ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ የተቀናጀ አመራር በመስጠት ሁለንተናዊ የልማት ስኬት ተመዝግቧል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ የተቀናጀ አመራር በመስጠት ሁለንተናዊ የልማት ስኬት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማው በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦችን አንስቶ መምከሩ ይታወቃል።

በመድረኩ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ግጭቶችን ማስቀረት ብልጽግናን ማጽናት "በሚል ርዕስ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም ግጭት የብልጽግና ሳንካ በመሆኑ መቀነስና ማስቀረት በሚቻልበት ልክ በመሥራት ሰላምን ማስፈን ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በለውጥ ውስጥ የሚያጋጥም አለመረጋጋት ወደ ውድቀት እንዳይወስድ አለመረጋጋትን መግታት የሚችል ዕድገት መፍጠርና ወደ ሁለንተናዊ ውህደት መሻገር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ለዚህም ጠቃሚ ሀሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም፣ የልማትና ጠንካራ ተቋማት የመገንባት ሀሳቦች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

በዚህ ረገድ ማነቆዎችን እየፈታን በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ኢትዮጵያ ስኬትን ያስቀጠለ ብልጽግናን ያስቻለ ጉዞ ውስጥ መሆኗን ገልፀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በሃሳብ ልዕልና ብቻ መዳኘት የሚፈልግ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የሕዝብ ውይይቶች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ሰላምን ለማረጋገጥ በተከታታይ በተሰሩ ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በክልሉ ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በአገልግሎት አሰጣጥና የልማት ሥራዎች ላይ እንከን ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በክልሉ የጥፋት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል ሕብረተሰቡን በማደናገር ለማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቀውሶች መዳረጉን ጠቅሰዋል።

በተለይም የግብርና እና ኢንቨስትመንት ሥራን ማስተጓጎሉን አስታውሰው፤ መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር በመግባቱ ችግሩ እየተፈታ መሄዱን ገልፀዋል።

የክልሉ መንግሥት የአሰራር ለውጥና የተቀናጀ አሠራር በመፍጠር የልማትና የሕዝብ አገልግሎቶች በተሳካ መልኩ እንዲቀጥሉ ማድረጉን አንስተዋል።

በመሆኑም በክልሉ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሄደበት ርቀት የተሳካ መሆኑን አስታውሰው፤ ይኸው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም