ማህበራዊ
ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው - ኮሚሽኑ
May 16, 2024 110
ሀዋሳ፤ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)፦ ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሀገራዊ ምክክር ዝግጁ በማድረግ በሀገራዊ ዘላቂ ሠላም ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ተናገሩ። በሀዋሳ የኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ አዘጋጅነት በግጭት አፈታትና ሠላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ሀገራዊ የምርምር ጉባኤ እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በጉባኤው ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ በአሁን ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሠላምና ምክክር ዝግጁ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው። በተለይ ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች በአመቻችነትና በበጎ ፍቃደኝነት እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች አዎንታዊ የሰላም ግንባታን ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅና በማሰራጨት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም አመልክተዋል። ኮሚሽኑ በራሱ በኩል ለሚያካሂዳቸው ጥናቶች ዩኒቨርሲቲዎች አጥኚ ምሁራንን በማቅረብም የጎላ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የምርምር ጉባኤዎች ዘላቂ ሠላም ለማስፈንና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት መደላድል በመፍጠር የኮሚሽኑን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንደሚረዱም ገልጸዋል።   የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ጂሎ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የግጭት አፈታት እና የሠላም ግንባታ ፅንሰ ሀሳቦች የዩኒቨርሲቲው አሁናዊ የምርምር ሥራዎች የትኩረት መስኮች ናቸው። ዩኒቨርሲቲው በራሱ አቅም ከሚያካሂዳቸው ምርምሮች ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ተቋማትና ሌሎች አጋሮች ጋር ውል ገብቶ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።   በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደብረወርቅ ደበበ፤ የምርምር ጉባኤው ዓላማ እንደ ሀገር ዘላቂ ሠላም ማምጣት የሚቻለበትን መንገድ የሚያመላክቱ ጥናቶች በውይይት ዳብረው የፖለሲ አካል እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያበረክተው አተዋዖ የጎላ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ደብረወርቅ፤ "ከኮሚሽኑ ጋር በምርምር ሥራዎችና ሌሎች ተግባራት ጋር ተናበን እየሰራን ነው" ብለዋል። ኮሚሽኑ የያዛቸውን ሀገራዊ ግቦች ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ከ46 የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት ስምምነት መፈራረሙ ተመላክቷል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የመንግስት አካላትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
በሲዳማ ክልል የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ
May 16, 2024 91
ሀዋሳ፤ ግንቦት 8 /2016 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል እየተደረገ ባለው ሁሉ አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድበው የተለያዩ የልማት ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተጀመረው የምክክር መድረክ ላይ ተገልጿል። “ሲቪክ ማህበራት በዴሞክራሲ ባህል ግንባታና በህብረተሰብ እድገት ላይ ያላቸው ሚና” በሚል ሃሳብ እየተካሄደ ባለው በዚሁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ ላይ የሲዳማ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሉ እንዳሉት ፤ በክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት እየተካሄዱ ይገኛሉ። የክልሉን መንግስት የልማት ተግባራት በመደገፍ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ሊያጠናክሩት ይገባል ብለዋል። ድርጅቶቹና ማህበራቱ በክልሉ በተለያዩ የልማት ተግባራት ተሳትፎ እያደረጉና ውጤታማ ስራ እየከናወኑ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አብርሃም ፤ ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበው ስራቸው ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። የሲዳማ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት ተወካይ አቶ ማስረሻ ክብረት በበኩላቸው፤ በክልሉ የተለያዩ 79 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድበው ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት በንጽህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ ስራዎች ማከናወናቸውን አስታውሰዋል። በተለይ ቅንጅትን ለማጎልበት የተጀመሩ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አብራርተዋል።    
የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለቅድመ ወሊድ ክትትልና ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል
May 16, 2024 93
አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)-የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የቅድመ ወሊድ ክትትልን ለማጠናከርና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትኩረት መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ። የጤና ሚኒስትር ያዘጋጀውና የእናቶች፣ የህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ጤና አጠባበቅ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን የሚገመግም መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በተለይ የቅድመ ወሊድ ክትትልን ለማስፋትና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። ነፍሰጡር እናት በጤና ተቋም የምታደርገው የእርግዝና ክትትል ለእናትየውም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአሁኑ ወቅት ለክትትል ወደጤና ተቋም የሚመጡ እናቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ገልጸዋል። አንዲት እናት መፀነሷን ካወቀችበት ጊዜ አንስቶ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ክትትል ማድረጓ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል። የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ጉዳት ለመቀነስ ከሚከናወኑ የጤና ልማት ሥራዎች መካከል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ አንዱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ናቸው። በክልሎች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የተሰራው ሥራ አበረታች ቢሆንም አፈጻጸሙ ወጥ እንዳልሆነ ነው የገለጹት። በቀጣይ በክልሎች ወጥ የአሰራር ስርአት በመዘርጋት በገጠርም ሆነ በከተማ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፤ በክልሉ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፣ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም በቀድሞው የደቡብ ክልል ከ100 ሺህ ወላድ እናቶች 871 የሚሆኑት በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር አስታውሰዋል። ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የሞት ምጣኔው ወደ 267 ዝቅ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረገችው በሚኒስትሩ የስነ-ተዋልዶ፣ የጨቅላ ህፃናት እና የህፃናት በጎ ፍቃደኛ አምባሳደር አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ እንዳለቸው፤ መንግስት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።   እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 በኢትዮጵያ ከተወለዱ 1 ሺህ ጨቅላ ህፃናት 33 የሚሆኑት ይሞቱ እንደነበር አስታውሳ፣ በ2023 የሚሞቱ ህጻናት ቁጥርን ወደ 26 ዝቅ ማለቱን ሪፖርቶች እንደሚያሳዩ ገልጻለች። ይህም ባለፉት ዓመታት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተተገበሩ የጤና ፖሊሲዎች ውጤታማ ስለመሆናቸው ማሳያ መሆኑን አርቲስት መቅደስ ገልጻ፣ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብላለች። በሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተጠሪ ተቋማት፣ የባለድርሻ አካላት እንዲሁም የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።  
ለንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ትግበራ መሳካት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ
May 16, 2024 86
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦የፍትሕ ሚኒስቴር የንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ትግበራ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠየቀ። የንግድና ሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፤ የንግድ ሥራ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ያህል በአግባቡ ካልተመራ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ገልፀዋል።   በመሆኑም በንግድ ሥራዎች ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሰብአዊ መብቶች አንጻር የተቃኙ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 የተባበሩት መንግሥታት 3ኛው ሁሉን-አቀፍ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ግምገማ ላይ ብሔራዊ ሪፖርት ማቅረቧን ጠቅሰዋል። በዚህም ከቢዝነስ ነክ ጎጂ የሰብዓዊ መብት ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዲቻል በቢዝነስና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር እንድታዘጋጅ ምክረ-ሃሳብ ቀርቦላት እንደነበር አስታውሰዋል። ለዚህም በዛሬው እለት ከንግድ ጋር የተያያዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል ያለመ ብሔራዊ የድርጊት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል። የድርጊት መርሃ-ግብሩ መዘጋጀቱ ለንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ጋር በሽርክና የሚከናወኑ ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ለድርጊት መርሃ-ግብሩ ስኬት የበርካታ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት የሰጠ የንግድና የልማት አሠራርን ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።   ለዚህም የመንግሥት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም ቅንጅታዊ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 መንግሥታት በንግድ አውድ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ የቢዝነስና የሰብዓዊ መብቶች መመሪያ መርሆዎችን ማጽደቁ ይታወቃል።  
በትምባሆ ጭስ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
May 16, 2024 75
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ በትምባሆ ጭስ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር ተናገሩ። የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከተማዋን ከትምባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ አካሂዷል። ንቅናቄው የተጀመረው "ህጻናትን ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት እንከላከል" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ነው። በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ እንዳሉት በከተማዋ የተጀመረው ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ለዜጎች ጤና ቅድሚያ መስጠት ይገባል። ለዜጎች ጤና ጠንቅ የሆኑ እንደ ትምባሆ ጭስ ያሉ የጤና ስርዓትን የሚያዛቡ እና አካባቢን የሚበክሉ ተግባራትን ችላ ማለት እንደማይገባ ጠቁመዋል። መንግስት ውብና ጽዱ ከተማ ለመፍጠር እያደረገ ላለው ጥረት የከተማዋ ነዋሪ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሙሉ እመቤት ታደሰ በበኩላቸው፥ ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ ትምባሆ እንዳይጨስ የግንዛቤ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።   የትምባሆ ጭስን መጠቀም በሰው ልጆች ላይ አካላዊ፣ አዕምሯዊና ስነ-ል ቦናዊ ጉዳት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አንስተዋል። በመሆኑም ሁሉም ህግን በማክበር በጋራ መከላከል እንዳለበት ጠይቀዋል። ለ22 ዓመታት በትምባሆ ማጨስ ሱስ ቆይተው አሁን ከሱስ የተላቀቁት አቶ ዮናታን ሊሬ ትምባሆ ለሞት የሚዳርግ ጎጂ ነገር ነው ብለዋል።   በድርጊቱ ቢገፉበት ኖሮ ህይወታቸውን ሊያሳጣቸው እንደሚችል ጠቅሰው፥ በራሳቸው ቁርጠኝነት ከሱስ ነጻ እንደወጡ እና ጤናማ ህይወትን መምራት እንደጀመሩ አክለዋል። በመሆኑም ሌሎች ትምባሆ ማጨስን የሚያዘወትሩ ግለሰቦች በጤናቸው እና በህይወታቸው ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ድርጊቱን ሊያቆሙ እንደሚገባ መክረዋል። የዓለም "ትምባሆ የማይጨስበት ቀን" በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ በዓለም ለ36ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምባሆ ማጨስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
ማሕበራዊ ሚዲያን የህዝብ አብሮነትና የመቻቻል እሴትን ይበልጥ ለማጎልበት መጠቀም ይገባል -ዶክተር ነገሪ ሌንጮ
May 16, 2024 92
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ማሕበራዊ ሚዲያን የህዝብ አብሮነትና የመቻቻል እሴትን ይበልጥ ለማጎልበት መጠቀም እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ። ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ይህን የገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ "ማህበራዊ ሚዲያን ለማህበራዊ ቁርኝት" በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።   ዶክተር ነገሪ ማህበራዊ ሚዲያ እንደ አጠቃቀም ሁኔታው ሀገርንና ሕዝብን ለመጥቀም ሆነ ሊጎዳ የሚችል ነው ይላሉ። የዲጅታል ማዕቀፉን ለበጎ ዓላማ ከተጠቀምነው ህዝብንና ሀገርን ወደተሻለ ዕድገት ለመውሰድ ትልቅ መሳሪያ መሆኑንም ገልጸዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ማሰራጫና ሌሎችም የአጠቃቀም ችግሮች ያሉበት ነው ያሉት ዶክተር ነገሪ፥ ይህንን ከወዲሁ ማረም ካልተቻለ በህዝብና በሀገር ላይ ትልቅ አደጋ ይደቅናል ብለዋል። በመሆኑም ማህበራዊ ሚዲያን ለህዝብና ሀገር አንድነት፣ የመቻቻልና መከባበር እሴትን ለማጎልበት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል። እያንዳንዱ ዜጋ የሚሰራጩ መረጃዎችን በመመርመር ለትክክለኛ እና ጠቃሚዎቹ ብቻ ትኩረት መስጠት አለበት ነው ያሉት። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዘለቀ ተሾመ፤ በተለይ በአንዳንድ አካላት የሚታየው ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና የጥላቻ ንግግር ሀገርን እና ህዝብን እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል። ለሀገርና ለትውልድ ሰላም የጥላቻ ንግግርን መከላከል፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤን ማስፋት እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ረገድ ምሁራን በጎ ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል። ከዚህ አኳያ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ማህበራዊ ሚዲያን ለዕኩይ ተግባር የሚያውሉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል። በመድረኩ ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ከማህበራዊ ትስስር አንጻር ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡  
የኦሮሚያ ልማት ማህበር ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
May 16, 2024 109
ሐረር፣ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)፡- የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ልማት ማህበር ገለጸ። ማህበሩ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በ160 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡትን ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና ሌሎች ያከናወናቸውን የድጋፍ ስራዎች አስረክቧል።   በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ በወቅቱ እንደገለጹት ማህበሩ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አቶ ደጀኔ እንዳሉት ማህበሩ ባለፉት ዓመታት በምስራቅ ሐረርጌ ዞን አራት ወረዳዎች 18 ብሎኮችና 72 የመማሪያ ክፍሎችን መልሶ መገንባቱንና የትምህርት ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል። በዚህም 18 ሺህ 600 የሚደርሱ ተማሪዎች አስፈላጊው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ መደረጉን ተናግረዋል። በተለይም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙና የትምህርት መቋረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል፤ የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብርም እንዲከናወን እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በወረዳዎቹ ለሚገኙ 1ሺህ 560 የተማሪ ወላጅ እናቶችም 2ሺህ 60 የእርባታ ፍየሎችን በድጋፍ መልክ በመስጠት እራሳቸውን እንዲደጉሙ እና የቤተሰብ ብልጽግናን እንዲያረጋግጡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዞኑ ቀርሳ ወረዳ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመስኖ ግድብ ግንባታ ስራዎችን እያከናወነና የግንባታ ስራውም በመፋጠን ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ማህበሩ የሚያገኘውን መልካም ተሞክሮ በማስፋት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ስራዎች ዘርፍ እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ለጋሽ ድርጅቶች በሚያደርጉት ድጋፍና ማህበሩ በገንዘብና በቁሳቁስ ባደረጉት 160 ሚሊዮን ብር የልማት ፕሮጀክት ስራዎቹን ማከናወኑን የተናገሩት ደግሞ በልማት ማህበሩ የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ናቸው። ማህበሩ በዞኑ ባከናወናቸው የተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ የህዝብ ተሳትፎን ከማነቃቃቱ ባለፈ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር መጨመሩንና የትምህርት ተሳትፎም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። ማህበሩ በመንግስት ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትና ተሳትፎ ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ተሙ ናቸው። ማህበሩ በዞኑ ያስገነባቸው ትምህርት ቤቶችም ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ የመማሪያ ክፍል ጥበት እንዲቀነስ ከማድረጉ በላይ ህጻናት በአቅራቢያቸው የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማስቻሉንም ገልጸዋል። የባቢሌ ወረዳ ጀጀባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት እቴነሽ አለማየሁ በበኩላቸው የልማት ማህበሩ በወረዳው ባከናወነው የትምህርት ቤት መሰረተ ልማትና የተማሪ ምገባ ስራ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ማህበሩ ለመምህራን የሚያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠናም የመምህራኑ አቅም እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አክለዋል።
የፌስቱላ በሽታን በመከላከል የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል
May 16, 2024 78
መቀሌ ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦የፌስቱላ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የእናቶችን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡ በመቀሌ ከተማ የፌስቱላ በሽታን በመከላከል ዙሪያ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ነጋሽ ለሆነ እንደገለፁት፤ ለበሽታው መስፋፋት የግንዛቤ ማነስ፣ ያለ እድሜ ጋብቻና በወሊድ ጊዜ የሚከሰት ከባድ ምጥ ለአብነት ይጠቀሳሉ። በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የሚቻልና ታክሞም ለመዳን ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ስለሆነም በሽታውን አስቀድሞ በመከላከል የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። ሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ ነጋሽ፤ በአገሪቷ ባሉ የፌስቱላ ህክምና ማዕከላት በሽታውን ከማከም ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በፌስቱላ በሽታ የተጠቁ እናቶችና ሴቶችን በመለየት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙና ህብረተሰቡ ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲይዝ ''ዜሮ ፕሮጀክት'' የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስካሁን በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ተግባራዊ መደረጉንና መልካም የሚባል ውጤትም መታየቱን የገለጹት አቶ ነጋሽ፤ በትግራይ ክልልም ስሓርቲ ወረዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም አመልክተዋል። በመቐለ ሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል የታካሚዎች ሃላፊ ሲስተር አልማዝ ተአምር እንደተናገሩት፤ የፌስቱላ በሽታ ተጠቂዎች በየአቅራቢያቸው ባሉ ሆስፒታሎች ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ ያሏትን የሚያኮሩ ታሪኮች ለዓለም ልናስተዋውቅ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
May 16, 2024 95
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ያሏትን ትላልቅ የሚያኮሩ ታሪኮች ማጉላትና ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። የሁለተኛው ምዕራፍ የሁለተኛ ትውልድ አገራዊ ጥሪን ተቀብለው ከመጡ አትዮጵያውያን ጋር በአድዋ ድል መታሰቢያ ውይይት እየተካሄደ ነው።   በዛሬው ዕለትም ይህን ጥሪ ተቀብለው ከመጡ የዳያስፖራ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የሁለተኛ ትውልድን ጥሪ ተቀብለው የመጡ የዳያስፖራ አካላትና ሌሎችም ታድመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው የመጡ የዳያስፖራ አካላት ሀገራቸውን እያወቁ፣ እየጎበኙ እና በልማት ውስጥም ተሳታፊ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል። ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ታሪክ በማወቅ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።   ኢትዮጵያ በርካታ የሚያኮሩ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው፤ ለአብነትም የአድዋ ድልን ጠቅሰዋል። የአድዋ ድልን ጨምሮ ሌሎችንም ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባም ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ከንቲባዋ፤ ይህንን ማገዝ እና የለውጡ አካል መሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል። አሁን ያለው ትውልድም የራሱን አኩሪ ታሪኮች እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ዳያስፖራውም እንደሁልጊዜው የሀገሩ የለውጥ አካል በመሆን መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ታሪካቸውን እንዲያውቁና ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል።   በዚህም በመጀመሪያ ምዕራፍ ጥሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ከታሪክ መሠረትዎን ይወቁ ጥሪም በርካቶች ወደ ሀገራቸው መምጣታቸውን ገልፀዋል። የሁለተኛው ትውልድ ሦስተኛው ምዕራፍ ጥሪ "leave your legacy" በሚል ከሰኔ 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።    
ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በመከላከል ረገድ የትብብር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል
May 16, 2024 67
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ተቀማጭነቱን ካርቱም ያደረገው ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል (ሮክ) ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በመከላከል የሀገራት የትብብር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ። ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን በማጠናከር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በትኩረት እየሰራች መሆኗም ተገልጿል። በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በአፍሪካ ሕብረት ሥር የተቋቋመውና መቀመጫውን ካርቱም ያደረገው ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል(Regional Operational Centre Khartoum) በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መከላከል ዓመታዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።   በመድረኩም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል አባል አገራት ተወካዮች፣ የኢንተርፖልና ዩሮ ፖል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ስጋት እየሆኑ መምጣታቻውን ገልጸዋል። ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በዜጎች የሚደርሱትን ስቃይና እንግልት ለመቀነስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ገንቢ የፖሊስ አቅምና የትብብር ምኅዳር እየፈጠረ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያም በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል ላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ፤ የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በትብብር ለመከላከል እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።   ማዕከሉም ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራቱን ወደ 13 ከፍ በማድረግ ከዩሮ ፖልና ኢንተርፖል ጋር ስኬታማ የወንጀል መከላከል ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ማዕከሉ ጽሕፈት ቤቱን በቋሚነት አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ለማዛወር በሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል በህገ-ወጥ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵም ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን በማጠናከር በማዕከሉ የሚሰጡ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ ሰፊ ተልዕኮን ሰንቃ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል። ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል(ሮክ) ቴክኒካል ዳይሬክተር ሀርቬ ጃሜት፤ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ህገ-ወጥ ስደትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራን ነው ብለዋል። ለዚህም ሁለት ዙር የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል የህገ-ወጥ ስደትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል የድርጊት መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። መድረኩም ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ተግባራትን መረጃ በመለዋወጥ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ ትብብርን ማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል በአፍሪካ ሕብረት ሥር የአፍሪካ ሀገራት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በትብብር የሚሰሩበት ተቋም መሆኑ ይታወቃል።            
አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ተጀመረ
May 16, 2024 71
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከተማዋን ከትምባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው። ንቅናቄው የተጀመረው "ህጻናትን ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት እንከላከል" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ነው። በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሙሉእመቤት ታደሰ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር እንዳሉት በከተማዋ የተጀመረው ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ለዜጎች ጤና ቅድሚያ መስጠት ይገባል። በትምባሆ ጭስ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት አለበት ነው ብለዋ። በጽዳትና ውበቷ እንዲሁም በዜጎች የተሻለ ኑሮ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ትምባሆ እንዳይጨስ የግንዛቤ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ ሙሉእመቤት ታደሰ አስታውቀዋል።
የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ  ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው   - የጤና ሚኒስቴር 
May 15, 2024 89
አርባምንጭ፤ ግንቦት 07/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል፣ የአቅም ግንባታና የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የ2016 የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም "የተሻለ አሰራር በመተግበርና በማዝለቅ ለላቀ የእናቶች፣ የሕፃናትና ወጣቶች ጤና!'' በሚል መሪ ሀሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገመገመ ነው። የምክክሩ ተሳታፊዎች የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልን ጨምሮ በሌሎች የጤና ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ጎብኝተዋል ። በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና፣ ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ እንዳሉት፤ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞትን ለመቀነስ በተቀናጀ መንገድ ሲሰራ ቆይቷል።   በዚህም የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንና በቀጣይም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የምልከታው አላማ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ በሆስፒታሎች፣ በጤና ጣቢያዎችና በጤና ኬላዎች የተከናወኑ ተግባራትን ለመፈተሽ መሆኑን ዶክተር አለማየሁ አስረድተዋል። በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በነበራቸው ጉብኝትም ሆስፒታሉ በተለይ የጨቅላ ህፃናትና የእናቶችን ሞት ከመቀነስ ረገድ አበረታች ለውጥ ማሳየቱን ገልጸው፣የሆስፒታሉ ሐኪሞች የሚያደርጉት እንክብካቤ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ሚኒስቴሩ በጤና ተቋማት ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚሰራ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው፣ በቀጣይ ሀብት በማፈላለግና ማህበረሰቡን በማሳተፍ የህክምና ቁሳቁስ ላይ የሚስተዋለውን እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰራ አመልክተዋል። በዚህም የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻልና የአቅም ግንባታ እንዲሁም የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በማዘመን ጥራቱን የጠበቀ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።   የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና የህፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አምባቸው ዱማ፣ በሆስፒታሉ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል። አገልግሎቱ ውጤታማ ሊሆን የቻለው የህክምና ባለሙያዎችና ሆስፒታሉ በተቀናጀ መንገድ ለተገልጋዮች በቂ ክትትል በማድረጋቸው መሆኑን ገልጸው፤ በጤና ተቀማት መካከል የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።   የሆስፒታሉ ተገልጋይ ወይዘሮ ዜና ባደገ፤ በሆስፒታሉ ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ ክትትል በማድረግ ልጃቸውን በሰላም መገላገላቸውንና ከወለዱ በኋላም ለልጃቸው በወቅቱ ክትባት ከመስጠት አንስቶ በህጻናት ጤና አጠባበቅ ላይ ትምህርት መከታተላቸው ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በተጨማሪ የሸለሜላ ጤና ኬላና ጤና ጣቢያ፣የድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎች የጤና ተቋማት የስራ እንቅስቃሴና አገልግሎት አሰጣጥን ጎብኝተዋል።
በክልሉ በፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽንና በፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው- ቋሚ ኮሚቴው 
May 15, 2024 103
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን እና በፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ማረጋገጡን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ። ቋሚ ኮሚቴው በሲዳማ ክልል እየተከናወነ ያለውን የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን እና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ሥራዎች ምልከታ አድርጓል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት እንደሀገር የተጀመረው የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽንና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ሥራዎች በክልሉ ውጤት እየተገኘባቸው ነው።   ከትራንስፎርሜሽን ግቦች መካከል ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ላይ ተሳትፎውን ማሳደግ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በእዚህ በኩል በክልሉ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። በተለይ በህብረተሰብ ተሳትፎ የፖሊስ ተቋማትን የመገንባትና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ሥራ በመሰራቱ መሰረታዊ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል። በፍርድ ቤቶች፣ በዐቃቢያነ ህግ እና በፖሊስ የተከናወነው ባለሙያን የማጥራት ሥራ ሌላው መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑንም ገልጸዋል። በስራቸው የተሻሉትን ከማበረታታት ባለፈ እገዛ የሚሹትን በስልጠናና በተለያየ መንገድ የመደገፍና ሌሎች የእርምት ሥራዎች መሰራታቸው በመልካምነት እንደሚወሰዱም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። ፍትህን ለማረጋገጥ በክልሉ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐቶችን በሕግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ እየተሰራ ያለው ሥራም አበረታች መሆኑን ወይዘሮ እፀገነት ጠቅሰዋል። የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የፍትህ ሥርዐቱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሥራዎችን ለማሳካት ተቋማት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።   በእዚህም ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት መቻሉን ጠቁመው፣ ህዝቡ በፍትህ ሥርዐቱ ላይ ያለው አመኔታ እንዲጨምር ከአጎራባች ክልሎች ልምድ የመቀመር ሥራም ተሰርቷል ብለዋል። ህብረተሰቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ የተጀመረው የትራንስፎርሜሽን ሥራ ውጤታማነት እንዲጠናከር ምክር ቤቱ በባለቤትነት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቶ ማሩ በበኩላቸው "እንደ ክልል የፍትህ ሥርዐቱን ትራንስፎርም ለማድረግ 10 የለውጥ አምዶችን ይዘን እየሰራን ነው" ብለዋል።   ከነዚህ አምዶች መካከል እንደ “አፊኒ” ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የዳኝነት ሥርዐቶችን በህግ ማዕቀፍ አስደግፎ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ ያለው ሥራ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። በፍትህ ሥርዐት ውስጥ ለመልካም አስተዳደር ተግዳሮት የሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎችን ለማጥራት በተሰሩ ሥራዎችም ከ40 በላይ የሚሆኑትን ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። የፀጥታ ተቋማትን የመገንባት፣ በተለወጠ የሰው ሀይልና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ሥራ በትኩረት መሰራቱን ያስረዱት ደግሞ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ናቸው።   ለአብነትም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ የፖሊስ ጽህፈት ቤቶች እና በ580 ቀበሌያት ደግሞ የፖሊስ መረጃ መቀበያ ማዕከላት መገንባታቸውንም አስረድተዋል። አቶ አለማየሁ እንዳሉት የጸጥታ ሥራውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በተሰራው ሥራም በሀዋሳ ከተማ 85 በመቶ በደህንነት ካሜራ የታገዘ ስራ እየተሰራ ነው። ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ እና በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባሉ የፍትህ ተቋማት ላይ እየተከናወኑ ያሉ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
የአዘርባጃን ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ለኢትዮጵያ የሰቪል ሰርቪስ ሪፎርም ምሳሌ የሚሆን ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
May 15, 2024 105
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ)፡- የአዘርባጃን ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ለኢትዮጵያ የሰቪል ሰርቪስ ሪፎርም ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ በአዘርባጃን ባኩ የሚገኘውን የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ በዲጅታል የሚሰጡበትን የአሳን አገልግሎቶች ማዕከልን ጎብኝቷል። ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት አቶ ተመስገን፥ በአሳን ማዕከል የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ በዲጅታል አሰራር በተቀላጠፈ መንገድ እየተሰጡ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። የሀዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስና ትናንሽ ሙስናዎችን ለመከላከል የጀመሩት ይህ አገልገሎት አሰጣጥ አሁን ላይ በዓለም እውቅና የተቸረው ሆኗል ነው ያሉት።   በጉብኝታቸው ወቅትም በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት የህዝብ እርካታ 99 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱና በዚህም መንግስት የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን መቀዳጀቱ እንደተገለጸላቸው ጠቅሰዋል። በአዘር ባጃኑ አሳን የመንግስታዊ አገልግሎቶች ማዕከል የሚሰጠውን የተቀናጀ የዲጅታል አገልግሎት ኢትዮጵያ በምሳሌነት እንደትምወስድም ተናግረዋል። እንደ ሀገር መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል በጉዞ ላይ ነን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም የአዘር ባጃንን ልምድ ከመቅሰም ባለፈ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል። መንግስት በሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማትና ማህበራዊ መስኮች እያስመዘገባቸው የሚገኙ ውጤቶችን በአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለመድገም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን የሚያሳዩ እርምጃዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፥ በሙከራ ደረጃ ስምንት ተቋማት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያን እየተገበሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥም ሪፎርሙን ወደ ሙሉ ትግበራ በማስገባት ሁሉም የፌደራል፣ የክልልና በተዋረድ ያሉ ተቋማት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ ይደረጋል ነው ያሉት።  
በጤናው ዘርፍ ለውሳኔ ሰጭነት የሚያግዝ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ እንዲኖር ትኩረት ይደረጋል - የአፋር ክልል ጤና ቢሮ
May 15, 2024 70
ሠመራ፤ ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ)፡- በጤናው ዘርፍ ለውሳኔ ሰጭነት የሚያግዝ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ እንዲኖር ትኩረት እንደሚደረግ የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ተናገሩ። "የተጠናከረ አመራርና ተጠያቂነት በመረጃ ላይ ለተመሠረተ የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ሐሳብ ክልል አቀፍ የጤና መረጃ ሣምንትን የተመለከተ መድረክ በሠመራ እየተካሄደ ይገኛል። በዚሁ ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ጥራት ያለው እውነተኛና ያልተዛባ መረጃን ማድረስ እንደሚያሻ ገልፀው፤ ይኸም ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት ጥራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም "የመረጃ ቋት ላይ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል" ያሉት ሃላፊው፤ መረጃን መጨመርም ሆነ መቀነስ በተለይ በጤናው ሴክተር ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ተናግረዋል። ሥራው የባለሙያ እገዛ የሚያስፈልገው ከሆነ እገዛ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ በተቃራኒው ሀሰተኛ መረጃ ማስተላለፍ ግለሰብንም ሆነ ህዝብን እጅግ የሚጎዳ ነው ብለዋል።   በመሆኑም በጤናው ዘርፍ ለውሳኔ ሰጭነት የሚያግዝ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ እንዲኖር ቢሮውና በደረጃው ያሉ የሴክተሩ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አሚን አርባ በበኩላቸው በመረጃ ቋት ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ አሰጣጥን መተግበር የሚችል ባለሙያ ማፍራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል። አሁን የመረጃ ስርዓት አያያዙ ከወቀሳ የፀዳ እና ዲጂታላይዝድ እየሆነ መምጣቱን የገለፁት አቶ አሚን፤ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን ለይተን እየሰራን እንገኛለን ነው ያሉት። ዳይሬክተሩ ከወረቀት ነፃ የሆነው የመረጃ ስርዓት መኖሩ ታካሚ ካርድ በተደጋጋሚ ከማውጣትና የጤና ሁኔታን የሚገልፁ መረጃዎችን ከጥፋት የሚታደግ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል። ሰለሆነም መረጃን በቀላሉ መለየትና ማግኘት እንዲቻል የሚያደርግ አሠራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት ላይ የሚመክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው
May 15, 2024 92
አርባ ምንጭ ፤ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)- በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ላይ የሚመክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው። የምክክር መድረኩ እየተካሄደ ያለው "የተሻለ አሰራር በመተግበርና በማዝለቅ ለላቀ የእናቶች፣ የሕፃናትና ወጣቶች ጤና!'' በሚል መሪ ሀሳብ ነው።   በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የተጠሪ ተቋማት፣ የሆስፒታሎችና አጋር ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህፃናትና አፍላ ወጣቶች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በእናቶች፣ በህጻናትና አፍላ ወጣቶች ላይ የተተገበሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝቶባቸዋል። የጤና አገልግሎቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአገልገሎቱን ተደራሽነትን ማስፋትና ጥራት ያለው የአገልግሎት ስርአት መዘርጋት እንደሚገባ ተናግረዋል። የጤና ሥራ ለአንድ አካል የሚተው አይደለም ያሉት ዶክተር አለማየሁ፤ አገልግሎቱን ለማስፋት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል። መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተመላክቷል። ከእዚህ ጎን ለጎን በአርባምንጭ ከተማ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተሞክሮ ለመውሰድ ጉብኝት ይደረጋል። በጉባኤው ማጠቃለያም በጤና አገልግሎት አሰጣጡ ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሔዎችና ለቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ታውቋል።  
በትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤን የማጎልበት ተግባር በትኩረት ይከናወናል
May 14, 2024 139
አዳማ፤ ግንቦት 6/2016 (ኢዜአ)፦በትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤ ማጎልበት ላይ ያተኮረ ስራ እንደሚከናወን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ። የጤና ሚኒስቴር በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚስተዋለውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ለመከላከልና ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለመ የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል። በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ እና ዘርፈ ብዙ ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘላለም ግዛቸው በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተቋማቱ የሚገኙ ተማሪዎች በቫይረሱ ስርጭት ላይ ተከታታይ መረጃ እንዲኖራቸው በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለይም ተማሪዎች መዘናጋት ሳይገባቸው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል በትምህርት ተቋማት ያሉ ወጣቶችን ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የህክምና አገልግሎቶችንና የመድኃኒት አቅርቦትን የማሻሻል ስራም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ምህረተክርስቶስ ታምሩ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሽታውን የመከላከል ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።   ከዚሁ በተጓዳኝ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ አግኝተው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ከአጋር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፍ እየተደረገ ነው ገልጸዋል። በተጨማሪም ከሚኒስቴሩ ጀምሮ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ለመከላከል እንዲቻል ራሱን የቻለ ዘርፉን የሚመራ አደረጃጀት እንዲኖር አመልክተዋል። ተማሪዎቹ ወደተቋማቱ ሲገቡ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትና መከላከል ምክር አስቀድሞ ማግኘት እንዳለባቸው የጠቀሱት ደግሞ የክርስትያን በጎ አድራጎት ማህበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ንጉሱ ለገሰ ናቸው።   ምክር ቤቱ ተማሪዎቹ መረጃና ምክር አግኝተው ተጋላጭነታቸው የሚቀንስበትን ስራ ከጤናና ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን የበኩሉን እንደሚወጣ አክለዋል።  
በመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ሊተገበር ነው
May 14, 2024 159
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ በቅርቡ ሊተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ። የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ሀገር አቀፍ አስገዳጅ ደረጃ ወጥቷል።   አስገዳጅ ደረጃው መድኃኒት ቤትም ሆነ መድኃኒት መደብር ምን ዓይነት ባለሙያዎች ሊኖሯቸው ይገባል፣ ምን ዓይነት መድኃኒት ይይዛሉ፣ የመድኃኒት ቤቱ ወይም መደብሩ ስፋት የሚለውንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል። ክልሎች ለመድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ የሚሰጡበት መስፈርት የተለያየ መሆኑን አንስተው፤ ወጥነት ያለው ለማድረግ ደረጃው መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ደረጃው መውጣቱን ተከትሎ አሠራሩ እስኪተገበር ድረስ ለአዲስ መድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ እንዳይሰጥ መደረጉንም አንስተዋል። የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ ደረጃ ወጥቶ ሲሰራ ስላልነበር በክልል ቁጥጥር አካላት ወጥ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል።   ስለሆነም በሁሉም ተቆጣጣሪ አካላት ሊተገበር የሚችል ሀገራዊ መስፈርት ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ደረጃው መውጣቱን ገልፀዋል። በደረጃው የተቀመጡ መስፈርቶች ላይ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለክልል ተቆጣጣሪ አካላት ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። ደረጃው አዲስ በመሆኑ በወጥነት እንዲተገበር ባለሙያዎችንና ባለድርሻ አካላትን የማሰልጠን ተግባር ይቀጥላል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም