የፌስቱላ በሽታን በመከላከል የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል

መቀሌ ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦የፌስቱላ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የእናቶችን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መስራት  አስፈላጊ መሆኑን የሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡

በመቀሌ ከተማ የፌስቱላ በሽታን በመከላከል ዙሪያ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ነጋሽ ለሆነ እንደገለፁት፤ ለበሽታው መስፋፋት የግንዛቤ ማነስ፣ ያለ እድሜ ጋብቻና በወሊድ ጊዜ የሚከሰት ከባድ ምጥ ለአብነት ይጠቀሳሉ። 

በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የሚቻልና ታክሞም ለመዳን ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤  ነገር ግን በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ስለሆነም በሽታውን አስቀድሞ በመከላከል የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ ነጋሽ፤ በአገሪቷ ባሉ የፌስቱላ ህክምና ማዕከላት በሽታውን ከማከም ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በፌስቱላ በሽታ የተጠቁ እናቶችና ሴቶችን በመለየት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙና ህብረተሰቡ ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲይዝ ''ዜሮ ፕሮጀክት'' የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ፕሮጀክቱ እስካሁን በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ተግባራዊ መደረጉንና መልካም የሚባል ውጤትም መታየቱን የገለጹት አቶ ነጋሽ፤ በትግራይ ክልልም ስሓርቲ ወረዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም አመልክተዋል።

በመቐለ ሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል የታካሚዎች ሃላፊ ሲስተር አልማዝ ተአምር እንደተናገሩት፤ የፌስቱላ በሽታ ተጠቂዎች በየአቅራቢያቸው ባሉ ሆስፒታሎች ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሃምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም