ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በመከላከል ረገድ የትብብር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በመከላከል ረገድ የትብብር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ተቀማጭነቱን ካርቱም ያደረገው ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል (ሮክ) ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን በመከላከል የሀገራት የትብብር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ።
ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን በማጠናከር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በትኩረት እየሰራች መሆኗም ተገልጿል።
በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በአፍሪካ ሕብረት ሥር የተቋቋመውና መቀመጫውን ካርቱም ያደረገው ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል(Regional Operational Centre Khartoum) በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መከላከል ዓመታዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል አባል አገራት ተወካዮች፣ የኢንተርፖልና ዩሮ ፖል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ስጋት እየሆኑ መምጣታቻውን ገልጸዋል።
ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በዜጎች የሚደርሱትን ስቃይና እንግልት ለመቀነስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ገንቢ የፖሊስ አቅምና የትብብር ምኅዳር እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል ላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ፤ የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በትብብር ለመከላከል እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።
ማዕከሉም ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራቱን ወደ 13 ከፍ በማድረግ ከዩሮ ፖልና ኢንተርፖል ጋር ስኬታማ የወንጀል መከላከል ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ጽሕፈት ቤቱን በቋሚነት አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ለማዛወር በሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል በህገ-ወጥ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵም ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን በማጠናከር በማዕከሉ የሚሰጡ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ ሰፊ ተልዕኮን ሰንቃ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል(ሮክ) ቴክኒካል ዳይሬክተር ሀርቬ ጃሜት፤ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ህገ-ወጥ ስደትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራን ነው ብለዋል።
ለዚህም ሁለት ዙር የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል የህገ-ወጥ ስደትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል የድርጊት መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
መድረኩም ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ተግባራትን መረጃ በመለዋወጥ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ ትብብርን ማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የካርቱም ቀጣናዊ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል በአፍሪካ ሕብረት ሥር የአፍሪካ ሀገራት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በትብብር የሚሰሩበት ተቋም መሆኑ ይታወቃል።