እንደዋዛ የበርካቶችን በር የሚያንኳኳው ዲጂታል (ቨርቹዋል) ኦቲዝም -- - ኢዜአ አማርኛ
እንደዋዛ የበርካቶችን በር የሚያንኳኳው ዲጂታል (ቨርቹዋል) ኦቲዝም --
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
እንደዋዛ የበርካቶችን በር የሚያንኳኳውን ዲጂታል (ቨርቹዋል) ኦቲዝም እንዴት መከላከል ይቻላል? አንድ ሰው ኦቲዝም አለበት የሚባለው ምን ዓይነት ምልክቶች ሲታዩበት ነው?
ከቨርቹዋል ኦቲዝም መንስዔ፣ ምልክቶቹ፣ የሚያስከትለው ጉዳትና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ወ/ሮ መዓዛ መንክር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
መነሻ
ልጆች በአራት የዕድገት ዘርፎች እንደሚያድጉ ያነሱት ወ/ሮ መዓዛ፤ እነሱም የቋንቋ ክኅሎት ዕድገት፣ የአዕምሮ (ነገሮችን፣ ሁኔታዎችን) የመረዳት ዕድገት፣ አካላዊ ዕድገት እና የማኅበራዊ መሥተጋብርና የተግባቦት ዕድገት መሆናቸውን ያብራራሉ።
በዚህም መሠረት ይላሉ ባለሙያዋ፤ አንድ ልጅ ጤናማ ወይም ሙሉ ዕድገት አለው የሚባለው በአራቱም የዕድገት ደረጃዎች በተመጣጠነ ሁኔታ ሲያድግ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
ምንድንነት?
ባለሙያዋ ኦቲዝም በሁለት ተከፍሎ እንደሚታይ ጠቁመው፤ የመጀመሪያው ከመጀመሪያ ጀምሮ በሕክምና የተረጋገጠ በኦቲዝም ጥላ ሥር ያሉ ልጆች ወይም “ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር” (ዋናው ኦቲዝም) እንደሚባል ይገልጻሉ።
ሁለተኛው ቨርቹዋል ኦቲዝም መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ማለት ደግሞ ኦቲዝም የሚመስል ምልክቶች የሚያሳዩ ልጆችን የሚገልጽ እንጅ፤ ዋናው ኦቲዝም እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ነገር ግን ይላሉ ወ/ሮ መዓዛ፤ አንድ ልጅ ከላይ ከተገለጹት ከአራቱ ሁለቱ በተለይም የቋንቋ ክኅሎት እና የማኅበራዊ መሥተጋብርና የተግባቦት ዕክል ሲገጥመው፤ ዋናው ኦቲዝም አለበት እንደሚባል አስገንዝበዋል።
ለቨርቹዋል ኦቲዝም አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ልጆች ከተወለዱ እስከ 3 ዓመት ባለው ዕድሜያቸው ለተንቃቃሽ ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ ቴሌቪዥን (ለስክሪኖች) ለረጅም ሠዓታት በድግግሞሽ ተጋላጭ ሲሆኑ ለኦቲዝም መሰል ምልክቶች (ቨርቹዋል ኢቲዝም) ተጋለጡ ተብሎ እንደሚወሰድ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም ልጆች ከሰዎች ጋር ባለመቀራረብ፣ በገሃዱ ዓለም የሚደረገውን ነገር ካላማየት የተነሳ ያልተለመዱ (አዳዲስ) ባሕርያትን እንደሚያዳብሩ ጠቁመው፤ እነዚህ ባሕርያትም ኦቲዝም መሰል (ቨርቹዋል ኦቲዝም) መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ጉዳዩን በምሳሌ ሲያብራሩም፤ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተግባብቶ መጫወት ምን እንደሆነ አለማወቅ፣ ተረጋግቶ መቀመጥ አለመቻል፣ በገሃዱ ዓለም ለሚደረጉ ነገሮች ትኩረት አለመስጠት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ለስክሪን እና ዲጂታል ለሆኑ ነገሮች ሱሰኛ መሆን (ምግብ ሲበሉ ሞባይል መያዝ፣ ቴሌቪዥን ዕያዩ መብላት መፈለግ)፣ ማንኛውንም ነገር ሞባይል ወይም ቴሌቪዥን ካልተከፈተ ማድረግ አለመቻል (አለመፈለግ) የሚሉት የቨርቹዋል ኦቲዝም ምልክቶች መሆናቸውን ነው የዘረዘሩት።
ይህን ተከትሎም ይላሉ ባለሙያዋ፤ የቋንቋ ክኅሎታቸው እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው የዳበረ አይሆንም፤ ከዚህም ሲያልፍ ኦቲዝም መሰል ምልክቶች በሚኖሩበት ወቅት በቀላሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመግባባት በጣም ይቸገራሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።
የኦቲዝም መንስዔ ምንድን ነው? እንዴት መጣ? የሚለው እስካሁን በመጠናት ላይ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዋ፤ ቨርቹዋል ኦቲዝም ግን መንስዔው እንደሚታወቅ አረጋግጠዋል። መንስዔውም ልጆች ለረጅም ሠዓትና በድግግሞሽ (ለብዙ ጊዜያት) ለስክሪን ተጋላጭ መሆናቸው ነው ይላሉ።
ልጆች ቴክኖሎጂን መቼ ይጠቀሙ?
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፤ ልጆች ከተወለዱ እስከ ሁለት ዓመት በፍጹም እንዳይጠቀሙ ይመከራል። በአንጻሩ ከወላጆቻቸው ጋር እንዲያወሩ፣ አካባቢያቸውን እንዲያዩ፣ በመንቀሳቀስና በመነካካት ገሃዱን ዓለም እንዲረዱ እንደሚመከር አመላክተዋል።
ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከሁለት እስከ ስድስት ዓመታቸው፤ ቋንቋን (ንግግርን) የሚያበረታቱ፣ ትምህርት ሰጭ ሆነው ከተገኙ ከአዋቂዎች ጋር በመሆን የጨዋታ ክኅሎትን የሚያዳብሩ ንግግር ያላቸው (መዝሙሮችና ሌሎችንም) በቀን ለ30 ደቂቃ እንዲመለከቱ ማድረግ ይመከራል ብለዋል።
ንግግር የሌላቸው ቪዲዮዎች ግን ልጆች ከፊልሙ ዐይተው እንኳን ቋንቋ እንዳይማሩ ስለሚገድቡ ለልጆች ተገቢ አይደሉም ይላሉ።
ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ለሆናቸው ግን ትምህርታዊ ጉዳይ ከሆነ እና ልጄ ስነግረው ስላልገባው በስክሪን ሳሳው ሊገባው ይችላል ብለው ወላጆች ሲያስቡ ለዚያውም ከአዋቂዎች ጋር በመሆን ለማስተማር ብቻ እስከ 30 ደቂቃ በቀን መጠቀም ቢችሉ ጥሩ ነው ብለዋል።
እነማን ተጋላጭ ናቸው?
ብዙ ጊዜ ወላጆች ባለማወቅ ልጆች ሲንቀሳቀሱ፣ ያገኙትን ሲነካኩ ጥፋት ይከሰታል፣ ይወድቃሉ … በሚል እሳቤ አርፈው እንዲቀመጡ በማሰብ ስልክ ይሰጧቸዋል፤ ቴሌቪዥንም ይከፍቱላቸዋል የሚሉት ወ/ሮ መዓዛ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሉ ልጆች ተጋላች መሆናቸውን አንስተዋል።
ስለዚህ ወላጆች ለረጂም ሠዓት እና በተደጋጋሚ ጊዜ ታብሌት፣ ስልክ እና ቴሌቪዥን ለልጆች መክፈት ለቨርቹዋል ኦቲዝም እንደሚያጋልጥ ተገንዝበው፤ የልጆቻቸውን ጤና ከማወክ ቢቆጠቡ መልካም መሆኑን አመላክተዋል።
ልጆች በቨርቹዋል ኦቲዝም መጠቃታቸውን ማወቅ ይቻላል?
እንደ ወ/ሮ መዓዛ ማብራሪያ፤ ልጆች በቨርቹዋል ኦቲዝም መያዛቸውን ወላጆችም በቤታቸው ማወቅ ይችላሉ፤ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድም በምርመራ ማወቅ ይቻላል።
ወላጆች በቤት ውስጥ መለየት የሚችሉበት ስልትም፤ ቴሌቪዥን ሲጠፋ፣ ሞባይል ሲከለከሉ ልጆች በከፍተኛ ሁኔታ የሚበሳጩ ከሆነ፣ ምግብ አልበላም የሚሉ ከሆነ፤ አልታዘዘም ካሉ፣ ተረጋግተው የማይቀመጡ ከሆነ፣ እየተንቀሳቀሱ ቁጣቸውን የሚገልጹ ከሆነ እነዚህ ምልክቶች ሱስ እንደሆነባቸው ይጠቁማል ይላሉ።
በተጨማሪም የንግግር መዘግየት ካለ፣በአካባቢያቸው ስለሚከናወኑ ሁኔታዎች ብዙም ትኩረት የማይሰጡ ከሆነ የቨርቹዋል ኦቲዝም ምልክቶች መሆናቸውን በመግለጽ፤ ለተሻለ የባለሙያ እገዛ በዚህ ጊዜ ልጆችን ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ እንደሚገባ ይመክራሉ።
ሕክምና
ቀዳሚው የሕክምና አካል የኦቲዝሙን ዓይነት በምርመራ መለየት መሆኑን ወ/ሮ መዓዛ አስረድተዋል።ይህም ማለት በኦቲዝም ጥላ ሥር ያሉ ልጆች (ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር) ነው ወይስ ቨርቹዋል ኦቲዝም ነው የሚለው ከተለየ በኋላ ወደ ቀጣዩ ሂደት መሄድ ይገባል ይላሉ።
በዚህም መሠረት፤ ልጆ ከስክሪን (ቴሌቪዥን፣ ሞባይል፣ ታብሌት…) እንዲከለከሉ ማድረግ የሕክምናው አካል መሆኑን ነው ያመላከቱት።
በተጨማሪም ከቤት ወጥተው ከልጆች ጋር እንዲጫወቱ ብሎም የገሃዱን ዓለም እንቅስቃሴ፣ የአኗኗር ሁኔታ እንዲያዩ እና እንዲረዱ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
የቋንቋ (ንግግር) መዘግየቱ ከባድ ከሆነ (ከእኩዮቻቸው በጣም ወደ ኋላ የቀሩ ከሆነ) ደግሞ ልጆቹ “ስፒች ቴራፒ” እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።
አክለውም ወላጆች ልጆችን ወደ ቤተሰብ እንዲሁም ወደ መዝናኛ ስፍራ ይዘዋቸው በመሄድ ከሰዎች ጋር ያላቸውን መቀራረብ እንዲያሳድጉ ትኩረትና ጊዜያቸውን ለልጆች መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ወ/ሮ መዓዛ እንዳሉት፤ ከላይ የተጠቀሱት አማራጮች ተደርገው መሻሻል ከሌለ (ልጆቹ ካልተሻላቸው) ዋናው ኦቲዝም (በኦቲዝም ጥላ ሥር ያሉ ልጆች/ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር) ሊሆን ይችላል ብለዋል። ስለዚህ ለዚህኛው የሚሆነውን የሕክምና ክትትል በባለሙያ ታግዘው ማከናወን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ግን የኦቲዝም ሕክምና ባብዛኛው ከመድኃኒት ይልቅ በትምህርታዊ ሥልጠና በመታገዝ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ የሚድንበትን ጊዜ ማወቅ እንደማቻል አመላክተዋል። በእርግጥ መድኃኒት የሚታዘዝበት ጊዜም እንዳለ ጠቁመው፤ ይህም ከፍተኛ የሆነ የእንቅልፍ ማጣት ካለ፣ ቤተሰብን የመረበሽ ነገር ካለ፣ ከፍተኛ የሆነ አስቸጋሪ ባሕርይ ሲኖር በባለሙያ ታይቶ ነው ብለዋል።
ምክረ ሐሳብ
ለቴክኖሎጂ ተጋላጭ መሆን ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ለአጠቃቀሙ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም በከተሞች አካባቢ ልጆች እንዳይረብሹ በሚል ሞባይል፣ ቴሌቪዥን፣ ታብሌትን እንደ ሞግዚት የመጠቀም ልማድ መኖሩን አንስተዋል።
ይህም በልጆች ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ወላጆች (ሠራተኞች፣ ሞግዚቶች) መገንዘብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ምንም እንኳን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠና ጥናት ባይኖርም፤ ከዲጂታል አማራጭና አቅርቦት አኳያ በከተሞች ለቨርቹዋል ኦቲዝም የመጋለጥ ሁኔታው ሰፊ እንደሆነ ይታመናል ሲሉም አመላክተዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #የጤና_ነገር #ኦቲዝም #ቨርቹዋል