ቀጥታ፡

በትምባሆ ጭስ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ በትምባሆ ጭስ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከተማዋን ከትምባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ አካሂዷል።

ንቅናቄው የተጀመረው "ህጻናትን ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት እንከላከል" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ነው።

በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ እንዳሉት በከተማዋ የተጀመረው ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ለዜጎች ጤና ቅድሚያ መስጠት ይገባል።

ለዜጎች ጤና ጠንቅ የሆኑ እንደ ትምባሆ ጭስ ያሉ የጤና ስርዓትን የሚያዛቡ እና አካባቢን የሚበክሉ ተግባራትን ችላ ማለት እንደማይገባ ጠቁመዋል።

መንግስት ውብና ጽዱ ከተማ ለመፍጠር እያደረገ ላለው ጥረት የከተማዋ ነዋሪ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሙሉ እመቤት ታደሰ በበኩላቸው፥ ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ ትምባሆ እንዳይጨስ የግንዛቤ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።


 

የትምባሆ ጭስን መጠቀም በሰው ልጆች ላይ አካላዊ፣ አዕምሯዊና ስነ-ል ቦናዊ ጉዳት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አንስተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ህግን በማክበር በጋራ መከላከል እንዳለበት ጠይቀዋል።

ለ22 ዓመታት በትምባሆ ማጨስ ሱስ ቆይተው አሁን ከሱስ የተላቀቁት አቶ ዮናታን ሊሬ ትምባሆ ለሞት የሚዳርግ ጎጂ ነገር ነው ብለዋል።


 

በድርጊቱ ቢገፉበት ኖሮ ህይወታቸውን ሊያሳጣቸው እንደሚችል ጠቅሰው፥ በራሳቸው ቁርጠኝነት ከሱስ ነጻ እንደወጡ እና ጤናማ ህይወትን መምራት እንደጀመሩ አክለዋል።

በመሆኑም ሌሎች ትምባሆ ማጨስን የሚያዘወትሩ ግለሰቦች በጤናቸው እና በህይወታቸው ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ድርጊቱን ሊያቆሙ እንደሚገባ መክረዋል።

የዓለም "ትምባሆ የማይጨስበት ቀን" በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ በዓለም ለ36ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምባሆ ማጨስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም