ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በገዳይነታቸው ቀዳሚ ከሆኑ አምስት በሽታዎች አንዱ -የሳምባ ምች (ኒሞኒያ)

የጤና ነገር
 
በዮሐንስ ደርበው
 
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ፣ የሳምባ እና የጽኑ ህሙማን ሰብስፔሻሊስት ዶክተር እስማኤል ሙሐመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሳምባ ምች መንስዔዎችን፣ ምልክቶቹን፣ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችና ሕክምናው ሳይንሳዊ ገለጻ አድርገዋል። 
 
· ምንድንነት
 
እንደ ዶክተር እስማኤል ማብራሪያም፤ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ማለት ሳምባ ላይ የሚፈጠር ኢንፌክሽ ነው። ይህም በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚከሰት ያስረዳሉ።
 
· የሳምባ ምች ከተለመዱት የሳምባ ህመሞች በምን ይለያል?
 
ከተለመዱት የሳምባ ህመሞች (አስም፣ ብሮንካይትስ፣ ሲኦፒዲና ሌሎችም …) የሳምባ ምች እንደሚለይም ነው የሚገልጹት።
 
ይህን ሲያብራሩም፤ የተለመዱት የሳምባ ህመሞች (አስም፣ ብሮንካይትስ፣ ሲኦፒዲና ሌሎች …) የሚያጠቁት የሳምባ አየር ቱቦን መሆኑን ገልጸዋል።
 
በአንጻሩ ኒሞኒያ የሚያጠቃው፤ ካርበንዳይ ኦክሳይድ የሚወጣበትንና ኦክስጅን የሚገባበትን (ጋዝ ኤክስቸንጅ የሚካሄድበትን) የታችኛውን የሳምባ ክፍል መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
· መንስዔዎች
 
እንደ ሕክምና ባለሙያው ገላጸ፤ የሳምባ ምች በርካታ መንስዔዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል በዋናነት የሳምባ ምች የሚከሰተው በቫይረስ (40 በመቶ ገደማ) እና በባክቴሪያ (እስከ 50 በመቶ ገደማ) መሆኑን ያብራራሉ።
 
በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ቢሆን በፈንገስ (ከ5 በመቶ በታች) ምክንያት የሚከሰት የሳምባ ምች መኖሩን አንስተዋል።
 
ባብዛኛው በቫይረስና በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የሳምባ ምች በትንፋሽ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍም አረጋግጠዋል ባለሙያው።
 
· ምልክቶቹ
 
ህመሙ ሳምባን እንደሚያጠቃ ያወሱት ባለሙያው፤ ከምልክቶቹ መካከል አንዱ ሳል ማሳል መሆኑን ገልጸዋል። ሳሉ ደረቅ ወይም አክታ ያለው ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፤ የአክታው ቀለምም ነጭ፣ ቢጫ፣ ደም የቀላቀለ ወይም የዛገ ብረት የሚመስል ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።
 
በተጨማሪም ይላሉ፤በሁለቱም ወይም በአንዱ በኩል የደረት ውጋት እና የትንፋሽ ማጠር (ለመተንፈስ መቸገር) ከምልክቶቹ መካከል ናቸው።
 
እንዲሁም የሳምባ ምቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ፤ ራስን መሳት፣ መረበሽ (ኮንፊውዝ መሆን ነገሮችን ወይም ሁኔታዎች ላይ የመዘባረቅ ነገር) ሊስተዋል እንደሚችል አንስተዋል።
 
· ወደ ሕክምና ተቋም መቼ ይሂዱ?
 
በቀላሉ የማይጠፋ ከ24 እስከ 48 ሠዓት የሚቆይ ከፍተኛ ትኩሳት ሲኖር፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት ካለ፣ ከፍተኛ የትንፋሽ ማጠር ሲስተዋል፣ ኮንፊውዝ መሆን (ነገሮችን መዘበራረቅ) ሲኖር፣ ራስን መሳት ካለ እንዲሁም እነዚህ ምልክቶች ዝቅተኛ ቢሆኑ እንኳ ተጓዳኝ ህመሞች ማለትም (የስኳር፣ የኤች አይ ቪ፣ የካንሰር ታካሚ (ኬሞ ቴራፒን ጨምሮ ለካንሰር ህመም መድኃኒት እየወሰዱ ከሆነ)፣ የበሽታ መከላከል ዐቅምን የሚቀንሱ መድኃኒቶች (እንደ ፕሪኒሶሎ ያሉና መሰል) የሚጠቀሙ ከሆነ ወደ ሕክምና በመሄድ ዕርዳታ ማግኘት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
 
ምክንያቱም እነዚህ ታካሚዎች ቶሎ ካልታከሙ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳምባ ምቹ የህመም ደረጃ ከፍ እያለ በመሄድ ለሕይዎት የሚያሰጋበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ነው ብለዋል።
 
·ሳምባ ምችና የአየር ሁኔታ
 
ብርድ (ቀዝቃዛ ዓየር) በራሱ የሳምባ ምች እንደማያመጣ የሚገልጹት ባለሙያው፤ በአንጻሩ የሳምባ ምች እንዲከሰት ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።
 
ይህንም በምሳሌ ሲያስረዱ፤ አንድ ሰው ቀዝቃዛ አየር ወደ ውስጥ በሚስብበት ወቅት በሰውነት ውስጥ በሚገኝ የአየር ቱቦ ላይ የሚገኙት ሲሊያ የተሰኙ ስትራክቸሮች ተግባራቸውን በአግባቡ ማከናወን ይሳናቸዋል ብለዋል። የሲሊያ ዋና ተግባርም ከአየር ጋር ወደ ውስጥ የሚገቡትን ቆሻሻ፣ ባክቴሪያ፣ ቫይረስ እና ፈንገስ በመግፋት ከሰውነት እንዲወጣ ማድረግ መሆኑን በማስገንዘብ።
 
በተጨማሪም አንድ ሰው ቀዝቃዛ አየር በሚስብበት ጊዜ የበሽታ መከላከል ሠራዊት ተግባርን እንደሚቀንሰው ነው ያስረዱት።
 
አክለውም በሳይንስ ብርድ መመታት የሚባል ህመም እንደሌለ በመግለጽ፤ ሰዎች በቀዝቃዛ አየር ውስጥ ሲቆዩ በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው ስለሚቀንስ ምናልባት ሳምባ ምችን ጨምሮ ለተለያዩ ህመሞች ሊጋለጡ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አብራርተዋል።
 
· የሳምባ ህመም እና የሳምባ ምች አንድ ነው ወይስ ይለያያል?
 
በሕክምና ቋንቋው ‘ኒሞኒያ’ የሚባለው በአማርኛ የሳምባ ምች መሆኑን በመግለጽ፤ ህመሙም ሳምባ ላይ በሚከሰት ኢንፌክሽን የሚፈጠር መሆኑን ነው ያስረዱት ዶክተር እስማኤል።
 
በተለየ በሽታ አምጭ ተኅዋስያን ምክንያት የሚከሰተው የሳምባ ህመም ‘ቲበርክሎሲስ’ ወይም የሳምባ ቲቢ (የሳምባ ነቀርሳ) እንደሚባል በመግለጽ በቀላሉ መፈወስ ስለማይቻል መድኃኒቱም ረዘም ላለ ጊዜ (እንደሁኔታው እስከ 6 ወርና ከዚያ በላይ) እንደሚወሰድና ከሳምባ ምች ጋር የማይገናኝ መሆኑን ተናግረዋል።
 
· የተባባሰ ጉንፋን እና የሳምባ ምች
 
ጉንፋን በቫይረስ ኢንፌክሽን የሚከሰት እንደመሆኑ፤ አንድ ሰው በቫይረስ ኢንፌክሽን ሲጠቃ ባክቴሪያዎች ይህን ሁኔታ ተጠቅመው ኢንፌክሽን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል የሕክምና ባለሙያው። ስለዚህ ቫይረሱ ሳምባ አካባቢ ያሉ የአየር ቱቦዎችን ስለሚያጠቃ ለባክቴሪያ መራባት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ይላሉ።
 
በዚህም መሠረት አንድ ሰው ጉንፋን ይዞትና እየቆየበት ሲሄድ፤ በተደራቢነት የባክቴሪያ ኒሞኒያ (የሳምባ ምች) ሊያጠቃው እንደሚችል አስረድተዋል።
 
· ለሳምባ ምች በይበልጥ እነማን ተጋላጭ ናቸው?
 
የሳምባ ምች ተጋላጭነት በዕድሜ ክልል ተወስኖ ሊታይ እንደሚችል ገልጸው፤ በዚህም መሠረት ከ65 ዓመት በላይ እና ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
 
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ህመሞች ያሉባቸው (የስኳር፣ የኤች አይ ቪ እና የካንሰር ታካሚዎች እንዲሁም በሽታ የመከላከል ዐቅም ለመቀነስ መድኃኒት የሚወስዱ) ከሌላው ሕብረተሰብ አንጻር ለሳምባ ምች ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
 
· የአሳሳቢነት ሁኔታ
 
የሳምባ ምች አሳሳቢነት ከፍተኛ መሆኑን የሕክምና ባለሙያው አሃዛዊ ማስረጃዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ በተለይም በገዳይነታቸው ደረጃ ከሚጠቀሱት አምስት በሽታዎች መካከል እንደሚመደብ አንስተዋል።
 
የሳምባ ምች በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሊከሰት የሚችል መሆኑን በመግለጽ፤ የጥናቶች ውጤቶች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የማኅበረሰብ ክፍል በሳምባ ምች ሊጠቃ ይችላል ብለዋል።
 
በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚደርሰው የዓለም ሕዝብ በሳምባ ምች የመጠቃት ዕድል እንዳለው አመላክተዋል።
 
የሞት ምክንያት ከመሆን አንጻርም ይላሉ ዶክተር እስማኤል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ሞት ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ምክንያቱ የሳምባ ምች መሆኑን ይናገራሉ። በተመሳሳይ በዓለም ላይ ከ18 እስከ 20 በመቶ ያህሉ የሞት ምክንያት የሳምባ ምች ነው ይላሉ።
 
· የሳምባ ምችን መከላከል ይቻላል?
 
ዶክተር እስማኤል እንዳረጋገጡት፤ የሳምባ ምችን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። ዋናው መከላከያውም ክትባት መሆኑን በመግለጽ።
 
በተለይም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የሳምባ ምች ክትባት በመከተብ ለበሽታው እንዳይጋለጡ መካለከል ይቻላል ብለዋል።

ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው፣ ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው እንዲሁም ቋሚ የሳንባ ህመም ያለባቸው ክትባቱን በመውሰድ ኒሞኒያን መከላከል እንደሚችሉ አስረድተዋል።
 
በተጨማሪም በምግብ እጥረት ሊከሰት የሚችልን የሳምባ ምች የአመጋገብ ሥነ-ሥርዓትን በማስተካከል አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አመላክተዋል።
 
በትንፋሽ ስለሚተላለፍ በሳምባ ምች ከተጠቃ ሰው ጋር ንክኪ ባለማድረግ፤ ማስክ በመጠቀም፣ በተፋፈገ (በጣም በተጨናነቅ) ሁኔታ ውስጥ ባለመሆን ተስፋፊነቱን መከላከል እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
 
· ሕክምና
 
የሳምባ ምች እንደሚታከም ያስገነዘቡት ዶክተር እስማኤል፤ እንደ በሽታው ደረጃ የሚወሰን ሆኖ ሕክምናው ከተመላላሽ በሆስፒታል ተኝቶ እስከ መታከም ሊደርስ እንደሚችል አስረድተዋል።
 
በዚህም መሠረት የህመሙ ደረጃ ከፍተኛ ካልሆነ በተመላላሽ፤ ከፍተኛ ከሆነ ከ5 እስከ 7 አንዳንዴም ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት እንደሚታከም አክለዋል።
 
ምልክቶች እንደታዩ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ አዋጭና ቶሎ ለመፈወስ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።
 
#Ethiopian_News_Agency
 
#ኢዜአ
 
#የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት
 
#የጤና_ነገር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም