶች መኖራቸውን የሚገልጹት የሕጻናት የስኳር ህመም ስፔሻሊስት ዶክተር ሰውአገኝ የሺዋስ፤ እንደሀገራችን ግን በዋናነት የሚጠቀሰው ዓይነት አንድ የሚባለው የስኳር ህመም ነው ይላሉ።
በአደጉ ሀገራት ላይ ዓይነት ሁለት የስኳር ህመምም በሕጻናት ላይ እንደሚከሰት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።
ዓይነት ሁለት የስኳር ህመም ባብዛኛው እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ከኑሮ ዘይቤ እንዲሁም ከመጠን ባለፈ ውፍረትና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት የሚከሰት መሆኑንም ያስረዳሉ።
ይሁን እንጅ በእኛ ሀገር ደረጃ ይህ (ዓይነት ሁለት የስኳር ህመም) በስፋት በሕጻናት ላይ እንደማይስተዋልና ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
በዋናነት በእኛ ሀገር ሕጻናት ላይ እየተከሰተ ያለው ዓይነት አንድ የስኳር ህመም መሆኑን ገልጸው፤ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ ልጆች ለውስብስብ ችግር እየተዳረጉ ነው ብለዋል።
እንደዋዛ የበርካቶችን በር የሚያንኳኳው ዲጂታል (ቨርቹዋል) ኦቲዝም
· ለዓይነት አንድ የስኳር ህመም አጋላጭ ምክንያቱ ይታወቃል?
እንደ ባለሙያው ገላጸ፤ ለዓይነት አንድ የስኳር ህመም አጋላጭ መንስዔው አይታወቅም። ይህን ተከትሎም አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ሕክምና የለም።
እንደ አጋላጭ ከሚታሰቡት መከካል ግን፤ ልጆች በተፈጥሮ ለዓይነት አንድ የስኳር ህመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑ እና ውጫው (አካባቢያዊ ሁኔታዎች) በምክንያትነት ይነሳሉ ብለዋል።
በእነዚህ ምክንያቶች በእያንዳንዱ የሰውነት እንቅስቃሴ ውስጥ ስኳር እንዲዋሃድ የሚያደርገው ኢንሱሊን የተሰኘ ሆርሞን መመረቱ ይቆማል፤ የኢንሱሊን እጥረት ሲያጋጥም ደግሞ ስኳር ደም ላይ እየጨመረ ይሄዳል፤ ደም ከ180 በላይ ከፍ በጊዜም ኩላሊት ወደ ውጭ ያስወግደዋል፤ በዚሁ ወቅትም ጠቃሚ ንጥረ ቅመሞች ጭምር ከሰውነት ይወገዳሉ፤ የፈሳሽ እጥረትም ያጋጥማቸዋል፤ ከዚያም የልጆች የሰውነት ክብደት መቀነስና ቶሎ ቶሎ (ከመደበኛው የተለየ) የመሽናት ሁኔታ ይከሰታል ሲሉ አብራርተዋል።
· ዓይነት አንድና ዓይነት ሁለት የስኳር ህመም
እንደ ዶክተር ሰዋገኝ ማብራሪያ፤ ዓይነት አንድ እና ዓይነት ሁለት የስኳር ህመሞች የተለያዩ ናቸው።
ዓይነት አንድ የስኳር ህመም ማለት፤ ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ሳይመነጭ ሲቀር የሚከሰት መሆኑን አስረድተዋል። ይህን ህመም ቀድሞ መከላከል አይቻልም፤ ሲከሰት ሕክምና ማግኘት እንጅ ይላሉ።
ዓይነት ሁለት የስኳር ህመም፤ ኢንሱሊን የማመንጨት ችግር ሳይሆን፤ ኢንሱሊኑ በሰውነት ውስጥ ሳይሠራ ሲቀር የሚከሰት ነው ይላሉ። ይህም ከሰውነት ክብደት መጨመር፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ባለማድረግ ምክንያት የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲውም ብዙ ጊዜ በዐዋቂዎች ዘንድ በስፋት የሚስተዋል ህመም መሆኑንም አመላክተዋል።
ይህን ህመም አመጋገብን በማስተካከል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የኑሮ ዘይቤን በማስተከከል ቀድሞ መከላከል እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት።
· የስኳር ህመም በየትኛው የዕድሜ ክልል ይከሰታል?
ዓይነት አንድ የስኳር ህመም የ6 ወር ዕድሜ ካለው ሕጻን ጀምሮ እስከ በዐዋቂነት የዕድሜ ክልል ሊከሰት እንደሚችል ዶክተር ሰውአገኝ ይናገራሉ።
ይህን ሲያብራሩም በተለይም ከ30 ዓመት በታች ባሉት የዕድሜ ክልሎች (በተለይም ከ5 - 7 እንዲሁም ከ14 - 15 ዓመት) ባሉ ልጆች ላይ በስፋት ከሰታል ብለዋል።
· ምልክቶቹ በውል ይታወቃሉ?
በአብዛኛው ከተለመዱ ምልክቶች መካከል፤ ቶሎ ቶሎ ውኃ መጠጣት፣ የማይረካ የውኃ ጥማት መኖር፣ ከወትሮው የተለየ ሌሊትን ጨምሮ ሽንት የመሽናት፣ ክብደት መቀነስ የሚሉት እንደሚገኙበት ይገልጻሉ።
እነዚህ ምልክቶች ሲታዩም ጊዜ ሳያባክኑ (ህመሙ ሥር ሳይሰድ) ቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ ተገቢ መሆኑን መክረዋል። በዚህ ሂደት ልጆች ህመማቸውን ዐውቀውና ራሳቸውን ችለው ወደ ሕክምና ተቋም እንደማይሄዱ ስለሚታወቅ ወላጆች (አሳዲዎች) ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዓለም ላይ አሳሳቢ ደረጃ ከደረሱ የህመም ዓይነቶች አንዱ
· ሕክምና እና ምክረ ሐሳብ
ምንም እንኳ አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል የታወቀ ነገር ባይኖርም ዓይነት አንድ የስኳር ህመም፤ ቶሎ ከታወቀና ሕክምና ከተደረገለት ልጆች እንደማንኛውም ጤናማ ልጅ ዕድገታቸው ይቀጥላል፣ ትምህርታቸውን መማር፣ ኑሯቸውን መቀጠል ይችላሉ።
ልጆች በጊዜው (ህመሙ እንደተከሰተ ወዲያውኑ) ካልታከሙ ሕይዎታቸውን እስከማጣት የሚደርስ ውስብስብ ችግር የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤ ወላጆች (አሳዳጊዎች) የልጆቻቸውን ጤና በአግባቡ እንዲከታተሉ መክረዋል።የተለየ ምልክት ሲያስተውሉም ወደ ሕክምና መሄድን መክረዋል።
ምንም እንኳን አመጋገብን ማስተካከል ለጤና እንደ ግብዓት ተጠቃሚ መሆኑ ቢታመንም፤ ዓይነት አንድ የስኳር ህመምን በአመጋገብ ብቻ እናስተካክላለን በሚል መዘናጋት ተገቢ እንዳልሆነ ሕብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
በአመጋገብ ብቻ እናስተካክላለን ማለት ቶሎ እንዳይታከሙ ጊዜ በማባከን የልጆችን ጤና በይበልጥ ማወሳሰብ በመሆኑ፤ አዋጩ መፍትሔ በሕክምና ኢንሱሊን መስጠት እና በተጨማሪ አመጋገብን ከኢንሱሊኑ ጋር ማጣጣም መሆኑን አስገንዝበዋል።