በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፦ በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር ወደ ኮርያ የዘመተችበትን 73ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብር ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ፣ የኮርያ ዘማች ቤተሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኮርያ ሰላም ማስከበር ላይ ለተሳተፉ ዘማቾች ክብር መስጠትና ማመስገን ብሎም ታሪካቸውን መሰነድ ይኖርብናል ሲሉ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለኮርያ ሰላም መረጋገጥ ያበረከተችው አስተዋፅኦ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናከረ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በወቅቱ ያበረከተችው ሚና የሀገራችንን ህዝቦች በጎነት ያሳየ መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሰላም የከፈለችው ዋጋ የማይዘነጋ መሆኑን ገልፀው አመስግነዋል።
የተከፈለው ዋጋ በኢትዮጵያ እና በኮርያ መካካል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር መሠረት መጣሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኮሌኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ኮሪያ የዘመቱበትን 73ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አክብረናል ብለዋል።