ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች የኃላፊነት ምደባ ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች የኃላፊነት ምደባ ሰጠ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሪፎርሙን በሚመጥን መልኩ ሥራዎችን ለማስቀጠል እና በዘመነ መልኩ ማከናወን እንዲቻል ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች ከምክትል ፕሬዚደንት እስከ ዋና ክፍል የዕድገት፣ የዝውውር እና ክፍት ቦታዎች ላይ የኃላፊነት ምደባ በዋና መሥሪያ ቤት ሰጥቷል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች ምደባ በሰጡበት ወቅት ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጥናት እና ምርምር ሥራዎች አስፈላጊ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ባለው መልኩ የበለጠ እንዲሻሻል ዛሬ የተመደቡ አመራሮች በቀጣይ በቁርጠኝነትና በትብብር ውጤታማ ሥራ መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል። 


 

ዩኒቨርሲቲውን በተሻለ አሠራር ለመቀየር ከብሔር፣ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከሌብነት በፀዳ መልኩ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ተወዳዳሪ የትምህርት ተቋም እንዲሆን ዕድሉ ያላችሁ እናንተ በመሆናችሁ የዩኒቨርስቲውን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ለሠራዊቱ መመኪያ፤ ለሀገራችን ኩራት የሚሆን የፖሊስ አካዳሚ ተቋም ለመገንባት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

በፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች ተቋሙን የሚቀይሩ እና የሚያሻግሩ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን የሚያሳድጉ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከምክትል ፕሬዚዳንትነት እስከ ዋና ክፍል የኃላፊት ምደባ የተሰጣቸው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መኮንኖች በትምህርት ደረጃቸው፣ በፖሊሳዊ ስነ-ምግባራቸው፣ በሥራ አፈፃፀማቸው ልቀው የተገኙ መሆናቸውም ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጌቱ ተ/ዮሐንስ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያካሄደ ያለውን ሪፎርም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ጠቅላይ መምሪያዎች መካከል ዩኒቨርሲቲው አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

በትምህርትና ስልጠና፣ በጥናትና ምርምር፣ ማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የዕውቀት ማዕከል የመሆን ግብ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም