የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለቅድመ ወሊድ ክትትልና ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለቅድመ ወሊድ ክትትልና ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)-የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የቅድመ ወሊድ ክትትልን ለማጠናከርና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትኩረት መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
የጤና ሚኒስትር ያዘጋጀውና የእናቶች፣ የህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ጤና አጠባበቅ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን የሚገመግም መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በተለይ የቅድመ ወሊድ ክትትልን ለማስፋትና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
ነፍሰጡር እናት በጤና ተቋም የምታደርገው የእርግዝና ክትትል ለእናትየውም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአሁኑ ወቅት ለክትትል ወደጤና ተቋም የሚመጡ እናቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።
አንዲት እናት መፀነሷን ካወቀችበት ጊዜ አንስቶ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ክትትል ማድረጓ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ጉዳት ለመቀነስ ከሚከናወኑ የጤና ልማት ሥራዎች መካከል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ አንዱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ናቸው።
በክልሎች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የተሰራው ሥራ አበረታች ቢሆንም አፈጻጸሙ ወጥ እንዳልሆነ ነው የገለጹት።
በቀጣይ በክልሎች ወጥ የአሰራር ስርአት በመዘርጋት በገጠርም ሆነ በከተማ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፤ በክልሉ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፣ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም በቀድሞው የደቡብ ክልል ከ100 ሺህ ወላድ እናቶች 871 የሚሆኑት በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የሞት ምጣኔው ወደ 267 ዝቅ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረገችው በሚኒስትሩ የስነ-ተዋልዶ፣ የጨቅላ ህፃናት እና የህፃናት በጎ ፍቃደኛ አምባሳደር አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ እንዳለቸው፤ መንግስት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።
እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 በኢትዮጵያ ከተወለዱ 1 ሺህ ጨቅላ ህፃናት 33 የሚሆኑት ይሞቱ እንደነበር አስታውሳ፣ በ2023 የሚሞቱ ህጻናት ቁጥርን ወደ 26 ዝቅ ማለቱን ሪፖርቶች እንደሚያሳዩ ገልጻለች።
ይህም ባለፉት ዓመታት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተተገበሩ የጤና ፖሊሲዎች ውጤታማ ስለመሆናቸው ማሳያ መሆኑን አርቲስት መቅደስ ገልጻ፣ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብላለች።
በሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተጠሪ ተቋማት፣ የባለድርሻ አካላት እንዲሁም የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።