ፖለቲካ
በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ የተቀናጀ አመራር በመስጠት ሁለንተናዊ የልማት ስኬት ተመዝግቧል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
May 15, 2024 86
አዲስ አበባ፤ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ የተቀናጀ አመራር በመስጠት ሁለንተናዊ የልማት ስኬት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማው በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦችን አንስቶ መምከሩ ይታወቃል። በመድረኩ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ግጭቶችን ማስቀረት ብልጽግናን ማጽናት "በሚል ርዕስ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል። በማብራሪያቸውም ግጭት የብልጽግና ሳንካ በመሆኑ መቀነስና ማስቀረት በሚቻልበት ልክ በመሥራት ሰላምን ማስፈን ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። በለውጥ ውስጥ የሚያጋጥም አለመረጋጋት ወደ ውድቀት እንዳይወስድ አለመረጋጋትን መግታት የሚችል ዕድገት መፍጠርና ወደ ሁለንተናዊ ውህደት መሻገር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል። ለዚህም ጠቃሚ ሀሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም፣ የልማትና ጠንካራ ተቋማት የመገንባት ሀሳቦች ያስፈልጋሉ ብለዋል። በዚህ ረገድ ማነቆዎችን እየፈታን በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ኢትዮጵያ ስኬትን ያስቀጠለ ብልጽግናን ያስቻለ ጉዞ ውስጥ መሆኗን ገልፀዋል። ብልጽግና ፓርቲ በሃሳብ ልዕልና ብቻ መዳኘት የሚፈልግ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የሕዝብ ውይይቶች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆኑንም አንስተዋል። በመሆኑም ሰላምን ለማረጋገጥ በተከታታይ በተሰሩ ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በክልሉ ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በአገልግሎት አሰጣጥና የልማት ሥራዎች ላይ እንከን ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። በክልሉ የጥፋት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል ሕብረተሰቡን በማደናገር ለማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቀውሶች መዳረጉን ጠቅሰዋል። በተለይም የግብርና እና ኢንቨስትመንት ሥራን ማስተጓጎሉን አስታውሰው፤ መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር በመግባቱ ችግሩ እየተፈታ መሄዱን ገልፀዋል። የክልሉ መንግሥት የአሰራር ለውጥና የተቀናጀ አሠራር በመፍጠር የልማትና የሕዝብ አገልግሎቶች በተሳካ መልኩ እንዲቀጥሉ ማድረጉን አንስተዋል። በመሆኑም በክልሉ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል። የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሄደበት ርቀት የተሳካ መሆኑን አስታውሰው፤ ይኸው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።    
የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎችን ለማፋጠን ከአዘርባጃኑ ጉብኝት ትልቅ ተሞክሮ ተገኝቷል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
May 15, 2024 84
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአዘርባጃኑ ጉብኝት ትልቅ ተሞክሮ መገኘቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት በአዘርባጃን ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በአዘርባጃን በተለይ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል እየተሰጠ እንደሚገኝና ይህም የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ምቹ እንዲሆን ማድረጉን መመልከታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ የሆነ ሪፎርም ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ደግሞ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ሪፎርም የማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል። የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ስራ እየተካሄደ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከአዘርባጃን ጋር በመስራት በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ጉብኝቱ እንደሚጠቅምም አክለዋል። በተለይ በስምንት የመንግስት ተቋማት ውስጥ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸው ከአዘርባጃን የተገኘው ተሞክሮ ለተጀመረው ስራ እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል ገልጸዋል። የኢትዮጵያና የአዘርባጃን የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም ጠቁመዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
May 15, 2024 209
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 32ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች፦ 1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በ4 የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘ የ52 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ለስራ ፈጠራ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከጣልያን መንግስት የተገኘ 10 ሚሊዮን ዩሮ፣ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኘ 255 ሚሊዮን ዶላር አንዲሁም ለፓወር ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንትና ሞደርናዜሽን ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ማስፈፀሚያ የሚውል 393 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተደረጉ የብድር ናቸው፡፡ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘው ብድር 0.01% ወለድ እና ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጭዎች 0.1% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብበት ሆኖ የ15 ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከጣልያን መንግስት የተገኘው ብድር ከወለድ ነጻ ከመሆኑም በላይ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለውና በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኙት ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.75% የአገልግሎት ክፍያ ብቻ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ሁሉም ብድሮች ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 2. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባቀረባቸው 3 ረቂቅ አዋጆች እና 1 ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን መሰረታዊ ከሆኑ መብቶች አንዱ የሆነውን የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር፣ የኢሜግሬሽን አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያዊንና ለውጭ አገር ዜጎች በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና መስጠት እንዲቻል፣ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የተሟላ የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ሁለተኛው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን በድጋሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ስርዓት የሰፈነበት እንዲሆን፣ የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት በሚገባ የሚያስጠብቅ ስልጣንና አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ 3. ሶስተኛው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ማድረግ፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረታዊ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና ለማስከበር ሁሉን አቀፍ የምዝገባ ስርዓት መዘርጋት የሚገባ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረቡት 3 ረቂቅ አዋጆች ላይ በሰፊው ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 4. አራተኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ መሸፈን የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያያው በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በቀረቡ 2 የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት መካከል ያለውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡ ሌላው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቶቹ ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና በአገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የሚያጎለብቱ መሆኑን በመገንዘብ፣ የስምምነቶቹ መጽደቅ የአገራችንን ጥቅም የማይጎና የተለየ ግዴታም የማያስከትል መሆኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለዘላቂ የሀገር ሰላም የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን ነው -አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች
May 15, 2024 60
አዳማ ፤ ግንቦት 07/2016 (ኢዜአ)፡- ከአካባቢያችን ጀምሮ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለዘላቂ የሀገር ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ገለጹ። የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች አለመግባባቶችን በሽምግልና፣ በምክርና በተግሳጽ በመፍታት ለሰላም መከበር አስተዋጽኦቸው የጎላ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው የምስራቅ ሸዋ ዞን እና የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች እንዳሉት ሁሉም በየአካባቢው የሚያደርጋቸው ሰላምን የመጠበቅ ስራ አንድ ላይ ሲደመር የሀገር ሰላም ለማጽናት ያስችላል ብለዋል። ከአባ ገዳዎቹ መካከል የምስራቅ ሸዋ ዞንና የአዳማ ከተማ የአባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባገዳ ረታ ያኢቦሩ፣ ሁሉም የቤቱን፣ የጎረቤቱንና የአካባቢውን ሰላም ከጠበቀ ሀገር ሰላም ይሆናል ይላሉ። ''የአካባቢያችንን ሰላም ለማስፈን በባህላዊ ስርዓትና ወግ መሰረት አለመግባባቶችንና ግጭትን እየፈታን እንገኛለን'' ብለዋል። ሰርቶ ለመለወጥና ሀገር ከማልማት በዘለለ የተረጋጋ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እንዲኖር ሁሉም ለአካባቢው ሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት ሲሉም ገልጸዋል። በአካባቢያቸው አለመግባባትና ግጭቶች ሲያጋጥሙ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እየተወጡ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም በባህላዊ ፍርድ ቤቶች አማካኝነት ትልልቅ አለመግባባቶችን እየፈቱ መሆኑን ተናግረዋል። በአዳማ ከተማ የጨፌ ወረዳ ባህላዊ ፍርድ ቤት አባል ሃደ ሲንቄ ፍታሌ ደክሲሳ በበኩላቸው ከቤትና ጎሮቤት ጀምረው ሰላም የሰፈነበት አካባቢ እንዲኖር ያላቸውን ማህበራዊ ተሰሚነት ተጠቅመው የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል። ሰላም ማስፈን የሚጀምረው ከራስ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን በመምከርና በመገሰጽ ለሀገር የሚጠቅም ስራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል። ወደ ፊትም ከአካባቢያቸው ጀምሮ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት እንዲጎለብት የሚጠቅባቸውን ማህበራዊ ሃላፊነት እንደሚወጡም ገልጸዋል። የማህበረሰባችን ሰላም እንዲሰፍን በማድረጉ ሂደት ቅድሚያ የእኛ አንድነትና ትብብር በተግባር መታየት አለበት የሚሉት ደግሞ በአዳማ ከተማ የጨፌ ወረዳ ባህላዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢና የሀገር ሽማግሌ ደጀኔ አረጋ ናቸው። የሀገር ሰላም እንዲጠበቅ ከአካባቢያቸው ጀምሮ የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባቶችን የመፍታት ስራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡ ሌላዋ ሃደ ሲንቄ ዘውዴ ከበደም በአካባቢያቸው ያላቸውን ማህበራዊ ተሰሚነት በመጠቀም ሰላም የማስፈን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች በልማት ስራ ላይ በመሳተፍ ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ በመምከራቸው በአካባቢያቸው ሰላም መስፈኑንም አክለዋል፡፡      
ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሳካት አስፈላጊውን እገዛና ትብብር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
May 15, 2024 69
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሳካት አስፈላጊውን እገዛና ትብብር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የምክክር ሂደቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ሲያበረክት የቆየውን አስተዋጽኦ በማስመልከት ውይይት እያደረገ ይገኛል። ከዚሁ መድረክ በተጓዳኝም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክቡ ተጠቁሟል።   በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል፤ ምክር ቤቱ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይም በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬት የበኩሉን በማበርከት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የምክር ቤቱ ድጋፍና አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል። በዛሬው ዕለትም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡ እና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክቡ ጠቁመዋል። በውይይት መድረኩ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ህብረት ገለጸ
May 14, 2024 99
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጽጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ተግባራዊ የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል። ኮሚሽነር ባንኮሌ የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም የታጠቁ ኃይሎችን ትጠቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ሂደት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ከሰላም ፈንድ ቋቱ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ማዕቀፍ የመጀመርያዋ ተጠቃሚ አባል አገር መሆኗን ገልጸዋል። በተጨማሪም ህብረቱ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ማሰማራቱ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነቱን እንደሚያመላክት ተናግረዋል። አክለውም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ የማዳበርና ማስፈጸም ስራዎችም ህብረቱ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል። ሁለቱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ወሳኝ በሆኑ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። አምባሳደር ባንኮሌ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስፈን ጥረቶች ውስጥ ወሳኝና ውጤታማ አገር እንደሆነች ተናግረው ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚሻ አንስተዋል።
ኢትዮጵያና አዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ ስምምነት ተፈራረሙ
May 14, 2024 158
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና አዘርባጃን በፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ እና ተጨማሪ ስራዎችን ተቀራርቦ መተግበር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።   ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዘርባጃን በነበራቸው የመጀመሪያ ቀን ውሎ በተለያዩ መስኮች በጋራ መልማትና በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መንገድ የከፈተ መሆኑን አመላክተዋል። አዘርባጃን በዲጂታል አገልግሎት በተለይም በክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማትና የዘመነ የሲቪል ሰርቪስ ተደራሽነትን በላቀ መንገድ እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።   ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ተዘዋውረን የጎበኘናቸው ተቋማትም ሀገሪቱ በዲጂታል ስርአት ላቅ ያለ እምርታ ላይ እንደምትገኝ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉን ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ስራዎችን ተቀራርቦ ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል። በቀጣይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራዎችን በዲጂታላይዜሽን በመታገዝ የላቀ ስራን ለመተግበርና ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ስርዓትን ለማረጋገጥ ከአጋር ሀገር አዘርባጃን ጋር ተቀራርበን ለመስራት ተስማምተናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች የኃላፊነት ምደባ ሰጠ
May 14, 2024 84
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች የኃላፊነት ምደባ ሰጠ። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሪፎርሙን በሚመጥን መልኩ ሥራዎችን ለማስቀጠል እና በዘመነ መልኩ ማከናወን እንዲቻል ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች ከምክትል ፕሬዚደንት እስከ ዋና ክፍል የዕድገት፣ የዝውውር እና ክፍት ቦታዎች ላይ የኃላፊነት ምደባ በዋና መሥሪያ ቤት ሰጥቷል።   የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች ምደባ በሰጡበት ወቅት ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጥናት እና ምርምር ሥራዎች አስፈላጊ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ባለው መልኩ የበለጠ እንዲሻሻል ዛሬ የተመደቡ አመራሮች በቀጣይ በቁርጠኝነትና በትብብር ውጤታማ ሥራ መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።   ዩኒቨርሲቲውን በተሻለ አሠራር ለመቀየር ከብሔር፣ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከሌብነት በፀዳ መልኩ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ተወዳዳሪ የትምህርት ተቋም እንዲሆን ዕድሉ ያላችሁ እናንተ በመሆናችሁ የዩኒቨርስቲውን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ለሠራዊቱ መመኪያ፤ ለሀገራችን ኩራት የሚሆን የፖሊስ አካዳሚ ተቋም ለመገንባት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል። በፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች ተቋሙን የሚቀይሩ እና የሚያሻግሩ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን የሚያሳድጉ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከምክትል ፕሬዚዳንትነት እስከ ዋና ክፍል የኃላፊት ምደባ የተሰጣቸው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች በትምህርት ደረጃቸው፣ በፖሊሳዊ ስነ-ምግባራቸው፣ በሥራ አፈፃፀማቸው ልቀው የተገኙ መሆናቸውም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጌቱ ተ/ዮሐንስ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያካሄደ ያለውን ሪፎርም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ጠቅላይ መምሪያዎች መካከል ዩኒቨርሲቲው አንዱ መሆኑን ገልፀዋል። በትምህርትና ስልጠና፣ በጥናትና ምርምር፣ ማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የዕውቀት ማዕከል የመሆን ግብ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገራዊ የምክክር መድረክ ችግሮችን በውይይት በጋራ የመፍታት ባህልን ስለሚያጠናከር ለስኬታማነቱ መትጋት ያስፈልጋል--ምሁራን
May 13, 2024 128
ጂንካ፤ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፡-ሀገራዊ የምክክር መድረክ ችግሮችን ተነጋግሮ በጋራ የመፍታት ባህልን በማጠናከር ዴሞክራሲን ስለሚያጎለብት ለስኬታማነቱ መትጋት እንደሚያስፈልግ የወልዲያ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ። በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ተነጋግሮ ለማስወገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በጋራ መክሮ የመፍታት ባህልን በማጠናከር እንደ ሀገር ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሽሽጉ አቤ እንዳሉት፣ ብዘሃነትን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሁሉን ያሳተፈ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ ወሳኝ ነው። መድረኩ አካታች መሆኑ ለሁሉም የመደመጥ ዕድልና ዕውቅና ስለሚሰጥ ውይይትና ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል እየጎለበተ እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል። በየዘመናቱ ሲንከባለሉ የመጡ የህዝበ ጥያቄዎችና ቁርሾዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ እንዲያገኙና የዜጎችን አብሮነት ስለሚያጠናክር ለስኬታማነቱ በጋራ መትጋት እንዳለበት መክረዋል። እንደ መምህርና ተመራማሪ ሽሽጉ ገለጻ ህዝቡ በሰለጠነ መንገድ በችግሮቹ ላይ በጋራ እንዲመክር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ የዴሞክራሲ ስርአት መገለጫ ነው። በሂደት የዴሞክራሲ ባህልንም ስለሚያሳድግ ሀገራዊ ምክክሩ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ማበርከት አለብን ሲሉ ተናግረዋል። ሀገራዊ ምክክሩ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ጠባሳዎችን የመሻር አቅም እንዳለው የተናገሩት ደግሞ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ አያኖ ጉደኖ ናቸው። እንደ መምህሩ ገለጻ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቂምና ቁርሾዎችን በማስወገድ ዜጎችን ማቀራረብ ያስፈልጋል። ለዚህም አካታች ብሔራዊ የምክክር መድረክ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በሰለጠነ መንገድ ማካሄድ ይገባል ብለዋል። በችግር ውስጥ ሆነው ተቀራርቦ መወያየት ባለመቻላቸው ብቻ የፈረሱ ሀገራት እንዳሉም መምህር አያኖ አስታውሰዋል። የእነዚህ ሀገራት ዕጣ ፈንታ እንዳያጋጥም ሀገራዊ ምክክሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስዶ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መስራት አለብን ብለዋል። ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ምሁራን በጥናትና ምርምር የታገዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይኖርብናል ያሉት መምህርና ተመራማሪው፣ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ በመነሳት ስኬታማ መንገዶችን ማሳየት እንደሚገባም አመልክተዋል።  
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ ናቸው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን
May 13, 2024 113
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡ ኮሚሽኑ ዜጎች በአንጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት የመሳተፋቸው አስፈላጊነትን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በማብራሪያውም በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም ብሏል፡፡ ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው አስፈላጊነትና የሚያስገኛቸውን ውጤቶችንም በተመለከተ እንዲሁ፡፡ በዚህም አካታች የሆነ ውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም ገልጾ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ ከዜጎች የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያስችላል ንወ ያለው፡፡ በሂደቱም ሁላችንም ሀሳባችንን ለማቅረብ በንቃት መሳተፋችን ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ በሀገራችን ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለመጫወት በር ይከፍትልናል ብሏል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በዜጎች እና ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ የአጀንዳ ሀሳቦች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ስሜት እና ፍላጎት እንዲያንፀባርቁ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ መንገድ ከፋች ነውም ሲል ገልጿል፡፡ የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሀሳቦችን ለማስተጋባት መደላድል ይፈጥራል ብሏል፡፡ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው ሀሳባቸውን ማቅረባቸው በሀገራችን የዲሞክራሲ ልምምድ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል ሲልም አክሏል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ዜጎች ሀሳቦቻቸውን በቀጥታም ይሁን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሲያቀርቡ በሂደቱ ሊኖራቸው የሚገባው የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ መንገዱን ይጠርግላቸዋል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ ከዚህ ባሻገር በሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ዜጎች የጉዳዩ ማዕከል ሆነው በሀገራዊ ምክክሩ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማመንጨት ይችላሉ ብሏል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በእውነት እና በግልፅ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ማቅረባቸው የጋራ መተማመንን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲልም ገልጿል፡፡ በሂደቱም ሀሉም አካላት ካለፈው ተምረው ስለ ነገዋ የጋራ ሀገራቸው መክረው የማህበራዊ ውሎቻቸውን ያድሳሉ ብሏል ኮሚሽኑ በማብራሪያው፡፡ በመሆኑም በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን መፃኢ ተስፋ ላይ ጉልህ ሚና በሚኖረው በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ በመሆን ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማምጣት እንድንችል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪውን በታላቅ አክብሮት ያቀርባልም ብሏል፡፡ ኮሚሽኑ በመደበኛ መልክ አጀንዳዎችን የሚሰበስብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ቢነሳልኝ የሚሉትን አጀንዳ/ዎች በቡድን ወይም በግል በፖስታ ሳጥን ቁጥር፡ 32623 አዲስ አበባ በኢሜል፡ ethiopianndc@gmail.com በኮሚሽኑ ድረ-ገፅ፡ https://ethiondc.org.et በመጠቀም ማቅረብ እንደሚችሉም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ምስጋና አቀረበ
May 13, 2024 134
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ምሥጋና አቀረቡ። ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው የርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ሙሉ የምስጋና መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችውንና የተፈጥሮ ውበቷን የበለጠ ፍንትው አድርጎ በማውጣት የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን የወርቃማ ዕድል ባለቤት በሆነችው ጎርጎራ፤ ከብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ስለሀገር ክብርና ስለህዝብ ጥቅም በዝርዝር ከመከሩ በኋላ ግንቦት 4/2016 ዓ.ም የሁሉም ክልል ርዕሳነ - መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች በተገኙበት በውቢቷ ባህር ዳር ከተማ በመገኘት በዓለማች ትልቁ ወንዝ በሆነው አባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ መርቀው ስራ አስጀምረውልናል። ለዚህ በጎ ተግባርዎ፤ በክልላችን ህዝብ እና መንግስት ስም ምስጋናዬን በታላቅ አክብሮት አቀርባለሁ። በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለክልላችን ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም መረጋገጥ ይበጅ ዘንድ በታላቁ የአባይ ድልድይ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኛችሁ የአበረታታችሁን ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ስለአደረጋችሁልን ሁሉ እጅግ እናመሰግናለን። እጅግ ለተከበራችሁና እንግዳ ተቀባይነት መገለጫችሁ ለሆነው የባህር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በሙሉ በፀረ ሰላም ኃይሎች የነበረባችሁን ጫና ከምንም ሳትቆጥሩ በምረቃ ቦታው በመገኘት እና እንግዶችን በመቀበል ላሳያችሁት ፍቅርና አክብሮት በራሴና በክልላችን መንግስት ስም ከፍ ያለ ምስጋናየን አቀርባለሁ። የተከበራችሁ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ ዛሬ እንዳሳያችሁት አንድነትና ህብረት ሁሉ ከተማችን የበለጠ ሰላሟና ልማቷ እንዲረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት አመራሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እንድትሠሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በጫካ ለምትገኙ ወንድሞቻችንም በእውነት ከክልላችን ህዝብ ጥቅምና ክብር ውጭ ሌላ ስውር አጀንዳ ከሌላችሁ በስተቀር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባቀረቡላችሁ ጥሪ መሰረት ችግሮቻችንን በውይይትና በድርድር እንድንፈታና ህዝባችንም እፎይታ እንዲያገኝ በድጋሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። በመጨረሻም መላ የክልላችን ህዝብ በክልላችን የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም የበለጠ ስር እንዲሰድና የልማት ስራዎች ሳይስተጓጎሉ የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የማይተካ ሚናህን እንድትወጣ በድጋሚ ጥሪዬን በአክብሮት አቀርባለሁ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች የሚፈቱ ተግባራት ተከናውነዋል - ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን
May 12, 2024 121
አሶሳ ፤ግንቦት 04/2016 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ መንግስት ገለጸ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተለይም የክልሉን ሠላም ለማጽናት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡ በመልሶ ማቋቋም ረገድ በተደረገ ጥረትም በክልሉ ከቀያቸው ከተፈናቀሉት መካከል አብዛኞቹን ወደ መደበኛ ኑሯቸው መመለስ መቻሉን ገልጸዋል። በዚህም በተለያዩ ችግሮች ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩት ዜጎች ወደ ቀደመ የእርሻና ማዕድን ልማት የተለያዩ ስራቸው መሰማራታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎችን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከናወኑ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡ እነኚህን ጉዳዮች በ2016 በጀት ዓመት በእቅድ ለመመለስ የክልሉ መንግስት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አቶ አሻድሊ ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ የተበላሹ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን መልሶ መጠገን እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚገኝበት ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎችን የሚጠናክሩ የተቋረጡ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች መልሰው ግንባታቸው እንዲቀጥሉ ለፍጻሜ እንዲቃረቡ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ የአሶሳ ከተማ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ክረምት ሳይገባ ለማጠናቀቅ ግንባታውን በየጊዜው በመከታተል የሚደረግ ርብርብ መኖሩን አቶ አሻድሊ ጠቁመዋል፡፡ የገጠር መንገዶችን በመገንባት እና የተበላሹትን በመጠገን ስራ ላይም ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በተለይም ገበያን ለማረጋጋት የሸቀጣሸቀጥ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚደረግ ጥረት እንዳለ ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተው፤ አርሶ አደሩ በስፋት ወደ በጋ መስኖ እርሻ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የጓሮ አትክልት እና የተለያዩ ሰብሎችን በሺዎች ሄክታር ላይ በሁለት ዙር በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሽያጭ እንዲቀርብ በተደረገው ጥረት የተገኘውን ውጤት አቶ አሻድሊ አብራርተዋል፡፡ ይህም መተከል፣ ካማሽ እና አሶሳ ዞኖችን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መከናወኑን ጠቁመው፤ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማሳደግ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እያስቻለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት ይኸው የህዝቡን ጥያቄ የመመለስ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ አሻድሊ፤ ክፍተቶቻንን ማረም እና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ የማስቀጠል አቅጣጫ ተቀምጦ ስራው ቀጥሏል ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት አቅምን አሟጦ ገቢ መሰብሰብ፣ ንግድ እና ፍትሃዊ ግብይት ማጠናከር፣ የጤና እና ትምህርት አገልግሎትን ማሻሻልን ጨምሮ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ከሩብ ዓመቱ ዋና ዋና ትኩረቶች መካከል መሆናቸውን አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡      
የሽብርና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም በሚሞክሩ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል -የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
May 11, 2024 235
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሽብርና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም ሙከራ በሚያደርጉ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ። የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ በአዲስ አበባና አዋሳኝ አካባቢዎች የተከናወኑ የመረጃ ሥምሪቶችን ሪፖርት በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ቀርቦ ምክክር ተካሂዶበታል። በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንን ጨምሮ የፌዴራል የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል ።   በዚህ መድረክ፣ የፀረ ሰላም ኃይሎችን የተደራጀ ሤራና ሌሎችንም ሕገ ወጥ ተግባራትን በመከላከልና በማክሸፍ ረገድ ስኬት መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡ ይህም የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በመናበብና በተቀናጀ መንገድ ሥምሪት በማከናወናቸው የመጣ መሆኑ ተገልጿል። በተለይ በአማራ ክልል በፋኖ ስም ሲንቀሳቀስ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት እየደረሰበት ያለውን ጠንከር ያለ ምት መቋቋም አቅቶት ሲበታተን የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያው ለማድረግ በኅቡዕ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ የቡድኑን ሰንሰለት ለመበጣጠስ መቻሉን መረጃው ጠቁሟል፡፡   በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል እየሞከረ ባለው የሸኔ የሽብር ቡድን ላይ የተወሰደዉ ርምጃ የቡድኑን አከርካሪ በመስበር ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች እንደደረሰበት ተነግሯል። ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ትሥሥር ያላቸው ቡድኖች በአዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ ዝርፊያ፣ እገታና ሌሎች የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም በኅቡዕ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም፣ በጸጥታና ደኅንነት አካላት በተሠራ የተቀናጀ ክትትልና ኦፕሬሽን መክሸፉን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል። በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ174 በላይ ግለሰቦች ከተቀጣጣይ ፈንጂዎችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን አመልክቷል።   በተጨማሪም ሕዝብን በማማረር፣ በመመዝበርና ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመተባበር ተግባር የተሠማሩ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በባንኮች፣ በፍትሕ አካላትና በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ግለሰቦችን በመረጃ ሥምሪትና ክትትል በመለየት በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ የጋራ ኦፕሬሽኖች በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ በሽብር፣ በተደራጀ ስርቆት፣ በዝርፊያ እና በእገታ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሠማሩ የጥፋት ኃይሎችን አከርካሪ ለመስበር እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህም አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠርና ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲገባ ማገዙን ጠቁመዋል፡፡ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በውስጣቸው ያሉትን ክፍተቶችና ውሱንነቶች እያረሙ የላቀ የመፈጸም ዐቅም እንዲላበሱ የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ተመሳሳይ መድረኮችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በቀጣይም የተደራጁ ወንጀሎችን፣ ሽብርተኞችንና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በጥናት ላይ በመመሥረት ለመከላከል የሚያግዙ ሥምሪቶች እንደሚያከናውኑ በመድረኩ የገለጹት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው። አምባሳደር ሬድዋን እንዳሉት፦ ተልዕኮን በብቃት ለመወጣትና በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥሩ ሥጋቶችን ለማስወገድ በቅድሚያ ሁሉም ተቋም ራሱን እያበቃ፣ እየፈተሸ፣ እያጠራ የመሄድ አስፈላጊነት ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ መድረኩ በርካታ መልካም ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን፤ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ ራሳቸውን ከብልሹ አሠራር ለማጽዳት፤ የአባላቱን ሥነ ምግባር በቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የሕዝብ አለኝታነታቸውን ለማስቀጠል የጀመሩትን ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተባበረና በተናበበ አኳኋን ተመሳሳይ መድረኮችን ማካሄዳቸውን እንደሚቀጥሉ መጠቆማቸውን መረጃው አስታውቋል፡፡ በመረጃና በደኅንነት ተቋማት መካከል የሚደረገው የመረጃ ልውውጥና ሁለንተናዊ መደጋገፍ ሀገራዊ ሰላምንና ደኅንነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲመራ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንና ተመሳሳይ መድረኮችም እየተዘጋጁ አፈጻጸሞች እንደሚገመገሙ አምባሳደር ሬድዋን መናገራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ ያመለክታል።
በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ
May 11, 2024 353
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፦ በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ። ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር ወደ ኮርያ የዘመተችበትን 73ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብር ነው። በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ፣ የኮርያ ዘማች ቤተሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።   በኮርያ ሰላም ማስከበር ላይ ለተሳተፉ ዘማቾች ክብር መስጠትና ማመስገን ብሎም ታሪካቸውን መሰነድ ይኖርብናል ሲሉ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ለኮርያ ሰላም መረጋገጥ ያበረከተችው አስተዋፅኦ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናከረ እንደሆነም ተናግረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በወቅቱ ያበረከተችው ሚና የሀገራችንን ህዝቦች በጎነት ያሳየ መሆኑን አክለዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሰላም የከፈለችው ዋጋ የማይዘነጋ መሆኑን ገልፀው አመስግነዋል።   የተከፈለው ዋጋ በኢትዮጵያ እና በኮርያ መካካል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር መሠረት መጣሉን ተናግረዋል።   የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኮሌኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ኮሪያ የዘመቱበትን 73ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አክብረናል ብለዋል።
በምስራቅ ሸዋ ዞን በሊበን ጭቋላ ወረዳ የአሸባሪው ሸኔን ሁለት ሻምበሎች ከነ ሻምበል አዛዦቻቸው ተደመሰሱ
May 10, 2024 183
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ሸዋ ዞን በሊበን ጭቋላ ወረዳ የአሸባሪው ሸኔን ሁለት ሻምበሎች ከነ ሻምበል አዛዦቻቸው መደምሰሳቸውን የጉና ክፍለ ጦር አራተኛ ሬጅመንት አስታወቀ፡፡ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ወረዳ አዋሽ ወንዝን ተከትሎ ባሉ ቀበሌዎች እና በዝቋላ አቦ ተራራማና ጫካማ አካባቢ ተሰግስጎ የሽብር ሴራ ሲፈፅም የነበረው አሸባሪ ሃይል ከጥቅም ውጭ መደረጉ ተገልጿል። የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን አማረ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት መረጃ በመሰብሰብ እና በማጥናት እልህ አስጨራሽ ክትትል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ በዋለበት የማያድር፣ ባደረበትም የማይውል መሆኑ ለግዳጅ አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁመው ሠራዊቱ የጠላትን ስልት በማወቁና ጠላትን ለመምታት ካለው ቁርጠኝነት አንፃር በገባበት እየገባ መደምሰሱን ገልጸዋል።   መቶ አለቃ ደምስ ተሾመ በበኩላቸው በአካባቢው ተሰግስጎ የነበረው ጠላት አሰቃቂ የሽብር ሥራ ሲፈጽም እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ከመዝረፍና ከማገት ሌላ በዝቋላ አቦ ንፁሃንን ካለርህራሄ የገደለ ስብስብ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጭት ይዘን ወደ ግዳጅ በመግባት የጠላትን ሁለት ሻምበል ሙሉ በሙሉ ደምስሰናል ብለዋል። የጠላት ሻምበል አዛዦች ጃል ቦንሳ፣ ጃል ፈይሳ፣ ጃል መኪን የተባሉ አመራሮቹ መመታታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም 34 ክላሽ፣ 13 ኤስ ኬ ኤስ ኋላቀር መሳሪያ፣ ስምንት የተለያዩ ቦምቦች፣ 1 ሺህ 681 የክላሽ ጥይት፣ ትጥቆች እና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች መማረካቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ አገረ መንግስትን እውን ለማድረግ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ያለውን ትብብር  አጠናክሮ ይቀጥላል
May 10, 2024 126
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፡- የብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ አገረ መንግስትን እውን ለማድረግ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ፥ ፓርቲው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ነው ብለዋል። በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር እና አመራር በመፍጠር ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች መሻገር ተችሏል ነው ያሉት። የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የኢትዮጵያን የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትሐዊነትና የወንድማማችነት እሴቶች በሚያጎለብት መልኩ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለቀጣይ ትውልድ ጠንካራ ሀገር፣ ተዓማኒና ቅቡልነታቸው ያደገ ተቋማትን ለማስተላለፍም ፓርቲው ከፖለቲካና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።   የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሙሳ ፍሮ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ጠቅሰው ለውጡ ፈተናዎች ያጋጠሙበትና በድል የተሻገርንበት ነው ብለዋል። በተለይም የአስተሳሰብ ፅንፈኝነትን የሚያራምዱ ቡድኖች በክልሉ ለውጡን ለመቀልበስ ቢሞክሩም አመራሩና ህዝቡ በመቀናጀት የጠላትን ሴራ መቀልበሱን ጠቁመዋል። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤት ማዕቀፍ በክልሉና በሀገር የሰላም፣ የልማትና የህዝብ ጥቅም ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሀገርን ልዕልናን ከፍ ለማድረግና ህዝባዊ አንድነትን ለማስቀጠልም ፅንፈኝነትን በፅኑ የሚታገል አመራር ወሳኝ በመሆኑ ፓርቲው ውስጡን እያጠራ ችግር ያለባቸው አመራርና አባላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው ብለዋል።   በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ነኢማ ሙኒር ለተሻለች ሀገር ግንባታ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የትብብር ስራ እንዲዳብር በጋራ ምክር ቤቶች ውይይት በማድረግ አመርቂ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ለመውሰድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የማህበራት፣ የፌዴሬሽኖች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሚና ቀላል አይደለም ነው ያሉት።   የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሀሰን አብዲ፥ ለረጅም ጊዜ በክልሎች ተወስኖ የቆየውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እስከ ወረዳ ድረስ በማዋቀር ለህዝብ ጥቅም ሁሉም በጋራ እየተረባረበ ነው ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫ ሰሞን ብቻ ከሚያደርጓቸው ክርክር እና ውይይቶች ባሻገር በዘላቂነት በሀገር ሰላምና ልማት ዙሪያ ተቀራርበው እንዲሰሩ ሰፊ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።   በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ግርማ ባሻ ፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ መስክ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በፓርቲው የተጠኑ ስትራቴጂካዊና ወሳኝ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ለሀገር እድገትና ልዕልና መረጋገጥ እንዲሁም ለሰላም መፅናት የአጭርና የረጅም ጊዜ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ሲሆን ሁሉም አካላት ይህን ጥረት ሊደግፉ ይገባል ነው ያሉት።      
የአማራ ክልል ህዝብ ሰላም በማረጋገጥ መደበኛ ሥራውን እየመራ መሆኑን ተመልክተናል - የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች
May 10, 2024 143
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ህዝብ በአብዛኛው ሰላሙን በማረጋገጥ ልማትና መደበኛ ስራውን እየመራ መሆኑን መመልከታቸውን የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ። የፓርቲ አመራሮቹ ጎንደር ከተማ ሰላማዊ መሆኗን ያለምንም ስጋት ከተማዋን ተዘዋውረን በመጎብኘት አረጋግጠናል ብለዋል። የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በጎንደር ከተማ ዘጠኝ ወራት የፓርቲውን የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አፈጻጸም ገምግመዋል። የተለያዩ ክልሎች የፓርቲው አመራሮች እንዳሉት÷ ወደ ጎንደር ከመምጣታቸው አስቀድሞ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡ መረጃዎች የከተማዋን ገፅታ የማይመጥኑና አካባቢው ሰላም እንዳልሆነ የሚያስመስሉ ነበሩ። ጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ ጊዜ ጀምሮ የከተማዋ ድባብ ፍጹም ሰላማዊና የህዝቡ እንቅስቃሴም መደበኛና ሞቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ሀሰተኛ መረጃና መሬት ላይ ያለው እውነታ ለየቅል መሆኑንን ያሳያል ነው ያሉት። የክልሉና የከተማዋ አመራር፣ የፀጥታ ኃይሎች እና ህዝቡ የፅንፈኞችን እኩይ ተግባር በማክሸፍ ሰላምን ማስፈናቸውን በአካል ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል። በጎንደር ከተማ ማህበረሰቡ በንግድ፣ በአገልግሎትና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፤ በሩቅ የሚሰማው ግን ከዚህ ተቃራኒ እንደነበር አውስተዋል። ስለ አማራ ክልል የሰላም ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገበውና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ ነው ያሉት አመራሮቹ፥ አካባቢው ሰላማዊ ህዝቡም የዕለት ተዕለት ህይወቱን እየመራ ነው ብለዋል። የከተማዋ ህዝብ እና አመራር በቆይታቸው ላደረጉላቸው ደማቅ እንግዳ ተቀባይነት አመስግነው፥ በቀጣይ ወደየክልላቸው ሲመለሱም የአማራ ክልል በአብዛኛው ሰላም እንደሆነ የግንዛቤ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም