የጤና ነገር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
የኪንታሮት ህመም እንዴት ይከሰታል? እንዳይከሰት መከላከል የሚቻልበት ብልኀት አለ? ከተከሰተ በኋላስ የሚድንበት ዕድል ይኖራል?
· ኪንታሮት እንዴት ይከሰታል?
አጠቃላይ የቀዶ ጥገና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ቤተልሔም አበራ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኙ በጤናማ መንገድ ፊንጢጣ እንዲዘጋ (‘ኩሽን’ እንዲሆን) የሚያደርጉ ደም ሥሮች በተለያየ ምክንያት ሲያብጡ ኪንታሮት (ሄሞሮይድ) ተከሰተ እንደሚባል አስረድተዋል።
· የኪንታሮት በሽታ መንስዔ ይታወቃል?
እንደ ሕክምና ባለሙያዋ ገለጻ ለኪንታሮት በሽታ መንስዔ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል፤ የሰገራ ድርቀት በዋናነት ይነሳል።
በተጨማሪም ይላሉ፤ በተለይም ሴቶች ላይ በእርግዝና ወቅት የጽንሱ መጠን (ክብደት) እየጨመረ በሚሄድበት ጊዜ ወደ መቀመጫ በሚያደርገው ጫና ምክንያት በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኙ የደም ሥሮች እንዲያብጡ በማድረግ ለኪንታሮት መከሰት መንስዔ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ በስፋት ለሚከሰት የኪንታሮት በሽታ በመንስዔነት የሚነሳው ከመጠን ያለፈ ውፍረት መጨመር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም ውፍረት ወደ መቀመጫ ጫና በማሳደር በፊንጢጣ ውስጥ ያሉ የደም ሥሮች እንዲያብጡ በማድረግ ኪንታሮት እንዲከሰት ያደርጋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል እንደ ሥራ ባሕርያቸው ለረጂም ሠዓታት የሚቀመጡ ሰዎች ስለማይንቀሳቀሱና ይህን ተከትሎም ለድርቀት ስለሚጋለጡ ለኪንታሮት በሽታ ይዳረጋሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከአመጋገብ ዘይቤ ጋር በተያያዘም፤ በቂ ውኃ አለመጠጣት እና በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን አለማዘውተር ለድርቀት ስለሚዳርግ የኪንታሮት በሽታ እንዲከሰት ያደርጋል ብለዋል።
· የኪንታሮት በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ያለው ለምንድን ነው?
ኪንታሮት የተለመዱ (‘ኮመን’) ከሚባሉ የቀዶ ሕክምና በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቤተልሔም፤ በትክክል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መረጃ ለጊዜው መግለጽ ባይቻልም በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 25 በመቶ ያህሉ ሕዝብ የኪንታሮት ተጠቂ እንደሆነ ጠቁመዋል።
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ የኪንታሮት በሽታ ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር እንደሚለያይ መሆኑን አስገንዝበው፤ ለዚህም ምክንያቱ ከውፍረት እና ለድርቀት ከሚያጋልጡ አመጋገቦች መዘውተር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው ይላሉ። ለምሳሌ፡- በጣም ወፍራም ሰዎች በሚበዙባቸው እና ለድርቀት አጋላጭ ምግቦች በሚዘወተሩባቸው አካባቢዎች የኪንታሮት ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው ይላሉ።
የኪንታሮት በሽታ እየጨመረ (እየተስፋፋ) የሚሄድበት ምክንያትም ከአኗኗር ዘይቤ ጋር እንደሚያያዝ ገልጸው፤ ለምሳሌ አብዛኛውን ጊዜ ቁጭ ብሎ (ተቀምጦ) ማሳለፍ ለኪንታሮት አጋላጭ መንስዔ ነው ብለዋል። በተለይም ቢሮ አካባቢ የሚሠሩ ሰዎች ለበርካታ ሠዓታት ስለሚቀመጡ፣ ሥራ ሲበዛባቸውም ወደ መጸዳጃ ቤት መሄድ ባለባቸው ሠዓት ባለመሄድ (የሚሄዱበትን ጊዜ ስለሚያራዝሙ፣ ቆይ ይችን ልጨርስ…ትንሽ…የተወሰነ ደቂቃ እያሉ ማራዘም) ሰገራን ለድርቀት ያጋልጣል፤ ይህም የደም ሥሮች እንዲያብጡና ከፊንጢጣ ውጭ እንዲወጡ በማድረግ ለኪንታሮት መከሰት ያጋልጣል ብለዋል።
· የኪንታሮት በሽታ ምልክቶች
በፊንጢጣ ላይ ዕብጠት መኖር፣ መድማት፣ ማሳከክ እና የህመም ስሜት መኖር ከምልክቶቹ መካከል መሆናቸውን ዶክተር ቤተልሔም ያብራራሉ።
የኪንታሮት በሽታ የውስጠኛው እና የውጨኛው ተብሎ እንደሚከፈል በመግለጽ፤ የበሽታው ደረጃም ከአንድ እስከ አራተኛ እንደሚመደብ ያስረዳሉ።
ይህን ሲያብራሩም፤ በውስጠኛው የኪንታሮት በሽታ ባብዛኛው ህመም አይኖርም፣ የፊንጢጣ ደም ሥሮች ዕብጠትና መድማት ይኖራል፤ በውጨኛው የኪንታሮት በሽታ ግን የህመም ስሜት ይኖራል ይላሉ።
· የኪንታሮት በሽታ ደረጃዎች
ደረጃዎቹን በተመለከተ ሲያስረዱ፤ ምልክቶቹን እንዳስተዋሉ ቶሎ ወደ ሕክምና ባለመሄድ ከአንደኛ ወደ ሁለተኛ ከዚያም ወደ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ እየተባባሰ እንደሚሸጋገር ገልጸዋል።
ስለዚህ ሰዎች ምልክቶቹን እንዳዩ ቢታከሙ ደረጃው ከፍ ሳይል በሽታውን የመግታት ዕድል ይኖራቸዋል ነው የሚሉት።
የመጀመሪያ ደረጃ የኪንታሮት በሽታ፤ በዚህ ወቅት የኪንታሮት ህሙማን እንኳን የዕብጠቱን መኖር ባብዛኛው በእጃቸውም ነክተው እንደማያውቁት እና የመድማት ምልክት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
ሁለተኛ ደረጃ የኪንታሮት በሽታ፤ በዚህኛው ደረጃ ደግሞ ህሙማኑ በሚጸዳዱበት ወቅት ዕባጩ ወደ ውጭ እንደሚወጣ እና ሲጨርሱ በራሱ ጊዜ ዕባጩ ወደ ቦታው እንደሚመለስ አስገንዝበዋል።
ሦስተኛ ደረጃ የኪንታሮት በሽታ፤ በሽታው ያለባቸው ሰዎች በሚጸዳዱበት ወቅት ወደ ውጭ የሚወጣውን ዕባጭ በእጃቸው ወደ ውስጥ ካላስገቡት በራሱ ጊዜ የማይመለስበት ደረጃ መሆኑን ይገልጻሉ።
አራተኛ ደረጃ የኪንታሮት በሽታ፤ ይህ ደረጃ ዕባጩ ከፊንጢጣ ውጭ ይወጣና ተገፍቶም ወደ ውስጥ መግባት የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ስለዚህ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለ የኪንታሮት በሽታ፤ ያለ ቀዶ ሕክምና ሰዎች እቤታቸው እንዲያደርጉ የሚመከሩትን ሁኔታዎች በአግባቡ ካደረጉ ወደ ቀጣዩ ደረጃ እንዳይሸጋገር ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
· በወቅቱ ካልታከመ
በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኪንታሮትን ከላይ በተገለጹ የኑሮ እና አመጋገብ ዘይቤዎች ማስተካከል እንደሚቻል (ወደ ቀጣዮቹ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ሳይሸጋገር ባለበት እንዲቆይ) ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ወደ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ከደረሰ ግን የቀዶ ሕክምና እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ይህ ደግሞ ጥቅምም የጎንዮሽ ጉዳትም እንዳለው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ካልታከመ እና ወደ መጨረሻዎቹ ደረጃዎች ከደረሰ ከፍተኛ የደም መፍሰስ እንደሚኖረውና ይህም ከሰው ደም እስከመለገስ ሊያደርስ እንደሚችል ይገልጻሉ።
ወደ ውጭ ወጥተው በሚቀሩ የፊንጢጣ ደም ሥሮች ውስጥ የደም መርጋት ሊያጋጥም እንደሚችልና ይህም ከፍተኛ ህመም እንደሚያመጣ ተናግረዋል። በዚህም ድንገተኛ ሕክምና የመፈለግ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው ያመላከቱት።
· የኪንታሮት በሽታ ሙሉ በሙሉ ይድናል ወይስ አይድንም?
በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ የኪንታሮት በሽታ በጊዜውና በአግባቡ ከታከመ ሙሉ በሙሉ እንደሚድን ዶክተር ቤተልሔም አረጋግጠዋል።
በተለይም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለ የኪንታሮት በሽታን ሰዎች እቤታቸው በሚያደርጉት ትሪትመንት (የአኗኗርና አመጋገብ ዘይቤያቸውን በማስተካከል) ሊያድኑት እንደሚችሉም አመላክተዋል።
በተጨማሪም ወደ ሕክምና ተቋም ቢሄዱ፤ የሰገራ ማለስለሻ፣ ፊንጢጣ ላይ የሚቀባ የህመምና ዕብጠት መቀነሻ መድኃኒት እንደሚሰጥ በመግለጽ ይህ ከተስተካከለ የአኗኗር ዘይቤያቸው ብሎም በብዛት ውኃ ከመጠጣት ጋር ሲሠናሰል በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኪንታሮት የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህንን አልፎ ወደ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስ እንኳን የተለያዩ የቀዶ ሕክምና አማራጮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በዚህም መሠረት እንደ ኪንታሮቱ መጠን ‘ረበርባንድ’ (ዕባጩን ዙሪያውን በመቋጠር በጊዜ ሂደት ደርቆ እንዲረግፍ የማድረግ ሕክምና) እና ኪንታሮቱን (የደም ሥሮቹን ዕባጭ) በቀጥታ በቀዶ ሕክምና በማውጣት ማከም ይቻላል፤ መዳንም ይቻላል ብለዋል።
· ኪንታሮት እና ባሕላዊ ሕክምና
ከላይ እንደገለጽነው (የኑሮ ዘይቤን ማስተካከል፣ ውኃ በብዛት መጠጣት፣ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን ማዘውተር፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ) ከዚያም ዘመናዊ ሕክምና መከታተል ተገቢ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዋ መክረዋል።
በአንጻሩ በባሕል (በልማድ) ፊንጢጣ ውስጥ የሆነ ነገር መቅበር፣ ኪንታሮትን በግለት መተኮስ ለካፋ ችግር ሊያጋልጥ ስለሚችል ይህን ከማድረግ መቆጠብ ይመከራል ብለዋል። ምክንያቱም ለፊንጢጣ መጥበብ (በሚጸዳዱበት ጊዜ ለመሰንጠቅና መድማት) ብሎም ለመሰል የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊዳርግ እንደሚችል አስረድተዋል።
ኪንታሮት በአግባቡ በቀዶ ሕክምና ካልወጣ በባሕል (ልማድ) መነካካቱ ለባክቴሪያ እንደሚያጋልጥ፤ ባክቴሪያው ደግሞ ከፊንጢጣ አልፎ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ወደ ታፋና አካባቢው) የሚዛመት መግል የያዘ ከፍተኛ ኢንፌክሽን ያጋልጣል ብለዋል። በዚህ ጊዜ ወደ ሕክምና ሲመጡ ሕክምናውን በጣም ከባድ (ውስብስብና አስቸጋሪ) ያደርገዋል ነው ያሉት።
· የፊንጢጣ ካንሰርና የኪንታሮት በሽታ
ቀደም ብለን እንዳነሳነው የኪንታሮት በሽታ ምልክቶች፤ ማሳከክ፣ ዕባጭ፣ መድማት እና ህመም ናቸው ያሉት ዶክተር ቤተልሔም፤ የፊንጢጣ ካንሰርም ተመሳሳይ ምልክቶች ይኖሩታል ይላሉ።
ስለዚህ ማንኛውም ሰው በፊንጢጣ በኩል ደም ሲመለከት ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም እንዲሄድ መክረዋል። ምክንያቱም ይላሉ፤ በፊንጢጣ በኩል ደም የሚታየው አንድም በኪንታሮት በሽታ እንዲሁም በአንጀት ቁስለት፣ በፊንጢጣ ካንሰር፣ በጨጓራ ቁስለት እና በትልቁ አንጀት ካንሰር ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ነው።
ከመድማት በተጨማሪ የፊንጢጣ ቁስለት በስፋት ከታየ ካንሰር ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል። ቁስለቱ ፊንጢጣ ውስጥ ስለሚሆን በእጅ መንካትና ማወቅ የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
· ምክረ ሐሳብ
ለኪንታሮት በሽታ ላለመጋለጥ ወይም ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ወደ ቀጣዮቹ ደረጃዎች እንዳይሸጋገር መንስዔዎቹን መቀልበስ ተገቢ መሆኑን በአጽንዖት አንስተዋል። በዚህም መሠረት ድርቀት እንዳይኖር ማድረግ ቀዳሚው መፍትሔ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለዚህም በቂ ውኃ መጠጣት፣ ከ25 እስከ 30 ግራም ፋይበር በየቀኑ መውሰድ (በደንብ ፋይበር ያላቸው ምግቦችን መመገብ ለምሳሌ፡- ጎመን፣ ቆስጣ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ አፕል፣ ባቄላ፣ ገብስ፣ አጃ፣ ስንዴ) ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም ድርቀትን ለመከላከል ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ፤ በሥራ ባሕርያቸው ቢሮ ውስጥም ሆነ ሌላ ቦታ መቀመጥ የሚያበዙ ሰዎች በመሐል በመነሳት መንቀሳቀስ እንዲሁም ከሥራ ሲወጡ በእግር መሄድ (ዎክ ማድረግ) እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ለአንጀት እንቅስቃሴ ዕገዛ በማድረግ ድርቀት እንዳይኖር ይጠቅማቸዋል ብለዋል።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ሰዎችም ክብደታቸውን እንዲቀንሱ መክረው፤ ይህ ሲሆን ከፊንጢጣ ውጭ የነበረው የደም ሥር ዕብጠት (የኪንታሮት በሽታ) ወደ ነባር ቦታው እንዲመለስ ወይም ባለበት እንዲቆይ (በይበልጥ ተገፍቶ እንዳይወጣ) ይረዳል ይላሉ።
ከልማዳዊ ሕክምና በመራቅ ዘመናዊ ሕክምናን ቀዳሚ ምርጫ ለማድረግ በተለይም ቀድሞ መከላከል የሚቻልበትን ብልኀት ለማዳበር ስለ ኪንታሮት በሽታ በስፋት ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ ነው ይላሉ።
በፊንጢጣ በኩል ደም ሲታይ ሁሌም ኪንታሮት ላይሆን እንደሚችልና ካንሰር ሊሆን እንደሚችልም በመገንዘብ ቶሎ ወደ ሕክምና በመሄድ ወደ ሌሎች ደረጃዎች ሳይሸጋገር በማከም እንዲድን ማድረግ ተገቢ መሆኑን መክረዋል።