እየተስፋፋ ያለው የጉበት ስብን (ቅባት) እንዴት መከላከል ይቻላል? - ኢዜአ አማርኛ
እየተስፋፋ ያለው የጉበት ስብን (ቅባት) እንዴት መከላከል ይቻላል?
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
በዝምታ እየተስፋፋ ያለው የጉበት ስብን (ቅባት) እንዴት መከላከል ይቻላል?
የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት፤ የጨጓራ፣ አንጀትና ጉበት ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ሚፍታህ ደሊል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የጉበት ጤናን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል፣ ለጉበት ጤና መታወክ ስለሚያጋልጡ ጉዳዮች፣ ስለጉበት ስብ (ቅባት) እንዲሁም ሕክምናው ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
· በሰው ልጅ ሕይዎት (ሠርካዊ እንቅስቃሴ) ውስጥ የጉበት ሚና ምንድን ነው?
ዶክተር ሚፍታህ እንደገለጹት፤ ጉበት በሰውነታችን ውስጥ ኪሚገኙ ትላልቅ የውስጥ አካል ክፍሎች (ኦርጋኖች) አንዱ ነው።
ከ1 ሺህ በላይ ተግባራትን የሚያከናውን ትልቁ እና ባተሌ የሆነ የአካል ክፍል መሆኑንም አስረድተዋል።
ካንሰር እንዴት ይከሰታል?
· ለጉበት ህመም አጋላጭ ምክንያቶች ይታወቃሉ?
ለጉበት ህመም አጋላጭ ከሆኑ መንስዔዎች መካከል፤ ቫይረሶች (ሄፓታይትስ ቢ፣ ሄፓታይትስ ሲ) እንዲሁም አልኮል (ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል መጠጣት) መሆናቸውን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በስፋት የሚስተዋለው አጋላጭ መንስዔ የጉበት ስብ መጨመር መሆኑንም በአጽንዖት ገልጸዋል።
በእኛ ሀገር ደረጃ ከሚከሰቱ የጉበት ህመሞች 50 በመቶው በሄፓታይትስ ቢ ምክንያት የሚከሰት ነው ይላሉ ዶክተር ሚፍታህ።
ከ15 እስከ 20 በመቶ ያህሉ የጉበት ህመም የሚከሰተው ደግሞ በአልኮል ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዱት።
እንዲሁም በሄፓታይትስ ሲ ምክንያት የሚከሰተው የጉበት ህመም ከላይ ከተገለጹት ቀጥሎ በሦስተኛነት እንደሚቀመጥም አመላክተዋል።
አሁን አሁን ደግሞ ይላሉ ዶክተር ሚፍታህ፤ በሥራም ሆነ ለመዝናናት ለረጂም ሠዓታት መቀመጥን ተከትሎ የጉበት ስብ (ቅባት) በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋና ለጉበት ህመም እያጋለጠ መሆኑን አስገንዝበዋል።
· የጉበት ፋት (ስብ፣ ቅባት) ለጉበት ህመም የሚያጋልጥበት ምክንያት ምንድን ነው?
የጉበት ስብ በተለያዩ ሀገራት (በእኛም ሀገር በትላልቅ ከተሞች) በስፋት የሚከሰት ነው ያሉት ዶክተር ሚፍታህ፤ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመላክቱት ከዓለም ሕዝብ 30 በመቶው (1/3ኛው ወይም ከ2 ቢሊየን በላይ ያህሉ) የጉበት ስብ ሊኖርበት ይችላል ይላሉ።
በእርግጥ ሁሉም የጉበት ስብ ወደ ከፍተኛ የጉበት ቁስለት ይሸጋገራል ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፤ የጉበት ስብ ካለባቸው መካከል ከ10 እስከ 15 በመቶ ያህሉ ብቻ ስቡ ከመብዛቱ የተነሳ ጉበቱን ማቁሰል እንደሚጀምር አስገንዝበዋል። ይህ ቁስለት ደግሞ እየዳነ እንደገና እያገረሸ ጠባሳ እየፈጠረ ይሄድና ጉበት ሥራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ የጉበት መድከም ይከሰታል፤ ሰዎችም ጉዳት ይደርስባቸዋል ይላሉ።
የጉበት ስብ መንስዔም፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ (መቀመጥን ማዘውተር)፣ ፋስት ፉድ ማዘውተር (የተጠበሱ ምግቦች፣ በርገር፣ ችብስ፣ ዘይት የበዛባቸው ምግቦች) እንዲሁም ከፍተኛ ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጠጦች፣ አልኮል መሆናቸውን አብራርተዋል።
· የጉበት ስብን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የጉበት ስብ ከፍ እያለ ሲሄድ በአልትራሳውንድ እንደሚታይ (ትንሽ ከሆነ አይታም) የገለጹት ዶክተር ሚፍታህ፤ እስካሁን ክትባት እንደሌለው አረጋግጠዋል።
ይህ ኬዝ እንቅስቃሴ ባለማድረግ፣ ኮምፒውተርም ሆነ ቴሌቪዥን ለማየት ረጂም ሠዓት በመቀመጥና በውፍረት መጨመር የሚከሰት መሆኑን ጠቁመው፤ መከላከያ መንገዱም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ (ቢያንስ በሳምንት እስከ 150 ደቂቃ በእግር መሄድ (ዎክ ማድረግ) ወይም በቀን ለ30 ደቂቃ ዎክ ማድረግ) መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
በተጨማሪም በፋብሪካ ፕሮሰስ የተደረጉ የታሸጉ ምግቦችን አለማዘውተር፣ ከስኳር ነጻ የሚሉ የሚበሉም ሆነ የሚጠጡ ነገሮችም ቢሆኑ በቀጥታም ባይሆን በሌላ መንገድ ጣፋጭ ስለሚኖራቸው አለማዘውተር፣ የተጠበሱ እንደ ችብስ እና መሰል ያሉ ምግቦችንም አለማዘውተር እንደሚገባ መክረዋል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት እንዳይኖር ማድረግም ለጉበት ስብ ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ አስረድተዋል።
· የጉበት በሽታ ምልክቶች
እንደ ኬዙ ቢለያይም ጉበት 80 በመቶ ያህል ክፍሉ እስከሚጎዳ ምልክት ላያሳይ እንደሚችል ዶክተር ሚፍታህ ይገልጻሉ።
15 ወይም 10 በመቶ ጤናማ ክፍሉ ሲቀር (ከ85 በመቶ በላይ ክፍሉ በጣም ሲጎዳ) አንዳንድ ምልክቶች ሊያሳይ እንደሚችል ገልጸዋል። እነዚህ ምልክቶችም፤ ሆድ ላይ ውኃ መፍጠር (አሳይተስ)፣ ደም ማስመለስ መሆናቸውን እና በዚህ ወቅት የጉበት ንቅለ ተከላ ካልሆነ መፍትሔ እንደሌለው አንስተዋል።
በአንጻሩ ግን፤ ‘አኪዩት ሄፓታይትስ’ የሚባለው ወይም አንድ ቫይረስ ጉበትን ሲያጠቃ ወዲያውኑ ሕክምና ይደረግለታል ሙሉ በሙሉም ይድናል ብለዋል።በዚህ ወቅት የሚየሳየው ምልክትም የዐይን ቢጫ መሆን፣ በቀኝ ደረት ሥር የውጋት ስሜት መኖር፣ ከፍተኛ ድካም መኖር፣ የምግብ ፍላጎት አለመኖር (ምግብ አስጠላኝ ማለት)፣ ማቅለሽለሽ እንዲሁም ማስመለስ መሆናቸውን አብራርተዋል።
· የጉበት በሽታ አሳሳቢ ነው?
የጉበት በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩ ሀገራት ከ1 እስከ 10 ገዳይ (አሳሳቢ) ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል መሆኑን ዶክተር ሚፍታህ አስረድተዋል።
በእኛ ሀገር ደረጃም የጉበት ካንሰር ከ3 እስከ 4 ገዳይ ተብለው ከሚጠቀሱ በሽታዎች መካከል መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በዓለም በየዓመቱ እስከ 3 ሚሊየን ሰዎች በጉበት በሽታ እንደሚሞቱ ገልጸው፤ ይህ አኃዝ አሳሳቢነቱን ያስረዳል ብለዋል።
ምንም እንኳን ቀድሞ በሚወሰድ ክትባት (ለሄፓታይትስ ቢ) ከተከሰተ በኋላም በሚወሰድ መድኃኒት (ለሄፓታይትስ ሲ) አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም፤ የጉበት ስብ (ቅባት) ግን በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ በተለይም በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት እየተስተዋለ ያለ በመሆኑ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
· የጉበት በሽታ በተለይም በየትኞቹ የዕድሜ ክልሎች ላይ በስፋት ይከሰታል?
የጉበት በሽታው ዓይነት በስፋት የሚከሰትበትን ዕድሜ እንደሚወስን ጠቁመው፤ በዚህም መሠረት ለምሳሌ፡- ሄፓታይትስ ቢ ከ30 ዓመት በታች ባሉ ሰዎች ላይ፣ ሄፓታይትስ ሲ ከ20 እስከ 40 ዓመት (አንዳንድ ጊዜ ከ40 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይም ሊከሰት ይችላል)፣ የጉበት ስብ (ቅባት) ደግሞ ከ40 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ በስፋት እንደሚስተዋል ያስረዳሉ።
· የጉበት በሽታን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል?
ዶክተር ሚፍታህ እንዳሉት የጉበት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የቻልባቸው የተለያዩ አማራጮች አሉ።
ለምሳሌ፡- የሰውነት ክብደት (ውፍረት) ከልኩ እንዳያልፍ መቆጣጠር፣ ረጂም ሠዓት አለመቀመጥ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር፣ አልኮል አለመጠጣት (በቀን ከአንድ ቢራ በላይ መጠጣት ለጉበት ስብ ያጋልጣል)፣ ጣፋጭ ምግብና መጠጦችን መቀነስ (ጭራሽ አለመጠቀም ቢቻል)፣ ዘይት የበዛባቸውና የተጠባበሱ ምግቦችንም አለማዘውተር የሚሉትን አንስተዋል።
በተጨማሪም በእኛ ሀገር ቀዳሚው የጉበት በሽታ ሄፓታይትስ ቢ መሆኑን በመግለጽ፤ ለዚህም ከ95 በመቶ በላይ የመከላከል ዐቅም ያለው ክትባት ስላለው ሦስት ጊዜ በመከተብ አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
· የሕክምና አማራጮች አሉት?
ሄፓታይትስ ቢ ተከስቶ ጉበቱን ማቁሰል ከጀመረም የሚሰጥ ውጤታማ መድኃኒት መኖሩን አስታውቀዋል። ይህ መድኃኒት ምናልባት ዕድሜ ልክ ሊወሰድ ይችላል ነገር ግን ቁስለቱንም ሆነ ቫይረሱን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ነው ያሉት።
ሄፓተይትስ ሲ ከሆነ ደግሞ በጣም ውጤታማ የሆነ ለሦስት ወር የሚሰጥ መድኃኒት አለ ብለዋል።
ጠባሳ ከሆነ እና ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የጉበት ክፍል ከተጎዳ (ከተበላሸ) ግን በውጭ ሀገር የጉበት ንቅለ ተከላ ማድረግ አስገዳጅ ይሆናል ብለዋል።
· ምክረ ሐሳብ
ተላላፊ ካልሆኑ የጉበት በሽታዎች አንዱ እና አሁን በስፋት እየተስተዋለ ያለውን የጉበት ስብ (ቅባት) ጨምሮ የጉበት ጤናን ለመጠበቅ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በየቀኑ ማድረግን መክረዋል።
በዓመት አንድ ጊዜ የጤና ምርመራ በማድረግ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅም ቢለመድ ሲሉ ይመክራሉ።
በወቅቱ ከተደረሰብት የጉበት በሽታ መዳን እንደሚችል ገልጸው፤ በቸልተኝነት ወደ ተወሳሰበ ደረጃ ከፍ ካለ ግን እስከ ጉበት ካንሰር ሊደርስ እንደሚችልም አመላክተዋል።