ቀጥታ፡

የጤና ነገር

በዮሐንስ ደርበው

ሾተላይ ምንድነው? እንዴትስ ይከሰታል? ቀድሞ መከላከልስ ይቻላል?

ሾተላይ የሚከሰተው RH-Negative የሆነች እናት RH-Positive የሆነ ፅንስ በምታረግዝበት ወቅት የእናትየው በሽታ የመከላከል ሥርዓት የፅንሱን ደም እንደ ባዕድ ነገር በመቁጠር በሚያመነጨው ንጥረ-ነገር (Antibodies) አማካኝነት መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። 

የጽንስና ማህጸን ስፔሻሊስት ዶክተር ዳንኤል ኃብተማርያም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከወሊድ ጋር በተያያዘው አር ኤች ኔጌቲቭ (RH-) ወይም ሾተላይ እየተባለ በሚጠራው በጽንስ ላይ የሚያጋጥም ችግር ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሾተላይ ወይም አር ኤች ኔጌቲቭ (RH-) ምንድን ነው?

እንደ ዶክተር ዳንኤል ማብራሪያ፤ ሰዎች ከሚታወቁበት አራቱ የደም ዓይነቶች ምደባ (ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ) በተጨማሪ በቀይ ደም ኅዋስ ሰርፌስ ላይ በፕሮቲን መኖርና አለመኖር ይለያሉ። በዚህም መሠረት አር ኤች ፖዘቲቭ (RH+) እና አር ኤች ኔጌቲቭ (RH-) ተብለው እንደሚከፈሉ ያስረዳሉ።

በዚህ ምደባ መሠረት ከአጠቃላይ ሕዝቡ 85 በመቶው አር ኤች ፋክተር ፖዘቲቭ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ማለት በቀይ ደም ኅዋሳቸው ሰርፌስ ላይ ፕሮቲን አላቸው ማለት ነው ይላሉ።

15 በመቶው ደግሞ አር ኤች ኔጌቲቭ ወይም በቀይ የደም ኅዋሳቸው ሰርፌስ ላይ ፕሮቲን የሌላቸው ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

አክለውም አር ኤች ኔጌቲቭ ወይም ፖዘቲቭ መሆን በሽታ እንዳልሆነ በአጽንኦት ገልጸው፤ ከወላጆች የሚወረስ መሆኑን አስገንዝበዋል። ስለዚህ አንድ ልጅ ሲወለድ እንደ ወላጆቹ አር ኤች ፋክተር መሠረት አር ኤች ፖዘቲቭ ወይም አር ኤች ኔጌቲቭ ይሆናል ሲሉ ይገልጻሉ።

ይህን በምሳሌ ሲያስረዱም፤ አንዲት ሴት አር ኤች ፋክተሯ ኔጌቲቭ ሆኖ ጽንሷ ደግሞ አር ኤች ፖዘቲቭ ቢሆን ተገቢው የሕክምና ክትትል ካልተደረገ ብሎም የእናትና ልጅ ደም ንክኪ ከተፈጠረ የበሽታ መከላከል ሥርዓቷ የሚያመነጨው አንቲ ቦዲ ጽንሱን እንደ ባዕድ ነገር ስለሚቆጥረው ጉዳት (ሾተላይ) ያስከትላል ይላሉ።

የአንቲ ቦዲ ሥራ ሴቷ ለአር ኤች ፖዘቲቭ የምትጋለጥበት ሁኔታ ከተፈጠረ ጽንሱን (አር ኤች ፋክተሩ ከእሷ ተቃራኒ ሲሆን) እንደ ባዕድ ነገር ቆጥሮ ሴትዮዋን ለመከላከል በጽንሱ ላይ ጥቃት ማድረስ መሆኑንም አመላክተዋል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ለማንኛውም ጤናማ የእርግዝና ሂደት የሕክምና ክትትል ማድረግ ቀዳሚ መፍትሔ መሆኑን መክረዋል።

ከሾተላይ ጋር በተያያዘ ደግሞ በእርግዝና ወቅት የሚስትና ባልን አር ኤች ፋክተር መለየት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ተከትሎም አር ኤች ፋክተራቸው ተመሳሳይ ከሆነ ጽንሱም ከእነሱ ጋር ስለሚመሳሰል ጤናማ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በአንጻሩ ግን፤ አር ኤች ፋክተሯ ኔጌቲቭ የሆነች ሴት የባለቤቷ አር ኤች ፋክተር ፖዘቲቭ ከሆነ ወይም ለአር ኤች ፖዘቲቭ ተጋልጣ ሰውነቷ መከላከያ አምርቷል ወይስ አላመረተም የሚለው በሕክምና ምርመራ እንደሚታወቅ አስረድተዋል።

ይህ ምርመራ ሲሠራ ውጤቱ ኔጌቲቭ ከሆነ ወይም ለአር ኤች ፖዘቲቭ ተጋልጣ ሰውነቷ መከላከያ አላመረተም የሚል ከሆነ በዚህኛው እርግዝናም ለአር ኤች ፖዘቲቭ ተጋልጣ፣ የእናትና የጽንስ ደም ንክኪ ኖሮ መከላከያ እንዳታመርት የሚሰጥ ሕክምና እንዳለ አረጋግጠዋል።

ይህ ሕክምናም 28ኛ ሳምንት ላይ በመርፌ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሰጣል ብለዋል። ከወለደች በኋላ ደግሞ የተወለደው ልጅ አር ኤች ፋክተር ታይቶ እንደእናቱ ከሆነ ተጨማሪ መድኃኒት እንደማያስፈልግና ከአባቱ ጋር ከተመሳሰለ ግን (አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ) በመርፌ ተጨማሪ መድኃኒት በወለደች በ72 ሠዓት ውስጥ በመስጠት ለቀጣይ እርግዝናዎች ሰውነቷ መከላከያ እንዳያመነጭ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ከሾተላይ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ሳይንሳዊ ያልሆኑ ልማዳዊ ድርጊቶችን ኮንነው፤ ትክክለኛው መፍትሔ ያለው የሕክምና ክትትል በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም፤ በተለይም የጎንዮሽ ህመም ያለባቸው ሴቶች (የኩላሊት፣ የደም ግፊት፣ ስኳር እና ሌሎችም) ቀድመው ሐኪም አማክረው ወደ እርግዝና ቢገቡ እንደሚመከር ገልጸው፤ የቅድመ እርግዝና ክትትል ማድረግ ካልተቻለ እንኳን በእርግዝና ወቅት በአግባቡ ክትትል ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

ለመከላከያ ትልቅ ትኩረት መስጠት ችግሩ ተፈጥሮ ከመታከም የተሻለና ተመራጭ መፍትሔ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት። 

#የጤና_ነገር #ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም