ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ህብረት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ህብረት ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጽጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ተግባራዊ የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ባንኮሌ የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም የታጠቁ ኃይሎችን ትጠቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ሂደት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ከሰላም ፈንድ ቋቱ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ማዕቀፍ የመጀመርያዋ ተጠቃሚ አባል አገር መሆኗን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ህብረቱ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ማሰማራቱ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነቱን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
አክለውም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ የማዳበርና ማስፈጸም ስራዎችም ህብረቱ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ወሳኝ በሆኑ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ባንኮሌ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስፈን ጥረቶች ውስጥ ወሳኝና ውጤታማ አገር እንደሆነች ተናግረው ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚሻ አንስተዋል።