በትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤን የማጎልበት ተግባር በትኩረት ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤን የማጎልበት ተግባር በትኩረት ይከናወናል
አዳማ፤ ግንቦት 6/2016 (ኢዜአ)፦በትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ግንዛቤ ማጎልበት ላይ ያተኮረ ስራ እንደሚከናወን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚስተዋለውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ለመከላከልና ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለመ የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ እና ዘርፈ ብዙ ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘላለም ግዛቸው በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተቋማቱ የሚገኙ ተማሪዎች በቫይረሱ ስርጭት ላይ ተከታታይ መረጃ እንዲኖራቸው በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በተለይም ተማሪዎች መዘናጋት ሳይገባቸው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል በትምህርት ተቋማት ያሉ ወጣቶችን ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የህክምና አገልግሎቶችንና የመድኃኒት አቅርቦትን የማሻሻል ስራም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ምህረተክርስቶስ ታምሩ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሽታውን የመከላከል ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ከዚሁ በተጓዳኝ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ አግኝተው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ከአጋር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፍ እየተደረገ ነው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከሚኒስቴሩ ጀምሮ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ለመከላከል እንዲቻል ራሱን የቻለ ዘርፉን የሚመራ አደረጃጀት እንዲኖር አመልክተዋል።
ተማሪዎቹ ወደተቋማቱ ሲገቡ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትና መከላከል ምክር አስቀድሞ ማግኘት እንዳለባቸው የጠቀሱት ደግሞ የክርስትያን በጎ አድራጎት ማህበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ንጉሱ ለገሰ ናቸው።
ምክር ቤቱ ተማሪዎቹ መረጃና ምክር አግኝተው ተጋላጭነታቸው የሚቀንስበትን ስራ ከጤናና ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን የበኩሉን እንደሚወጣ አክለዋል።