ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው - ኮሚሽኑ

ሀዋሳ፤ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)፦ ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሀገራዊ ምክክር ዝግጁ በማድረግ በሀገራዊ ዘላቂ ሠላም ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ተናገሩ።

በሀዋሳ የኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ አዘጋጅነት በግጭት አፈታትና ሠላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ሀገራዊ የምርምር ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በጉባኤው ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ በአሁን ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች ህዝቡን ለሠላምና ምክክር ዝግጁ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው።

በተለይ ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች በአመቻችነትና በበጎ ፍቃደኝነት እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች አዎንታዊ የሰላም ግንባታን ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅና በማሰራጨት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ በራሱ በኩል ለሚያካሂዳቸው ጥናቶች ዩኒቨርሲቲዎች አጥኚ ምሁራንን በማቅረብም የጎላ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የምርምር ጉባኤዎች ዘላቂ ሠላም ለማስፈንና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት መደላድል በመፍጠር የኮሚሽኑን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንደሚረዱም ገልጸዋል።


 

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ጂሎ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የግጭት አፈታት እና የሠላም ግንባታ ፅንሰ ሀሳቦች የዩኒቨርሲቲው አሁናዊ የምርምር ሥራዎች የትኩረት መስኮች ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በራሱ አቅም ከሚያካሂዳቸው ምርምሮች ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ተቋማትና ሌሎች አጋሮች ጋር ውል ገብቶ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደብረወርቅ ደበበ፤ የምርምር ጉባኤው ዓላማ እንደ ሀገር ዘላቂ ሠላም ማምጣት የሚቻለበትን መንገድ የሚያመላክቱ ጥናቶች በውይይት ዳብረው የፖለሲ አካል እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያበረክተው አተዋዖ የጎላ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ደብረወርቅ፤ "ከኮሚሽኑ ጋር በምርምር ሥራዎችና ሌሎች ተግባራት ጋር ተናበን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ኮሚሽኑ የያዛቸውን ሀገራዊ ግቦች ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ከ46 የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት ስምምነት መፈራረሙ ተመላክቷል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የመንግስት አካላትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም