ለንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ትግበራ መሳካት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ትግበራ መሳካት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦የፍትሕ ሚኒስቴር የንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ትግበራ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠየቀ።
የንግድና ሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፤ የንግድ ሥራ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ያህል በአግባቡ ካልተመራ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በንግድ ሥራዎች ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሰብአዊ መብቶች አንጻር የተቃኙ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 የተባበሩት መንግሥታት 3ኛው ሁሉን-አቀፍ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ግምገማ ላይ ብሔራዊ ሪፖርት ማቅረቧን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከቢዝነስ ነክ ጎጂ የሰብዓዊ መብት ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዲቻል በቢዝነስና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ-ግብር እንድታዘጋጅ ምክረ-ሃሳብ ቀርቦላት እንደነበር አስታውሰዋል።
ለዚህም በዛሬው እለት ከንግድ ጋር የተያያዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል ያለመ ብሔራዊ የድርጊት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል።
የድርጊት መርሃ-ግብሩ መዘጋጀቱ ለንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ጋር በሽርክና የሚከናወኑ ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ለድርጊት መርሃ-ግብሩ ስኬት የበርካታ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት የሰጠ የንግድና የልማት አሠራርን ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም የመንግሥት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም ቅንጅታዊ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 መንግሥታት በንግድ አውድ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ የቢዝነስና የሰብዓዊ መብቶች መመሪያ መርሆዎችን ማጽደቁ ይታወቃል።