መጣጥፍ - ኢዜአ አማርኛ
መጣጥፍ
ከሮም እስከ አዲስ አበባ
Jul 11, 2025 74
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ይካሔዳል። የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ፣ የምግብ ስርዓት ሽግግር ሁለንተናዊነትና የተገቡ ቃሎችን ከመፈጸም አንጻር ያለውን የተጠያቂነት ስርዓት ማጠናከር ጉባኤው ትኩረት ያሚያደርግባቸው ሀሳቦች ናቸው። ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተምግብ ጉባኤ በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በጣልያን ሮም የተካሄደው የመጀመሪያ የተመድ ስርዓት ምግብ ላይ የተገቡ ቃሎች ትግበራ ሂደትን መነሻ በማድረግ የሚካሄድ ነው። በመጀመሪያው ጉባኤ ላይ የ182 ሀገራት ተወካዮች፣ 21 የሀገራት መሪዎች እና 126 ሚኒስትሮችን ጨምሮ 3 ሺህ 300 ተሳታፊዎች ታድመውበታል። በጉባኤው ላይ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሀገራት እና ተቋማት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ስድስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርገው ነበር። የምግብ ስርዓት ስትራቴጂዎችን ከብሄራዊ ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር፣ ሁሉን አቀፍ የምግብ ስርዓት አስተዳደር መገንባት፣ በጥናት፣ ዳታ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፣ ሁሉን አቀፍ የእቅድ ዝግጅት እና ትግበራን ማጠናከር፣ በምግብ ስርዓት ውስጥ የንግዱ ማህበረሰብ ያለውን ድርሻ ማሳደግ እና የአጭርና የረጅም ጊዜ የአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ። ኢንቨስትመንት፣ የበጀት ድጋፍ እና የእዳ አስተዳደር ሌላኛው የትኩረት መስክ ነው። በጉባኤው ላይ 300 ገደማ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የምግብ ስርዓት ሽግግርን እውን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በተለይም እ.አ.አ 2030 የማይበገር፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የምግብ ስርዓት መገንባት እንዲሁም ምግብ ለሁሉም የሚለውን ግብ ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርጉ ሀገራት ቃል ገብተዋል። ሁሉን አሳታፊ ነው በሚል አድናቆት ያገኘው ጉባኤው በስርዓት ምግብ ላይ ግንዛቤን ከማሳደግ እና አቅምን ከመገንባት አንጻር ውጤታማ እንደነበር ይነሳል። የምግብ ስርዓት ሽግግር አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ እንደሆነም በጉባኤው ተወስቷል። ኢትዮጵያም በስርዓተ-ምግብ ጉባኤው ላይ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ ነበር። በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ልምደችን አቅርባለች። በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና በስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማምጣት እየወሰደች ባለው የፖሊሲ እርምጃና ውጤቶች ዙሪያ ገለጻ አድርገውም ነበር። ኢትዮጵያ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ለየስነ ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን፣ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል። በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርት እና በሌማት ትሩፋት እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ለጉባኤው አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታታትም ሆነ በስርዓተ-ምግብ ሽግግር ለማድረግ አዲስና የተለየ የፋይናንስ ሞዴል ያስፋልጋል በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል። ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግር አቅጣጫዎች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም በፋይናንስ አቅርቦት፣ በዓለም አቀፍ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም በትብብር በመስራት በኩል በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የገለጹት። በመሆኑም ሀገሮች በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአነስተኛ እርሻ ስር-ነቀል ለውጥ በማምጣት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንኦት አንስተዋል። ለዚህም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እንዲያሳድጉና ለግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል ። ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ-ምግብ ጉባኤ የመጀመሪያውን ጉባኤ መነሻ በማድረግ በተለያዩ አጀንዳዎች ይመክራል። ቀዳሚ ትኩረቱ ከመጀመሪያው ጉባኤው በኋላ የምግብ ስርዓትን አስመለክቶ ያሉ ለውጦች ምንድን ናቸው? የሚለው ነው። በጉባኤው ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ ያገኟቸውን ስኬቶች እና የጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ። በተለይም የምግብ ስርዓት ሽግግሩ ሁለንተናዊነት እና ሁሉን አሳታፊነት ዋንኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሁለተኛው የጉባኤው አጀንዳ በመንግስታት፣ የምግብ አምራቾች፣ የንግድ ማህበረሰቡ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር ነው። የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው ታምኖበታል። በተጨማሪም ሀገራት እና ተቋማት በሮሙ ጉባኤ የገቧቸው ቃሎች የደረሱበትን ደረጃ የሚገመገም ሲሆን ቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል። ለምግብ ስርዓት ሽግግር የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት እና የኢንቨስትመንት መጠንን መጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ጉባኤው ይመክራል። ለምግብ ስርዓት ሽግግር ስራዎች በአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ፣ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም እና ሀገር በቀል የፋይናንስ መሰብሰብ አቅምን ማጎልበት ላይ ምክክሮች ይደረጋሉ ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በሮም በነበረው ጉባኤው ላይ ይፋ ያደረጓቸው ስድስት የትኩረት መስኮች አፈጻጸም ግምገማ ሌላኛው አጀንዳ ነው። በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አርሶ አደሮች፣ አምራቾች እና የምግብ ስርዓት ሽግግር ተዋንያንን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው። በጉባኤው ላይ ከዋናው ሁነት ጎን ለጎን የምግብ ስርዓት ትራስፎርሜሽን እና የስርዓተ ምግብ ሽግግርን አስመልክቶ በርካታ የጎንዮሽ ስብስባዎች ይደረጋሉ። ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ሽግግር ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶም በጉባኤው ተሳታፊዎች የመስክ ምልከታ ይደረጋል። ኢትዮጵያ በስርዓት ምግብ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በግብርናው ዘርፍ ባደረጋቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ጉባኤውን እንድታስተናግድ የተመረጥችባቸው ምክንያቶች ናቸው። ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ሽግግር እየተወጣች ያለው የመሪነት ሚና እና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗ ተመድ ዓለም አቀፉን ከፍተኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ የማስገንዘብ ስራ ታከናውናለች። ተባባሪ አዘጋጇ ጣልያን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በምግብ ስርዓት ሽግግር ውጤታማ ተሞክሮ ያላት ሀገር ናት። የደቡብ አውሮፓዊቷ ሀገር ከኢትዮዮጵያ ጋር በመሆን ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን እየሰራችም ትገኛለች። ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ተሳታፊዎች ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እየጠበቀች ትገኛለች።
በቻይና ይህም አለ!
Jul 8, 2025 219
በአብነት ታደሰ በርግጥ ከዓለማችን የጥንት ስልጣኔ ምድሮች አንዷ ናት- ቻይና። በታሪክ ገጾች ‘የግኝት ምድር’(Land of Invention) የሚል ተቀፅላ የሰፈረላት የሺህ ዘመናት ባለታሪክ ሀገር። የጥንት ቻይኖች አያሌ ‘ግኝቶችን’ ለዓለም አካፍለዋል። ወረቀት ፈብርከው ዘመናቸውን ጽፈዋል፣ ማተሚያ ቁስ ፈጥረው አትመዋል፤ ኮምፓስ ፈልስመው አቅጣጫ ጠቁመዋል።በ221 ዓመተ-ዓለም አንድ ወጥ ስርወ መንግስት መስርተው በሀገረ መንግስት የታሪክ ዑደት ከፍታንም ዝቅታንም አይተዋል። በቻይና አያሌ ስርወ መንግስታት ተፈራርቀዋል። ቻይናውያን ክፉውንም ደጉንም ችለው አልፋዋል። የሕዝቡ ጽናት፣ ጥበብ፣ ቱባ ባህል፣ ታሪክና ብልሃት በቻይና ግንብ ይመሰላል። ግንቡም ዝም ብሎ የጡብ ክምር አይደለም፤ የመሰረተ-ጽኑነታቸው ትዕምርት(symbol) እንጂ። ሲሶውን ሕዝቧ በያንግትዝ ወንዝ ተፋሰስ ጉያ አቅፋ፣ ጥንተ ማንነቷን ሸክፋ ዕልፍ ዘመናትን ተሻግራለች። የቻይና ስርወ መንግስታት ከስመው የዛሬዋ ኮሚኒስት ሪፐብሊክ ቻይና ከተመሰረተች ገና አንድ ምዕተ ዓመቷ ነው። ቅድመ ልደተ ክርስቶት በ221 ዓመተ-ዓለም የተመሰረተው ወጥ-ስርዎ መንግስት በመልከ ብዙ ምክንያቶች ተዳከመ። በፈረንጆቹ 1912 የመጨረሻው የቻይና ስርዎ መንግስት ተንኮታኮተ። ዘመናዊቷ የቻይና ሪፐብሊክ በዚህ ዘመን ተመሰረተች። ዳሩ ለውጡ አልጋ በአልጋ አልሆነም። ለሺህ ዘመን የጽኑ ስርዓተ መንግስት ባለቤቷ ሀገር ቻይና በአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ታመሰች። ወረራንም፣ ዕልቂትንም አስተናገደች። በዘመኑ ማኦ ዘዶንግ የሚባል ባለራዕይ መሪ በቻይና ምድር ተነሳ። አርቆ አሰበ፤ ሀሳቡንም አሰረጸ፤ በዓላማ ጸንቶ ክፉ ዘመን ተሻገረ። ማኦ እና ተከታዮቹ ለቻይና ትንሳኤ ታተሩ። በጽናት ታገሉ። ለመስዕዋትነት ቆርጠው ተነሱ፤ ዋጋም ከፈሉ። በአውሮፓዊኑ ዘመን አቆጣጣር በ1949 የዛሬዋን የቻይና ሕዝባዊ ኮሚኒስት ሪፐብሊክ መሰረተ። ሃሳቡን ወደ ፖሊሲ ቀየረ፤ ተገበረውም። ቻይናን በኢንዱስትሪና ግብርና ምርት በንቅናቄ የማስፈንጠር ፕሮግራምንም (Great Leap Forward) ገቢራዊ አደረገ። ሆኖም ፖሊሲው በአንዴ ፍሬ አላፈራም። በወቅቱ በተፈጥሯዊና በሌሎች ምክንያቶች ቻይና በረሀብ ጠኔ ተመታች። ቻይናዊያን ተራቡ፤ ጎረቤት ሀገራትን ደጅ ጠኑ፤ ታላቁን ረሀብ መሻገር ያልቻሉ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናዊያን በረሀብ አለቁ። በቻንግሻ የሚገኘው የማኦ ዘዶንግ ግዙፍ ሐውልት መራራ ጽዋን ተጎነጩ። የሀገሪቷ መሪ ማኦ ዘዶንግ በወቅቱ ፈተና ተስፋ ሳይቆርጥ ሀገር አሻጋሪ ፖሊሲውን ገቢራዊ አደረገ። ልመናን ለትውልድ ላለማውረስ፣ ንቅዘትን(ሙስናን) ነውር የሚያደርግ ስርዓት አጸና። ስራን ወንጌል፤ ሙስናን ወንጀል ያደረገ ጽኑ ስርዓተ መንግስት ገነባ። ከራሷ አልፋ ለዓለም የተረፈችዋን የዛሬዋን ቻይና በጽኑ መሰረት ላይ አነበረ። የዛሬዋ ቻይና ከዓለማችን ቁንጮ ልዕለ ሃያል ሀገራት አንዷ ናት። ከራሷ አልፋ ለዓለም ተርፋለች፤ የቻይና ቴክኖሎጂ ምጥቀትና ርቀት ዓለም ጉድ አሰኝቷል። በቅርቡ ሀገረ ቻይናን ከጎበኙ ጋዜጠኞች አንዷ ሆኜ ‘መልክዓ ቻይና’ን በወፍ በረር ቃኘሁ። በዚህ ማስታወሻዬ በቻይና የቴክኖሎጂ ልህቀትና ምጥቀት ላይ ብቻ አተኩራለሁ። ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ባላት፣ በ14 ሀገራት በምትዋሰነው፣ በአንድ ኮሚኒስት ፓርቲ በምትመራው ሀገር ቻይና በነበረኝ የ15 ቀናት ቆይታ ቻይና እንደ ጥንተ ታሪኳ ሁሉ በዘመኑ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ላይ ያላትን የመራቀቅ ጥግ ታዘብኩ። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን የመቅደም እሽቅድድሟ ‘አጃይብ’ ያሰኛል። በሀገሪቷ ርዕሰ መዲና ቤጂንግ እና በማዕከላዊ ቻይዋ በምትገኘው የሁናን ግዛት ዋና ከተማ ቻንግሻ ምልከታዬ ቻይና ’ከተባለላት በላይ’ የቴክኖሎጂ ምጥቀቷ አስደንቆኛል። ምናልባትም የመጀመሪያ ጉዞዬ መሆኑም ነገሩን በአንክሮት እንድመለከት ሳያስገድደኝ አልቀረም። የሀገሪቷ ርዕሰ መዲና ቤጂንግ እና ጥንታዊቷ ቻንግሻ ከ22 ሚለዮን የሚልቅ ህዝብ በጉያዋ የታቀፈችው ታላቋ ቤጂንግ ከተማ ከዓለማችን ግንባር ቀደም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ማዕከላት አንዷ ናት። የአዲስ አበባ እህት ከተማ በዚህ ወቅት ሞቃታማ አየር ጸባት አላት። ቤጂንግ የ21ኛው ክፍል ዘመን የኪነ ህንፃና ክትመት ቴክኖሎጂ ያበበች ብቻ አይደለችም፤ ይልቁኑም በዛፎች ሀመልማላዊ ገጽታ የተላበሰች ውብ መዲና እንጂ። በሕንፃዎችም፣ በዛፎችም የተደነነች ከተማ። በተፈጥሮ የበቀሉ የሚመስሉ ሰማይ ታካኪ ሕንጻዎች፤ የመንገድ መሰረተ ልማት ስፋት፣ ጽዳትና ጥራት ‘ኩልል’ ያለች፣ ‘ምልል’ የምታደርግ ከተማ ያደርጋታል። ቤጂንግ ከተማ ከዘመናችን አስደናቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ በሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት(አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሕይወትና ኑሮን እንዴት እንዳቃለለ የቤጂንግ የዕለት ከዕለት ክዋኔ ሁነኛ ማሳያ ነው። ቻይኖች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጠበዋል፤ መጠበብ ብቻም ሳይሆን ኑባሬያቸውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት መር አድርገዋል። ከሮቦት መስተንግዶ እስከ ሰው ሰራሽ ፀሐይ መራቀቅ ይስተዋላል። ካረፍኩበት ሆቴል (15ኛ ወለል ላይ ከሚገኘው መኝታ ክፍሌ) ሆኜ ያዘዝኩት ምግብ በቅጽበት አስተናጋጇ ‘ከች’ ብላ ትደውላለች። ፍጥነቷ ስትገረም፤ አስተናጋጆች ሮቦቶች መሆናቸውን ስትመለከት ይበልጥ ትደነቃለለህ። በክፍሌ ውስጥ ማብሪያ ማጥፊያ ስጫን መጋረጃው ሲከፈት መደንገጤን አልሸሽግም፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት ፀሐይ አለመጥለቋን ስመለከት ‘የቻይና ሰው ሰራሽ ፀሐይ ወጣች እንዴ?’ ማለቴ አልቀረም። በነገራችን ላይ የቻይና የሰው ሰራሽ ፀሐይ ሳይንሳዊ ፈጠራ ሁለት ግዜ ተሞክሮ ያለምንም እንከን እንደሚሰራ ነግረውናል። የሰው ሰራሽ ፀሐዩ ሃይድሮጅን እና ዱተሪየም ጋዞችን እንደ ሀይል ማመንጫ ነዳጅነት በመጠቀም ንጹህ ኢነርጂን ለማመንጨት ታስቦ ዲዛይን እንደተደረገና ሰው ሰራሽ ፀሐይ በርሐን ከተፈጥሮ ፀሐይ 13 እጥፍ ያክል ሙቀት እንደሚያመነጭም ሰምተን ተደንቀናል። የቻይና ሰው ሰራሽ ፀሐይ ፕሮጀክት የሥራ ሰዓትን ከ13 ሰዓት ወደ 24 ሰዓት ለመጨመርና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ የሰነቀ ነው። በቻይና በሰዉ ቅርፅ የተሰሩ ሮቦቶች በእግር ኳስ ጨዋታዎች ተወዳጅነት አትርፈዋል። ቤጂንግ የሚገኘው ሂዩማኖይድ የተሰኘ የሮቦት ቡድን የሰራቸው ሮቦቶች አመርቂ ውጤት ከራቀው የሀገሪቷ እግር ኳስ ቡድን ይልቅ የሀገሬውን ቀልብ እንደሳቡ ይነገራል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት በታገዘ የሮቦቶች ውድድር አያሌ ቻይናዊያን ይታደማሉ። ሮቦቶቹ በጨዋታ መሐል ቢወድቁ በራሳቸውን ይነሳሉ፤ ቢጎዱም ከሜዳ የሚወጡበት ስርዓት ተዘርግቷል። የታላቋ ቻይና ሰዎች ቴክኖሎጂን ከችግር መፍቻነት ወደ መዝናኛነትም አልቀውታል። በሀገራችን እንደ አዲስ ቴክኖሎጂ በንግዱ ስርዓት ውስጥ እየተዋወቀ ያለው የፈጣን ምላሽ መለያ ወይም ኪው አር ኮድ(Quick Response code) በቻይና ዕለታዊ ከዋኔዎች ቅንጦት አይደለም። በቻይና ማንኛውም ግልጋሎት በዚህ በዲጂታል ስርዓት ይከወናል። እንደሌሎች ስልጡን ሀገራት ሁሉ በንክኪ የሚደረግ ገንዘብ ዝውውር ቀርቷል። በቤጂንግ ጎዳናዎች በኪው አር ኮድ(QR Code) በሚንቀሳቀሱ ሞተር ሳይክሎችን በየመንገዱ ተሰድረዋል፤ የፈለገ መንገደኛ ሳይክሎችን በመጠቀም ወደ ፈለገበት ስፍራ ተንቀሳቅሶ ክፍያውን በኪው አር ኮድ ከፍሎ ይሄዳል። ሌላውም እንዲሁ። በአዲስ አበባ መኖሪያ ሰፈሬ የነበሩ ሳይክሎኝ ከደጃችን ደብዛቸው እንደጠፋ ሳስብ በቻይኖች ብልሃት፣ ታማኝነትና የከተሜነት ልህቀት ቀናሁ። በርግጥ በቻይና ኪው አር(QR) ኮድ ለተገለገልንበት መክፈያ ብቻ ሳይሆን ለልመናም መዋሉን ሲመለከቱ ፈገግ ሊሉ ይችላሉ። በቻይና ይህም አለ በማለት። በርግጥ በቤጂንግ የሰው እጅ ከሚያይ ይልቅ ጆሮቸውን ቢቆጥርጣቸው የሚሰሙ የማይመስሉ አዛውንቶች ሳይቀር በስራ ላይ ተጠምደው ይስተዋላሉ። ከቻይናውያን ጋር ለመግባባት በተለይም በንግድ ማዕከላት የቻይንኛ ቋንቋ መረዳት ግድ ይላል። “ሃው ማቺ፣ ጉዳ ጉዳ፤ ሺሼ፣ ኢ፣ አር…” እና መሰል ቃላት ማወቅ ይበጃል። ከዚህ ባለፈ በምልክት መግባባት አልያም በቋንቋ ተርጓሚ መተግበሪያ መጠቀም ያሻል። የቻይና ሰራሽ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርቶች በራሳቸው ብራንድ፣ ቋንቋና መልክ እየተመረቱ በተመጣጣሽ ዋጋ ለህዝቦቿ ተደራሽ እየተደረጉ ነው። የቻይና የራስ-በቅነት ጥረት ያስቀናል። በቴክኖሎጂ፣ በባሕልና በኢኮኖሚ ተጽዕኖ ተላቀው በራሳቸው ለመቆም የሄዱበት ርቀት ግሩም ነው። ግብይቶች በራሳቸው ገንዘብ ብቻ ይከወናል። በወቅቱ ምንዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር ሰባት የቻይና ገንዘብ(ዩዋን) ነው። ከምዕራባዊያን ማህበራዊ ትስስር ገጾች(ለምሳሌ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ) በሕግ በማገድ የራሳቸውን መተግበሪያ አበልጽገው ገቢራዊ አድርገዋል። ‘ዊቻት’ የተሰኘው መተግበሪያ ሁሉም ቻይናውያን መገልገያ ነው። ከቤጂንግ ሌላ ያስደነቀችኝ ጥንታዊቷ ቻንግሻ ከተማ ነች። ቻንግሻ ስመ-ብዙ ነች። ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ጠገቧ የሁናን ግዛት ርዕሰ መዲና ቻንግሻ ‘የከዋክብት ከተማ’ ትሰኛለች። በነገራችን ላይ ማኦ ዘዶንግ ትውልዱ ሁናን ግዛት ውስጥ ነው። ቻንግሻ በስራ ከተማነቷ ‘የማታንቀላፋው መዲና’ ትባላለች። በመዝናኛ ስፍራነቷ ‘የተዝናኖት መነሃሪያ’ የሚል ተቀጥላ ስም አላት። ‘የሚዲያ ጥበብ’ ስፍራም ትሰኛለች። በኢንዱስትሪ፣ በጥንታዊ ሐውልቶች፣ አብያተ መቅደሶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎች መገኛ በመሆኗ በቱሪስቶች ተወዳጅ ከተማ ናት። ትናንትና ዛሬን ያዋደደች፣ ታሪክና ባህል ባዛነቀችዋ ቻንግሻ የአምስት ቀናት ቆይታዬ ብዙ ገጽታዋ አስደምሞኛል። የሻንግ ወንዝን ተንተርሳ፣ በተራራማ፣ በሜዳማና ኮረብታማ መልክዓ ምድር በማዛነቅ የተቆረቆረች በመሆኗ የስብት ማዕከል ሆናለች። እንደ ቤጂንግ በደን የተከበበች፣ በዘመነኛ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እና በታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎች የተጌጠች ከተማ ናት። ከዚህ ባሻገር የአምራች ኢንዱስትሪዎች መናገሻም ናት። የምቹ ከተሜነትና ጠንካራ የስራ ባህል በግላጭ የሚስተዋልባት ከተማ። የዓለማችን ገዙፉ በጣም ሞቃታማ አየር ጸባይ ባላት ቻንግሻ ሌት ከቀን ይሰራል። ፋብሪካዎቿ አይተኙም። ሌትና ቀኑ የሚታወቀው በሰዓት ብቻ እንጂ የስራና የንግድ ድባቡ እኩል ነው። ብርሃናማዋ ቻንግሻ ‘የቻይዊያን መስቀል’ በተሰኘው በቀይ በተቀለመው መስቀልም ትታወቃለች። በርግጥ ከዓለማችን ግዙፍ ማማዎች አንዱ የሆነው ሕንጻም መገኛ ናች። በጥቅሉ የቻይና ጉብኝት ትዝብቴ የገናና ታሪክ ባለቤቷ ሀገር ከባድ ውጣ ውረዶችን አልፋ ዛሬ ዓለምን እየቀደመች መሆኑን ሳስብ፤ እንደቻይና ሁሉ የሺ ዘመናት ገናና ታሪክና አኩሪ ገድል ያላት ኢትዮጵያስ የሚል ተጠየቅ እንዳውጠነጥን አድርጎኛል። ቻይናዊያን የዘመን የፈተና ቋጠሮዎቻቸውን ፈታተው ከዛሬ ከፍታ ሰገነት ላይ ወጥተዋል። ከዛሬም በበለጠ ነገን በጽኑ መሰረት ላይ እየገነቡ ነው። እኛስ? ብዬ ሳስብ በቁጭትና በተስፋ ተዋጥኩ! ሰላም!
በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ምን አሉ?
Jul 7, 2025 163
በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ምን አሉ? 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ እየተካሄደ ይገኛል ጉባኤው እየተካሄደ የሚገኘው “ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የደቡብ ንፍቀ ዓለም” በሚል መሪ ሀሳብ ነው። በጉባኤው ላይ ተሳታፊ የሆኑ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በዓለም አንገብጋቢ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል። ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት በሚያስችል ሁኔታ አፋጣኝ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው። በብሪክስ አዳዲስ አባላት መጨመራቸው የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ አላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል። እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በአለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ ታደርጋለች። የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊስ ኢግናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የዓለምን የአስተዳደር ስርዓትን ለመቀየር የሚያስችል መሰረተ ልማትና የጋራ ትብብራችንን ማጠናከር ይገባል። ብሪክስ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚሆን አዲስ የብዝሃ ዓለም አስተዳደር የመፍጠር ቁልፍ ሚና አለው። ከጦርነት ይልቅ ሰላም ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ትርፋማ ያደርጋል። የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ቃል የገቡትን ገንዘብ መስጠት አለባቸው። የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ብሪክስ በዓለም ፍትሃዊ እና መርህን ያከበረ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር የመሪነት ሚናውን መወጣት አለበት። ለብሪክስ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ልማት ትልቅ ድርሻ ያለው የእድገት ምሰሶ ነው። በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ልውውጥ እና የጋራ መማማር የበለጠ ማሳደግ ይገባል። ብሪክስ በዓለም ደረጃ ያሉ ግጭቶች በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ በማድረግ የሰላም ኃይል መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት ይኖርበታል። የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን (በበይነ መረብ) ሊበራሊዝም መር የሆነው የዓለም የሉላዊነት አስተዳደር ስርዓት ጊዜው አልፎበታል፤ አዲስ የባለብዝሃ የዓለም ስርዓት እያቆጠቆጠ ነው። በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ የመገበያያት ልምምዳቸውን ማጠናከር አለባቸው። የብሪክስ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብት፣ ሎጅስቲክስ፣ ንግድ፣ ፋይናንስ እና በሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አለባቸው። በሚሸፍነው መልክዐ ምድር፣ በያዘው የህዝብ ብዛት እና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ባለው ድርሻ ብሪክስ ትልቅ ኃይል ሆኗል። የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍትሃዊ ውክልና በሚያረጋገጥ መልኩ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ሊደረግበት ይገባል። የ21 ክፍለ ዘመን ሶፍትዌር በ20ኛ ክፍለ ዘመን የታይፕ ራይተር ማሽን ላይ ግልጋሎት ሊሰጥ አይችልም። የሰው ልጅ እና የዓለማችን የምንግዜውም ትልቅ ስጋት ሽብርተኝነት ነው። ሽብርተኝነት መከላከል እና ማውገዝ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ነው። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መጠቀም እና ማስተዳደር በጣም አስፈላጊ ነው። ህንድ በዓለም ደረጃ ያሉ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲ፣ በሰላም እና በንግግር እንዲፈቱ በቁርጠኝነት ትሰራለች። የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወቅታዊ የዓለም ነባራዊ ሁኔታን መሰረት ያደረገ አፋጣኝ ማሻሻያ ያስፈልገዋል። ብሪክስ ዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ውጥረቶችን ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና አሳታፊ የደህንነት ማዕቀፎችን ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ አሰራር መፍጠር አለባቸው። ደቡብ አፍሪካ የብሪክስ የፀረ-ሽብርተኝነት ስትራቴጂ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመተግበር ቁርጠኛ ናት። የብሪክስ መስፋት ንግድ ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አዳዲስ የትብብር አማራጮችን ይፈጥራል። የኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት ብራቦዎ ሱቢያንቶ ብሪክስ በደቡብ-ለደቡብ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የዓለም ጤና እና የከባቢ አየር ትብብር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ የዓለም የብዝሃ ወገን ተቋማት እኩልነትን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አማካኝነት በብሪክስ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ሚዛናዊ ትብብር መፍጠር ይገባል። በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ እና ጦርነት እንደ አማራጭ መጠቀም ሊቆም ይገባል። ዓለም አቀፍ ፍትህ እና ሰላምን ማስፈን ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዓለም ከምንጊዜውም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል። ግጭቶችን በውይይት እና በንግግር መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የሰውን ህይወት እና ኢኮኖሚ በፍጥነት እየቀየረ ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለእኩይ አላማ እንዳይውል በከፍተኛ ኃላፊነት እና ጥንቃቄ መጠቀም ይገባል። ብዝሃ ዓለም የባለብዝሃ ወገን አስተዳር ስርዓት ያስፈልገዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና የዓለም የፋይናንስ መዋቅርን ጨምሮ የዓለም የአስተዳደር ስርዓት ከጊዜው ጋር ተራማጅ መሆን አለበት። በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም ኢኮኖሚ እና አስተዳደር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ ይገባል። ሁለተኛ ቀኑን የያዘው 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የዋጋ ንረት ምን ማለት ነው?
Jun 30, 2025 408
የዋጋ ንረት በንፅፅር ለምሳሌ አምና 26 በመቶ ዘንድሮ 14 በመቶ ሲሆን ምን ማለት ነው? ለምሳሌ የአንድን የ100 ብር ዕቃ ወስደን ብንመለከት ካቻምና ከነበረበት 100 ብር አምና 126 ብር ሆኖ ነበር ማለት ነው። ስለዚህ የዕቃው ዋጋ በአመት ብር 26 ጨምሯል ማለት ነው። በተመሳሳይ መንገድ አምና 100 ብር ዋጋ ያለው ዕቃ ዘንድሮ 14 በመቶ ካደገ ዘንድሮ 114 ብር ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ስሌት የዕቃው ዋጋ ካምና ወደ ዘንድሮ የጨመረው በ14 ብር በመሆኑ አምና ከጨመረበት ብር 26 ጋር ሲነፃፀር ጭማሪው ቀንሷል ማለት ነው። ዋጋን ያየን እንደሆነ ግን 100 ብር የነበረ ዕቃ 114 በመሆኑ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም። የዋጋ ንረት ጨመረ የሚባለው ደግሞ ለምሳሌ አምና 26 በመቶ የጨመረው ዘንድሮ 14 በመቶ ሳይሆን 30 በመቶ ቢሆን የጨመረው አምና 100 ብር የነበረው ዕቃ ዘንድሮ 114 ሳይሆን 130 ብር ይሆናል ማለት ነው። ይህ አምና ከጨመረበት የ26 ብር ይበልጣል ማለት ነው። ስለዚህ ካቻምና 100 ብር የነበረው ዕቃ አምና 26 ብር ጨምሮ 126 ከሆነ በኋላ ዘንድሮም 14 ብር ስለጨመረ በቀላል ቀመር ዘንድሮ 140 ብር ሆኗል ማለት ነው። ስለዚህ በሁለት አመታት የዕቃው ዋጋ 40 ብር ጨምሯል። የዕቃው ዋጋ አልቀነሰም በየአመቱ የጨመረበት ምጣኔ ግን ካምና ዘንድሮ ያነሰ ነው። ይህ ነው የዋጋ ንረት ቀነሰ ማለት። ዋጋ ቀነሰ ማለትስ ምን ማለት ነው? ዋጋ ቀነሰ የሚለውን ከማየት በፊት የዋጋ ንረት የለም ማለት ምን እንደሆነ በዛው 100 ብር ዋጋ ባለው ዕቃ እንመልከት። ይህ ባለፈው አመት ብር 100 የነበረ ዕቃ ዘንድሮም እዛው 100 ብር ላይ ቢቆይ የዋጋ ንረት ዜሮ ነው። ስለዚህ የዕቃው ዋጋ አልተለወጠም ማለት ነው። ዋጋ ቀነሰ ማለት ግን የዋጋ ንረት ከዜሮ በታች ይሆናል ማለት ነው። በምሳሌው ለማስረዳት አምና 100 ብር ዋጋ ያለው ዕቃ ዘንድሮ 90 ብር ቢሆን የዋጋ ንረቱ ወይም ለውጡ ከዜሮ በታች 10 በመቶ ነው። በዚህ ግዜ የዋጋ ንረት ቀነሰ ሳይሆን ዋጋ ቀነሰ ይባላል። እነዚህ ሶስቱ የዋጋ ለውጦች ለሸማቾችና ለአምራቾች ምን ማለት ናቸው? ለሸማቾች ከሁሉም የሚመረጠው ዋጋ ሲቀንስ ማለትም 100 ብር የነበረው ዕቃ 90 ብር ሲሆን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ተመራጩ ዋጋ ንረት ሳይኖር አምና 100 ብር የነበረው ዕቃ ዘንድሮም ሳይለወጥ በዜሮ ንረት 100 ብር ላይ ሲቆይ ነው። ሶስተኛው የተሻለ አማራጭ አምና 100 ብር የነበረ ዕቃ ዘንድሮ በ26 በመቶ ጨምሮ ብር 126 ከሚሆን በ14 በመቶ ጨምሮ ብር 114 ሲሆን ነው። ይህ ሶሰተኛው አማራጭ በሁለቱም ዋጋ ስለሚጨምር በትንሽ የጨመረው ተመራጭ ይሆናል ማለት ነው። ከአምራቾች አንፃር ሲታይ ከላይ ለሸማቾች የተሻለ አማራጭ በቅደም ተከተል ያስቀምጥነውን ገልብጠው ማንበብ ነው። አሁን ብሔራዊ ባንክ እያለ ያለው የዋጋ ንረት ወይም አመታዊ ጭማሪው ቢበዛ ከ10 በመቶ እንዳይበልጥ የሚረዳ የገንዘብ ፖሊሲ እተገብራለሁ ነው። የባንኩ አላማ የዋጋ ንረት ዜሮ ወይም ከዜሮ በታች እንዲሆን ሳይሆን 1) ከ10 በመቶ በታች እንዲሆን ሲሆን 2) የትረጋጋና ተገማች እንዲሆን ነው። የተረጋጋ ማለት ከወር ወር ወይም ካመት አመት ዋጋ የሚለወጥበት ሁኔታ በጣም የተራራቀ ያልሆነ ማለት ነው። ለምሳሌ ካንዱ ወር ወደ ቀጣይ ወር ጭማሪው 0.5 በመቶ ሆኖ በቀጣይ ወር ደግሞ የ5 በመቶ ጭማሪ ከዚያም በቀጣይ ወር ከዜሮ በታች የ2 በመቶ ወርሃዊ ለውጥ ቢመዘገብ ያልተረጋጋ ወይም ተገማች ያልሆነ የዋጋ ለውጥ አለ ማለት ነው። ሰለዚህ የተረጋጋና ተገማች የዋጋ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ የባንኩ ሁለተኛው አላማ ነው ማለት ነው። ብሔራዊ ባንክ በጣም ዝቅተኛ የዋጋ ንረት ወይም ከዜሮ በታች የዋጋ ለውጥ እንዴት ያየዋል ብለን ያየን እንደሆነ ነገሩ እንዲህ ነው። ቅድም ከላይ እንዳየነው የዋጋ ንረት ከሸማቾችና ካአምራቾች አንፃር የሚታየው በተቃራኒ መንገድ ነው። ስለሆነም ምንም እንኳን የዋጋ ንረት በጣም ዝቅተኛ ወይም ከዜሮ በታች ቢሆን ለሸማቾች ጥሩ ቢሆንም አምራቾችን ግን የማያበረታታ ስለሚሆን ማምረት ያቆማሉ ሠራተኛ ይቀንሳሉ አጠቃላይ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ይገታና ጭራሽ ከምርት እጥረት የተነሳ የዕቃዎች ዋጋ መናር ይከሰታል ሥራ አጥነት ይበዛል። ስለዚህ መንግስት ሥራ እንዲፈጠር ኢኮኖሚ እንዲነቃቃም ስለሚፈለግ የተረጋጋና ዝቅተኛ ሸማቹን የማይጎዳ አምራቹንም የሚያበረታተ የዋጋ ሁኔታ እንዲኖር ይሰራል ማለት ነው። ለአንድ ኢኮኖሚ ትክክለኛው የዋጋ ንረት ስንት ነው? ይህ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ግን ከባድ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለለስ ከሚረዱት ሁኔታዎች አንዱ ኢኮኖሚው ያለበት ደረጃ ነው። ምን ማለት ነው በጣም ባደገና የበለጠ የማደግ እድሉ ጠባብ ለሆነ ኢኮኖሚ 1 በመቶ ወይም 2 በመቶ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ ገና የማደግ እምቅ አቅም ላለውና በማደግ ላይ ላለ ሀገር ነጠላ አሃዝ የዋጋ ንረት እንደ ሁኔታው የሚለያይ ሆኖ ተመራጭ ሊሆን ይችላል። ስንት ነው የሚለው ግን በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጥ አለበት። ለምሳሌ የሀገራችንን threshold inflation or optimal inflation level ለማወቅ እኔን ጨምሮ የባንኩ ሠራተኞች በሳይንሳዊ መንገድ ለማወቅ ተሞክሯል። በኔ ጥናት 7 በመቶ ሲሆን በሌሎቹም ከዚሁ ያልራቀ ውጤት እንዳለ አይቻለው የመረጃ አጠቃቀምና የሜቶዶሎጂ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። ሰለዚህ በነዚህ ጥናት መሰረት ብሔራዊ ባንክ የነጠላ አሃዝ የዋጋ ንረት አላማ አድርጎ መንቀሳቀሱ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ማለት ነው ለኛ ኢኮኖሚ። ለማጠቃለል የዋጋ ንረት ምንነትን በተመለከተ ያለውን ውዥምብር ለማጥራት ይህ አጭር መግለጫ ያግዛል ብዬ እያመንኩ የበለጠ መብራራት ካለበት ወይም ጥያቄ ካለ አንባቢዎች በአስተያየት መስጫው ላይ ማሰቀመጥ ትችላላችሁ። አቶ ፈቃዱ ደግፌ የብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ
የሺህ ሀይቆች ምድር
Jun 24, 2025 567
የሺህ ሀይቆች ምድር (በራሔል አበበ) በርካታ መገለጫዎች አሏት። የሺህ ሀይቆች መፍለቂያ። አረንጓዴ ምድር። 75 በመቶ የአገሪቱ ገፀ-ምድር በደን የተሸፈነ። የአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ። በአውሮፓ ከበለጸጉ አገራት አንዷ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በዓለም ቁጥር አንድ የደስተኞች አገር በመባል የተሰየመች ሰሜን አውሮፓዊት አገር - ፊንላንድ። በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋባዥነት በአዲስ አበባ የአገሪቱ ኤምባሲ አስተባባሪነት በቅርቡ ፊንላንድን የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር። በጉብኝቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፤ ሞዛምቢክ እና ዛምቢያ ጋዜጠኞች ተሳትፈናል። የአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ምንም እንኳን የትም አገር ስሄድ ቀድሜ መረጃ የማየት ልምድ ቢኖረኝም በመጀመሪያው ዕለት ለእራት ስንወጣ ያየሁት በምሽት ያልተለመደ የፀሐይ ፍካት ግን እራቱ ቁርስ እንዲመስለኝ አድርጓል። ከዚያ በኋላ ለመድሁት። በእርግጥ በአንድ ወቅት በስፔንም ፀሐይ እስከ እኩለ ሌሊት የማትጠልቅበትን ክስተት ተመልክቻለሁ። በፊንላንድ ያየሁት ግን ተለየብኝ። ፀሐይ ፈጽሞ ለጨረቃ ቦታ መልቀቅ አትፈልግም። ምሽቱ የሚደምቀው በመብራት ሳይሆን በፀሐይ ነው። ሌሊቱ ብርሀን ነው። ሰማይ አይጠቁርም። በየዕለቱ ሳይጨልም ይነጋል። በዚህ ወቅት በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ሰማይ ላይ የሚታየው ሰሜናዊ የቀለማት የብርሀን ፀዳል ሌላው የፊንላንድ መድመቂያ ነው። የሰሜን አውሮፓ/ኖርዲክ አገራት በተፈጥሮ የታደሉ ናቸው። እኔ ደግሞ የተፈጥሮ አድናቂ ነኝ። ያለማጋነን በፊንላንድ ተፈጥሮ ከነክብሯ ተጠብቃ አይቻለሁ። ንጹህ አየሯ የዚህ ውጤት ነው። አድናቆቴ የጀመረው ከኤርፖርት እስካረፍኩበት ሆቴል 15 ኪሎ ሜትር ያህል በመኪና ስንጓዝ የከተማዋን አረንጓዴነትና የምድሪቱን ልምላሜ ስመለከት ነበር። በጉብኝቴም በተግባር አረጋገጥሁ። የአገሪቱ አብዛኛው መሬት በደንና በውሃ ተሸፍኗል። በዋና ከተማዋ ሄልሲንኪና በዙሪያዋ በሚገኙ ውብ ደኖች መሀል ስንጓዝ መሬቱ ለም ስለመሆኑ ዓይን ብቻ ሳይሆን እግርም ምስክር ነው። ሲራመዱ የመሬቱ ምቾትና እንደ ስፖንጅ ስምጥ ስምጥ ማለት ለምነቱን ይናገራል። በሄልሲንኪ ሴኔት እና ካንሳላስቶሪ አደባባዮች እንደእኛዎቹ አራት እና ስድስት ኪሎ አደባባዮች ናቸው። ቤተ-መንግስት፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ፓርላማ፣ ቤተ-መጽሐፍት እና ቤተክርስቲያንን አጎራብተው ይዘዋል። የሄልሲንኪ ሕንጻዎች እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ውብና የሥነ-ሕንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ናቸው። የነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ከተማዋ አልተጨናነቀችም። በአስፋልትና ደረጃውን በጠበቀ ኮብልስቶን የተሰራው የከተማዋ አውራ ጎዳና ከዘመናዊ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የህዝብ አውቶቡስና የኤሌክትሪክ ባቡር ያስተናግዳል። ለአውሮፓ ከተሞች አዲስ የሆነ ሰው ኮብልስቶኑ የእግረኛ መንገድ መስሎት መሐል የመኪና መንገድ ላይ ሊገኝ ይችላል። እኔም የተረፍሁት እንዲህ አይነቱን የመኪና መንገድ በአንድ ወቅት በኢጣልያ በማየቴ ነበር። የተፈጥሮ ውበት ደምቆ የሚታይባት ፊልናልድ ሲልቨር በርች የተሰኘው ብርማ ቀለም ቅርፊት ያለው ዛፍ እና ቡናማ ድብ ብሔራዊ መለያዎቿ ናቸው። በረጃጅሞቹ ዛፎች መሐል ከእንስሳት ባሻገር ስትሮበሪና እንጉዳይን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ዕጽዋት ይገኛሉ። በፊንላንድ ብዙ አይነት የእንጆሪ/ስትሮበሪ ዝርያ አለ። ወቅቱ ፍሬ የሚደርስበት አልነበረም እንጂ ከጫካዎቹ መሐል ገብቶ በተለያዩ የስትሮበሪ ፍሬዎች ቅርጫት ሞልቶ መውጣት የተለመደ መሆኑን ተረድቻለሁ። ፊንላንድ የሺህ ሀይቆች ምድር ተብላም ትሞካሻለች። ለቁጥር የሚያዳግቱ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀይቆችና የውሀ አካላት ከተፈጥሮ ሀብቶቿ መካከል ናቸው። ለጉብኝት በሄድኩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚቀርብልኝን ኩልል ያለ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በፍቅር ነበር የምጠጣው። ግዴታ ካልሆነ የፋብሪካ ውሃ በፊንላንድ ቦታ የለውም። ንጹህ የተፈጥሮ የምንጭ ውሃ ከቧንቧ ይቀዳል። ጽድት ከማለቱ ጣዕሙ። ፊኒሾች ለባህልና ቅርስ ትልቅ ቦታ አላቸው። በተለይ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ቁርኝት አስገራሚ ነው። በአብዛኛው አፍሪካ ውስጥ የሚነገር አፈ-ታሪክና ተረት በፊንላንድም ከተፈጥሮ በተለይም ከዛፎችና ከእንስሳት ጋር ተያይዞ ሲተረትና የመድረሻቸው መነሻ እንደሆነ ሲነገር ተደንቄያለሁ። በጉብኝታችን በአንዱ ቀን ኑኪሲኦ ብሔራዊ ፓርክ ሄድን። ይህ ደግሞ እጅግ የተለየ ተፈጥሮን ማያ ስፍራ ነው። በረዣዥም ዛፎች መሐል ካደረግነው ጉዞ በኋላ የቀረበልን ባህላዊው የፊንላንድ የሳውና እና የዋና ግብዣ ነበር። ሳውና የፊንላንድ ባህል ነው። በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለ የፊኒሽ ቃል “ሳውና” እንደሆነ ይነገራል። ዛሬ በዓለም ላይ በተለይም በባለኮከብ ሆቴሎች በስፋት የምናገኘው ሳውና መነሻው ፊንላንድ ናት። በርካታ የሳውና ስፍራዎች ከመኖራቸው የተነሳ የሳውና ቁጥር በአገሪቱ ከተመዘገቡ መኪኖች ቁጥር ይበልጣል ይባላል። ግብዣውን ሁላችንም በደስታ ነበር የተቀበልነው። በባህሉ መሰረት ሳውና ውስጥ በቅጠል እየተጠበጠብን ከፍተኛ ሙቀት ሲሰማን ከፊት ለፊት ባለው ቀዝቃዛ የተፈጥሮ ሀይቅ ውስጥ በመግባት ዋና የሚችል ዋኝቶ የማይችል ደግሞ በመነከር ሰውነቱን አቀዝቅዞ እንደገና ወደሳውናው ይመለሳል። የተለየ ነው። የጉብኝቱ ዋና አስተባባሪ አና ላሚላ ትባላለች። የ35 ዓመት የስራ ልምድ ያላት ብስል ዲፕሎማት ናት። በተለያዩ አገራት ፊንላንድን ወክላ ሰርታለች። አሁንም በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አምባሳደር ነች። ትክክለኛ የኮሙኒኬሽን ሰው ናት። አንቺ ያልኳት በአንቱታ ላርቃት ባለመፈለጌ ነው። ለነገሩ ስትታይም የ35 ዓመት ወጣት እንጂ የ35 ዓመት የስራ ልምድ ያላት አትመስልም። አንድ ቀን አን “መኮንን” በሚለው የአያቴ ስም እየጠራችኝ ስምሽ እኮ የፊኒሽ/የፊንላንድ ነው ይህን ታውቂያለሽ? ከእኛ ጋር ዝምድና ይኖርሽ ይሆን?" አለችኝ ፈገግ ብላ። "ኸረ በፍፁም ኢትዮጵያዊት ነኝ" አልኳት። ትክክል ነበረች። አጭር የፅሁፍ መልዕክት የመለዋወጥ ሀሳብን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቀው “ማቲ መኮንን” የተባለ ፊንላንዳዊ ኢንጂኒየር ነው። የቴክኖሎጂ ነገር ከተነሳ አብዛኞቻችን ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር ስንተዋወቅ የያዝነው ኖኪያ የፊንላንድ ምርት ነው። የመኮንንን ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት ለዓለም ይፋ ያደረገውም ኖኪያ ነው። አሁንም ኖኪያ በኔትወርክ ዝርጋታ ጭምር እየሰራ ያለ ግዙፍ የቴሌኮም ተቋም ነው። ኢትዮጵያና ፊንላንድ የረዥም ዓመታት የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው 66 ዓመታትን ተሻግሯል። ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ከእርዳታና ትብብር ባሻገር በተለያየ መስክ በጋራ ትሰራለች። በጉብኝቴ ወቅት ያገኘኋቸው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሌና ቫልቶነን ይህን ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት መኖሩን ነግረውኛል። ከንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ኖኪያን ከመሰሉ ኩባንያዎች ጋር የሚደረግ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና በአገሪቱ ቴክኖሎጂ መዘመኑን የተረዳሁት በአገሪቱ ብሔራዊ የሚዲያ ተቋም ይሌ ያለማንም እርዳታ ዜና ቀርጾ የሚያሰራጭ ሰው አልባ ሮቦትድ የስቱዲዮ ቴክኖሎጂ ስመለከት ነበር። ፊንላንድ በትምሕርት ጥራትም ስሟ በቀዳሚነት ይነሳል። በአገሪቱ ከ800 በላይ፤ በመዲናዋ ደግሞ 40 የሚጠጉ ቤተ-መጻሕፍት አሉ። ከአገሪቱ ፓርላማ አቅራቢያ የሚገኘውና አገሬው የእኩልነት ተምሳሌት ነው የሚለው የሄልሲንኪ ግዙፉ ማዕከላዊ ቤተ-መጽሐፍት ኦዲ ይባላል። በውስጡ በርካታ አገልግሎቶችን ይዟል። ንባብ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የባህልና ፈጠራ ታለንቶችን ያስተናግዳል። ከልጅ እስከ አዋቂ ለሁሉም ቦታ አለው። ፊንላንድ ዜጎቿ በደስታ ግብር የሚከፍሉባት አገር መሆኗን የአገሪቱ የታክስ አስተዳደር ሲናገር በኩራት ነው። ግብር መሰወር፤ ክፈሉ ብሎ በየግዜው መቀስቀስን የመሳሰሉ ነገሮች እዛ ቦታ የላቸውም። የኩባንያም ሆነ የግለሰብ ግብር ከፋዮች በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በወቅቱ እንደሚወጡ አስተዳደሩ ይገልጻል። ይህም የዜጎች ፍላጎትን ለማሟላት በተሰራ ስራ የተፈጠረ መሆኑን የተመለከትኳቸው ተቋማት ሃላፊዎች ይገልጻሉ። ዜጎች በመንግስት ላይ ከፍተኛ እምነት አላቸው። በፊንላንድ የዜጎች ደስተኝነት የሰላምና ነጻነት መገለጫ እንደሆነ ምሁራኖቻቸው በጥናት ስራዎቻቸው ጭምር ይመሰክራሉ። የደስታቸው ምንጭ ነጻና ጥራት ያለው ትምሕርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፤ በፍትህና እኩልነት፤ በበጎ አድራጎት ተግባር፤ የእናቶችና ህጻናት ጤናን ጨምሮ አርአያ የሚሆኑ ጠንካራ የማሕበራዊ ደህንነትና ትስስር ስራዎች የመጡ ውጤቶች እንደሆኑ ይገለጻሉ። በጾታ እኩልነት ሴቶች በሁሉም መስክ ጥሩ ስፍራ አላቸው። በፖለቲካውም ከወንዶች ተቀራራቢ ቦታ እንዳላቸው የአገሪቱን ፓርላማ ስንጎበኝ ተረድቻለሁ። ከ200 የምክር ቤት አባላት 91ዱ ሴቶች ናቸው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ፊንላንድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደስተኛ አገራት ደረጃ ላይ ለስምንት ተከታታይ ዓመታት የከፍታ ስፍራዋን ሳትለቅ በቁጥር አንድ ላይ እንድትቆይ አድርጓታል። ዜጎቿ በቀጣዩ ዓመትም ለዘጠነኛ ጊዜ የዓለም የደስተኞች አገር ሆና ትቀጥላለች የሚል እምነት አላቸው።
ቢልጌትስ ታላቁን የኢትዮጵያ የክብር ኒሻን እንዴት ተቀዳጁ?
Jun 2, 2025 639
በሀገረ አሜሪካ ሲያትል ውስጥ ተወልደው ያደጉት ቢል ጌትስ የዕውቁ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮ ሶፍት መስራችና ባለቤት ናቸው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ከአጋራቸው ፖል አለን ጋር የመሰረቱት ማይክሮሶፍት ቢልጌትስን ከምድራችን ግንባር ቀደም ቱጃሮች አንዱ አድርጓቸዋል። ቢልጌትስ ከኮምፒዩተር ቴክኖሎጂው ማይክሮሶፍት ባሻገር በፈረንጆቹ 1990 በቀድሞ ስሙ ‘ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሸን’ በአሁኑ መጠሪያው ‘ጌትስ ፋውንዴሽን’ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመዋል። ፋውንዴሽኑ የሰው ልጆች ሁሉ ዕኩል ዕድልና የተሻለ ነገ ይኖራቸው ዘንድ በተለይም በግብርና እና በጤናው ዘርፍ መልከ ብዙ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ተግብሯል። የጌትስ ፋውንዴሸን ተልዕኮ “ሁሉም ሰው ጤናማና ምርታማ ሕይወት የሚመራባት ምቹ ዓለም መፍጠር” የሚል ነው። የጌትስ ፋውንዴሽን በስፋት ድጋፍ ካደረገባቸው ሀገራት መካከል ታዲያ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2000 ስራ የጀመረ ሲሆን እ.አ.አ በ2012 ቢሮውን በአዲስ አበባ በመክፈት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እና ለጋሾች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያውያን ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸውና የኑሮ ዘይቤያቸው እንዲሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን መደገፍ የፋውንዴሽኑ ግብ ነው። ከለጋሾች በተገኘ ድጋፍ የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ለውጦች መታየታቸውንና በእናቶችና ህጻናት ጤና፣ ትምህርት እና ግብርና ምርታማነት አመርቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያመለክታል። ፋውንዴሽኑ ጥረቶቹን ከኢትዮጵያ መንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር በማሰናሰን በስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት፣ በፋይናንስ አካታችነት እና በንጽህና አጠባበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል። ለዚህ ተግባሩም በኢትዮጵያ ከ777 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ከጌትስ ፋውንዴሽን ስራዎች መካከል በጤናው ዘርፍ የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም አማካኝነት በገጠራማ አካባቢዎች ዜጎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን እንዲያገኙ ማስቻል ይጠቀሳል። የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የሳምባ ምች እና ወባ በሽታዎችን በምርምር፣ በገንዘብ ድጋፍ እና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለመከላከል እየሰራ ነው። በግብርና ዘርፍ ደግሞ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ አላማ ላነገበው የስንዴ ክላስተር እርሻ ኢኒሼቲቭ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን አምራቾች ከቤት ፍጆታነት ወደ ገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያገኙ ደግፏል። አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች የዶሮ ጫጩቶችን ለሚያቀርበው የግል ኩባንያ ኢትዮ ቺክን ድጋፉን ለግሷል። የፋውንዴሽኑ መስራችና ሊቀመንበር ቢል ጌትስ ባሳለፍነው መስከረም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የክላስተር የስንዴ ማሳዎችንና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ስራዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር መጎብኘታቸው ይታወሳል። ቢል ጌትስ ከጉብኝቱ በኋላ ባሳተሙት መጣጥፍ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በግብርናው ዘርፍ የመጣው እመርታ እንዳስደነቃቸው አስፍረዋል።በኢትዮጵያ ያልታረሱ ማሳዎችን በማረስ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቅምና ሌሎች የሪፎርም ስራዎችን በመተግበር በቅርብ ዓመታት ተምሳሌታዊ የሆነ ምርትና ምርታማነት መመዝገቡን ገልጸው ነበር። በዚህም ፋውንዴሽኑ ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያን ግብርና ዘርፍ በመደገፉ ትልቅ ኩራት ይሰማዋል ብለው ነበር ቢል ጌትስ ። ጌትስ ፋውንዴሽን በሌሎች የልማት ኢኒሼቲቮች ለአብነትም የኢትዮጵያ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ በፋይናንስ አካታችነት፤ በመረጃ አሰባሰብ፣ ምርምር እና ፖሊሲ ትግበራ የሀገር በቀል አቅሞችን የመገንባት ስራዎችን ይደግፋል። ኢትዮጵያም ጌትስ ፋውንዴሽን በተለያዩ መስኮች ላለፉት 25 ዓመታት ላከናወናቸው ስራዎች እውቅና ሰጥታለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን ታላቁን የክብር ኒሻን ለቢል ጌትስ ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቤተመንግሥት በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ሸልመዋል። ይህ የከበረ ሽልማት የጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተፅዕኖዎችን ያከበረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በንግግራቸው ለቢል ጌትስ ፋውንዴሽን የ25 ዓመታት አሸጋጋሪ ሥራዎች ምስጋና አቅርበዋል። ቢል ጌትስ ከቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅነት ወደ በጎ አድራጊነት ያደረጉትን ጉዞ በማውሳትም ዝቅ ብሎ በማገልገል፣ በአክብሮት እና በእኩልነት እምነት ላይ የተመሠረተውን አገልግሎታቸውን አድንቀዋል። ፋውንዴሽኑ በጤና፣ በግብርና፣ በዲጂታል መታወቂያ የሚያደርገው ብርቱ ድጋፍ ብሎም በመከባበር ላይ የተመሠረተ የፋውንዴሽኑ የትብብር ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወስቷል። ቢል ጌትስ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ የሰዎችን ጤናና ምርታማነት ለማሻሻል በፋውንዴሽናቸው አማካኝነት ላደረጉት በጎ ድጋፍ ኢትዮጵያ የክብር ኒሻን ሸልማቸዋለች።
ደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ የአራት ዓመት ጉዞና ስኬት
Apr 25, 2025 1746
ደመና ማበልጸግ(Cloud Seeding) ምንድን ነዉ? የደመና ማበልጸግ በደመና ውስጥ ያለውን የዝናብ መጠን ወይም ዓይነት የሚለውጥ(የሚጨምር) የአየር ሁኔታ መቀየሪያ ዘዴ ነው። ይህም ማለት በመሰረታዊነት ዝናብ ሊሆን የሚችልን ነገር ግን አቅም ያጣን ደመና ወደ ዝናብ እንዲቀየር በማፋጠን መዝነብን የመጨመር ተግባር ነው። የደመና ማበልጸግና ማዝነብ ቴክኖሎጂ በ1940ዎቹ የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂን ለመተግበር የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም በዋናነት በአውሮፕላን፣ ባሎን፣ ሮኬት፣ ድሮን እና መሬት ላይ በሚቀመጥ ጀነሬተር በመታገዝ ደመና ላይ ጨው መሰል ብናኝ በመርጨት በዝናብነት ወደ ምድር የማይወርድ ደመናን አቅም ኖሮት እንዲዘንብ ወይም እንዲወርድ ማድረግ ነው። ይህ ሂደት ሰው ሰራሽ ሲሆን የደመና መዝነብን አቅም ከ15-30 በመቶ በማሳደግ ዝናብ እንዲከሰት የማድረግ አቅም አለው። ይህ ቴክኖሎጂ በተለያዩ ሀገራትና ጊዜያት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በ2013 ዓ.ም ሀገራችን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነትና ትብብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ችሏል። በወቅቱም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ማዕከል በመጣ አውሮፕላንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአየር ላይ ኦፕሬሽን ተደርጓል፤ የማቴሬሪያልና የሙያ ድጋፍ ተገኝቷል።ድርቅ አጋጥሞ በነበረበት በቦረና ጉጂ አካባቢ የዝናብ ማዝነብ ኦፕሬሽን ተከናውኗል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚሰጠው አቅጣጫ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተለያዩ ተቋማትን አስተባብሮ ሀገራችን የቴክኖሎጂው ባለቤት የምትሆንበትን መሰረተ ልማትና ሲስተም እንዲያበለጽግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ሲስተሙን ከመጠቀም አልፎ ከዚህ ቀደም በቻይና ተመርቶ ስንጠቀምበት የነበረው የደመና ማበልጸጊያ(ማዝነቢያ) ግራውንድ ጀነሬተር በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስተባባሪነት በሀገራችን በሙሉ አቅም መሥራት ተችሏል። በራስ አቅም ልንሰራው በመቻላችን የቴክኖሎጂ ባለቤትነታችንን ከማረጋገጥ ባሻገር የውጭ ምንዛሪን በማዳን ከፍተኛ አገራዊ ጥቅም ሊገኝበት ችሏል። በ2015 ዓ.ም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሎ በሀገራችን በዝናብ እጥረት የሚያጋጥመውን አደጋ ለመከላከል ለዝናብ ማዝነቢያ የግራውንድ ጄኔሬተር ማምረቻ የሚሆን የፕሮጀክት በጀት መድቧል። የፕሮጀክት በጀቱንም የማምረት ሥራው ሂደትና ስኬት እየታየ በሁለት ዙር ለመልቀቅ ከኢፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ውል በተፈራረመው መሰረት በመጀመሪያው ዙር 20 ግራውንድ ጀነሬተር ማምረት ሥራ በስኬት በማጠናቀቅ በኦሮሚያ ክልል በሚፈለግበት ወረዳዎች በሟቋቋም ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡ ተደርገዋል። በሁለተኛው ዙር 25 የግራውንድ ጀነሬተሮቹን የማምረት ሥራው ተጠናቋል፡ ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡም ተደርገዋል። በአጠቃላይ 45 ጄኔሬተሮች በማምረት የዝናብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ቦታዎች (ደቡብና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በሶማሊ ክልል፣በእንጦጦ ተራራ) ተተክሏል። የአየር ንብረት እና ክላውድ ሲዲንግ መሰረታዊ እውቀት፣የሲስተም ተከላና ኦፕሬሽን በመስክና በታቀደ ስልጠና አቅም ተገንብቷል። ድሮንን በመጠቀም ሙከራዎች ተደርገዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት በአየር ላይም ኦፕሬሽን ስናደርግ ቴክኖሎጂን በራስ አቅም፣ ባለሙያና ቴክኖሎጂ ለመስራት ጥናትና ትግበራው የሚቀጥል ይሆናል። በአገር ደረጃ የሚመለከታቸውን ተቋማት በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትና ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ምርምርና ከፍ ያለ ሥራ ይሰራል። የደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት በዋናነት በኦፕሬሽናልና በተግባራዊ ምርምር ቴክኖሎጂን የመጠቀም፣አስቻይ መሰረተ ልማት የማቋቋም፣ የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ ልማትን በሚያሳልጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ተልዕኮውን የሚፈጽም ነው። ይህ ፕሮጀክት ወደ ስራ ሲገባ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግቦ ሲሆን የመጀመሪያው በሀገራችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከባለድርሻ አካል ጋር በመሆን እገዛ ማድረግ፤ በምርምር ፣ ልማት እና ትግበራ ላይ የተመሰረተ ዳመናን ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማስቻል ፣በዘርፉ ልህቀት ማዕከል ማቋቋም ነው። ከዚህ በተጨማሪ የዳመናን ማልማት ምርምር፣ ልማት እና ትግበራን ለማሳለጥ የሚያግዙ ሀገራዊ የፖሊሲና የመሠረተ-ልማት ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ማቅረብ፤ እንዲሁም በዳመና ልማት ዙሪያ የሚሰማሩ ባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ትስስርን ምቹ ምህዳር መፍጠር ነው።
ሀዘንና ደስታ የተሰናሰሉበት ትዕይንተ ጥበብ - "ኩርፍወ"
Apr 23, 2025 1351
(በእንዳልካቸው ደሳለኝ - ከኢዜአ ወልቂጤ ቅርንጫፍ) "ኩርፍወ ጨዋታ" በጉራጌ የተለያዩ ድራማዊ ትዕይንቶች የሚገለፁበት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ እሴት ነው። ይህ ትውፊታዊ ክንዋኔ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት እንደተጀመረም ከአፈ ታሪክ መረዳት ይቻላል። ይህ ጨዋታ አዝናኝና ማራኪ እንዲሁም ብዙ ጊዜያትን ካስቆጠሩ ባህላዊ ጭፈራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሀዘንና ደስታን አንድ ላይ በማሰናሰል የሚተገበር ሲሆን ተጀምሮ እስኪያልቅም የሚያጓጉ ትዕይኖች ይታዩበታል። "የኩርፍወ ጨዋታ" ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ሞትና ትንሳኤ ጋር ተያይዞ የሀዘንና ደስታ መግለጫ ነው። ለሁለት ሳምንታት በዙር ይከወናል። የመጀመሪያው በሰሞነ ህማማት ተጀምሮ እስከ ትንሳኤ የሚቆይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ዙር ልጃገረዶቹን ብቻ ሳይሆን ወጣቶች እንዲሁም እናትና አባቶችን ጭምር የሚያሳትፍ ነው። ከትንሳኤ በኋላ መጫወትን ይመርጡታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በደስታ ለመጫወት፣ የፍስክ ምግብና መጠጥንም መጠቀም ስለሚያስችል ነው። የ"ኩርፍወ ጨዋታ" መከወኛ ስፍራ ጨፌ ወይም ወንዝ በሚገኝበት አካባቢ ሲሆን ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ተጋጊጠውና አምረው ደምቀው መታየት ስላለባቸው ሁሉም ባህላዊ የክት ልብሳቸውን ለብሰውና ተውበው ይገኛሉ። ኩርፍው አስደናቂ ከሆኑ ገፅታዎቹ መካከል ሁለት መልኮችን አንድ ላይ አሰናስኖ ማንፀባረቁ ነው። የልጃገረዶቹ የእጅ እንቅስቃሴና የእግር አጣጣል በጉራጌዎች ለጀግና የሚከወነውን "ወርኮ" የተሰኘ ሙሾ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ዜማው ደግሞ የደስታ ቅላፄ መሆኑ ነው። የኩርፍወ ጨዋታ የራሱ ዜማ እና ግጥም ያለው ሲሆን ከዜማ አውራጇ ቀጥሎ ሁሉም ተጫዋች አዝማቹን ተቀባብለው ያዜማሉ። አዝማሪ፡- ተቀባዩ ኩርፍወ ኩርፍወ (2×) ኤዋዬ ኩርፎ ኩርፍወ ኩርፎ ኩርፎ ዋዬ ኩርፎ ኩርፎ ሞቴም ባማማቴ ጎር ቲገባ ዘር ይገባ እንደገና በተለየ ዜማ ኩርፍወ -----------------------ዋይ (2×) ኩርፍወ በሞቴ ዃም ባማማቴ ውርሰንበት ገባቴ ......... እያሉ ረዘም ባሉ ግጥሞች ያዜማሉ። ዜማና ግጥሞቹ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በቅብብሎሽ የመጡ ናቸው። የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ልጃገረዶች ለምልሞና ማራኪ ገጽታ ይዞ በበልግ ወራት በስፋት በሚበቅለው "አምባሬ" ከተባለው የተክል ቅጠል ዝርያ በማገልደም ይጫወታሉ ብለዋል። ጨዋታው በዞኑ በይበልጥ በምሁር አክሊል ወረዳ እንደ ሚዘወተርም አመላክተዋል። ልጃገረዶቹ አምባሬ የሚባለው ተክል ቅጠል ከእነስሩ ነቅለው በመሸንሽን ወገባቸው ላይ አስረው ልክ እንደ ጉራጌ ባህላዊ ለቅሶ እንቅስቃሴ እጆቻቸውን ዘርግተው እግራቸውን ደግሞ ከመሬት ከፍና ዝቅ በማድረግ ነው ሚጫወቱት።ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ባህላዊና የክት ልብሳቸውን ከመልበስ በተጨማሪ በአምባር እና በአልቦ ጌጦች ተሽቆጥቁጠው ፀጉራቸውን ሹርባ በመሰራት ከየአቅጣጫው ወደዚሁ ስፍራ ይተማሉ ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት በደስታ መቀየሩን በጭፈራው ይጎላል ነው ያሉት። ኩርፍወ ከሌሎች ባህላዊ የጉራጌ ባህላዊ እሴቶች የሚለየው ራሱን የቻለ ዜማ ፣ ግጥም እና የክዋኔ ስርዓት ያለው መሆኑን ነው። የ"ኩርፍወ ጨዋታ" ማሳረጊያ ላይ ልጃገረዶች አምቾን ወንዶች በማያገኙት ቦታ ላይ ደብቀው ይቀብራሉ። የደበቁትን አምቾ ወንዶች ካላገኙት የልጃገረዶች የወደፊት መፃኢ ዕድል ብሩህ ተስፋ እንዳለው፤ ካገኙት ደግሞ ለወንዶች የተሻለ ጊዜ ይመጣል ተብሎ እንደሚታመን ወይዘሮ መሰረት ይጠቅሳሉ። ይህ እሴት ጥናት እና ምርምር እንዲደርግበት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀው ድራማዊ ስርዓቱ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል ። በዞኑ የኩርፍወ ጨዋታ ከሚዘወተርበት በዋናነት የሚጠቀሰው የምሁር አክሊል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳህሉ ወልደማርያም በበኩላቸው ኩርፍወ እርስ በርስ የሚያቀራርብ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴት የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል። አብሮነትና አንድነትን ከመስበክ አንጻር ያለው ሚና የላቀ መሆኑን አውስተው ባህሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ ቢቆይም ከነበረበት እንዲያንሰራራ ተደርጓል ነው ያሉት። ልጃገረዶች በኩርፍወ ጨዋታ ድራማዊ ትዕይንትን በማሳየት በአንድ በኩል ደስታቸውን ሲያንጸባርቁ በሌላ ጉኑ ሲያዝኑ ይስተዋላል። ጨዋታው የሰሙነ ህማማት የሚሆንበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዳውያን የደረሰበት መከራ፣ ስቃይና ሞት ከዚያም የክርስቶስ ትንሳዔን ለማመላከት ነው። ባህላዊ ትውፊቱ ይዘቱን ሳይለቅ በየአካባቢው እንዲተገበርና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራም መሆኑን ነው አቶ ሳህሉ የገለጹት። አቶ አለምይርጋ ወልዴ ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጃገረዶች ኩርፍወን ሲጫወቱ መመልከታቸው እና በአሁኑ ወቅት ከዚህ እሴት ጋር ተያይዞ መፅሀፍ ለማሳተም እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። እንደእሳቸው ገለጻ ኩርፍወ ሁለት ኩነቶችን የያዘ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል መሰቀሉንና ሞትንም አሸንፎ ከመቃብር መነሳቱን ምክንያት በማድረግ የሚከወን ነው። በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሰሞነ ህመማት ሀዘንን በኩርፍወ እንጉርጉሮ ይገልፃሉ። ከህማማት መጀመሪያ እስከ ስቅለት ባለው ጊዜ በጉራጌ ለጀግና "ወርኮ" በሚባለው የሙሾ ሥርአት መሰረት ልጃገረዶች ሲያዜሙ ይስተዋላል። ከትንሳኤ እለት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ደግሞ የኩርፍወ አጨፋፈር፣ ዜማና ግጥሞች ለየት ባለ መልኩ ነው የሚቀርቡት። የጌታን መነሳት ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን የሚገልጹበት ነው። ከትንሳኤ እስከ ዳግማዊ ተንሳኤ የሚያዜሙት ዜማ ከሰሞነ ህማማት ልዩነት አለው። የሚበዛ ትዕይንት የሚበዛውና ጭፈራ ያለው መሆኑንም ነው የተናገሩት። ወይዘሮ ጀምበርነሽ አርጋ በምሁር አክሊል ወረዳ ግናብ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የኩርፍወ ጨዋታ በልጅነታቸው አምረውና ደምቀው ያሳለፉት ውብ ባህላዊ ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ የደረሰበተን ሞት እና ስቃይ በማስመልከት ሀዘናቸውን የሚገልጹበትና ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን የሚያሳየው ጫወታ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ከየቤታቸው ምግብ በማዋጣት በጋራ በልተውና ጠጥተው ያሳልፉበት ባህላዊ እሴት እንደ ነበር አስታውሰዋል። ይህ እሴት እንዳይጠፋ ዛሬ ላይ ለወጣት ሴቶች ለማሸጋጋር ልምዳቸውን እያጋሩ መሆኑን ነው የገለጹት። በወረዳው ግናብ ቀበሌ የምትኖረውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኩርፍወ ጨዋታ ላይ በንቃት እየተሳተፈች መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ወይዘሪት ሰላም ምትኩ ናት። የኩርፍወ ጨዋታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቶችን አጣምሮ የያዘ ልዩ ትዕይንት እንደሆነ አንስታ ጭፈራው፣ ዜማው እና ድራማዊ ትዕይንቱ ይበልጥ እንደሚስባት ተናግራለች። ከበሮዋን ይዛ፣ ማስጌጫ ቅጠሉን በወገቧ አገልድማ በዜማና ጭፈራ ወጣት ወንዶች በተገኙበት ከሰሞነ ህማማት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ትውፊታዊ ስርአት በጠበቀ መልኩ እንደምታሳልፍም አውስታለች። መንግስት ይህን ባህላዊ እሴት ለመታደግ እየሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ወይዘሪት ሰላም አመላክታለች። ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀት ክፍል ተጠሪና የቋንቋ መምህር ናቸው። ኩርፍወ በትዕይንት የተሞላና ለረጅም ዘመናት በቅብብሎሽ የተሻገሩ ግጥሞች አሉት ይላሉ። ልጃገረዶቹ ደብቀው የሚቀብሩትን አሚቾ (የኮባ ስር የውስጠኛው ክፍል) ለማግኘት የሚደረገው ግብግብ። የተደበቀው እንዳይገኝ ቦታውን ለማሳት የሚደረግ ጥረት። ወንዶች የተቀበረበት ነው ብለው የሚያስቡትን ቦታ ማሰሳቸው የትዕይንቱ አካላ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ወንዶች የተደበቀውን አሚቾ ፈልገው ካገኙት ዘመኑ ለእነሱ ገዳም እንደሚሆን ሲታመን ካላገኙት ደግሞ የሴቶች መልካም ዘመን ነው ተብሎ ይታሰባል። የኩርፍወ ጨወታ ባለቤቶች ልጃገረዶች እንደመሆናቸው መጠን ወደፊት ስለሚገጥማቸው ትዳርም ጭምር መልካምነት የተቀበረው አሚቾ የማሳየት ብቃት ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታመን እጅግ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ነው ጨዋታውን የሚያስኬዱት። ይህ ትዕይንት ዘርፈ ብዙ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሀላፊነቱን ለመወጣት ይሰራል ሲሉም ነው ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል የገለጹት።
ዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ የዓለም የክላሲካል ሙዚቃ አዋርድ ሽልማት አገኘ
Apr 16, 2025 544
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- ዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው “ብራቮ አዋርድ” በተሰኘ የዓለም የክላሲካል ሙዚቃ አዋርድ በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ ሽልማት አግኝቷል። ስነ ስርዓቱ በሞስኮ ጥንታዊው ቦልሾል ቴአትር አዳራሽ ተከናውኗል። በሽልማቱ ላይ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ከሆኑት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ህንድ፣ ሰርቢያ እና ቤላሩስ የተወጣጡ ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ደራሲዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የዘርፉ ተዋንያን ተገኝተዋል። በሁነቱ ላይ የታደሙት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ለዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ለተበረከተለት ሽልማት የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፒያኒስቱ ኢትዮጵያ ለሩሲያ ህዝብ በማስተዋወቅ ለተወጣው ሚና ያላቸውን አድናቆታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደር ገነት የሽልማቱ አዘጋጆች ኢትዮጵያ ለሙዚቃ እና ለባህል ልውውጥ እያበረከተች ላለው አስተዋጽኦ ለሰጡት እውቅና ምስጋና ማቅረባቸውን በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ከተሞችን ያነቃቃው የኮሪደር ልማት - የጭሮ ኮሪደርን በጨረፍታ
Apr 1, 2025 707
የጭሮ ወተት ገበያ ከከተማው ዋና መንገድ ግራና ቀኝ የሚካሄድ የተጨናነቀ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ በርካቶች ከማለዳ እስከ ማታ ገዥና ሻጮች ይገናኙበታል። የዚሁኑ የገበያ ማእከል እንቅስቃሴ ለመቃኘት የኢዜአ ሪፓርተር ወደ ስፍራው ባቀናበት ወቅት በገበያው ግራና ቀኝ በመንገዱ ዳርቻ ቁፋሮ እየተከናወነ ሲሆን ግብይቱም ሞቅ ደመቅ እንዳለ እንደቀጠለ ነው። በገበያው አመሻሽ ላይ ወተት እየሸጡ ካገኘቸው መካከል ወይዘሮ ሳርቱ አሊ፤ በአካባቢው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የመንገድ ስራው ሌት ተቀን የሚከናወን በመሆኑ የወተት ገበያው በምሽትም በርካታ ተጠቃሚዎች ስላሉት ለመሸጥ መገኘታቸውን ነገሩን። ከዚህ በፊት በተለይም በምሽት ገበያው ቀዝቀዝ ያለ እንደነበር አስታውሰው የኮሪደር ልማቱ ከተጀመረ ግን በየቀኑ በምሽት አራት ጀሪካን ወተት ሽጠው የሚመለሱ መሆኑን ጠቅሰው ''ልማቱ ስራም ገበያም ፈጥሮልናል'' ይላሉ። በጭሮ ከተማ ምሽት ጭምር የሚደራው የወተት ገበያ ከአስር ብር ጀምሮ በመግዛት የሚጠቀሙ መሆኑን ሸማቾችም ይናገራሉ። በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠራቸው እንዳለ ሆኖ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። በመሆኑም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ የፕሮጀከቶች መጓተት ችግር የተፈታበትና ሌት ተቀን የሚሰራበትን የስራ ባህል የፈጠረ መሆኑን ለማየት ችለናል። የኮሪደር ልማት ስራው በአጭር ጊዜ በጥራት ለማከናወን እየተደረገ ያለው የመንግስት የስራ አመራር እና በባለሙያዎች ጥረትም የሚደነቅ ነው። በጭሮ የኮሪደር ልማት በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ካሉ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች መካከል ወጣት ጀማል ኑሬ እና አምስት ጓደኞቹ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል አግኝቷል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራም በላይ በዩኒቨርሲቲ የቀሰሙትን የምህንድስና ትምህርት በተግባር ለመፈፀም ያስቻላቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ የኮሪደር ልማት ስራ ከዚህ ቀደም ሲከናወኑ ከነበሩት የመሰረተ ልማት ስራዎች የሚለየው በመንገዶች ግራና ቀኝ የሚከናወኑ የውበት ስራዎች እንዲሁም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ የእግረኛ መንገድ፤ የአደባባይ የድልድይና የመሳሰሉ ተዛማጅ ስራዎች በአንድ ላይ መያዙ ነው፡፡ በዚህም ከተማን ከማዘመን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ ማድረጉ ኮሪደር ልማቱ ልዩ ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡ ''የኮሪደር ልማት ስራው ሲጠናቀቅ እኔም ሙሉ ልምድና ዕውቀት አዳብሬ እወጣለው'' ያለው ወጣቱ ከገቢ በተጨማሪ እንደ ልምድ ማካበቻ እና መማሪያ በማየት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከጨርጨር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሰርቬይንግ ሙያ የተመረቀው የሱፍ ቀመር በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ሌላኛው ወጣት ነው፡፡ የኮሪደር ልማት በርካታ ስራዎች በአንድ ላይ የሚከናወንበት በመሆኑ ከሙያው በተጨማሪ ሌሎች ሙያዎችንም ለመቅሰም ያስችለዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችም የኮሪደር ልማቱን ጠቀሜታ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ችግሮች ጋር በማያያዝ ይገልጹታል፡፡ ጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ጅቡቲ የሚጓዙ ተሸከርካሪዎች የሚተላለፉባት ከተማ በመሆኗ የመንገዱ ጥበት ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር ተያይዞ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት መንገዱን በእጥፍ እያሰፋው በመሆኑ የትራፊክ ፍሰቱን የተሸለ ከማድረግ ባለፈ የኢኮኖሚ እንንቅስቃሴውንም በመጨመር ከተማዋን የሚያነቃቃ ነው ይላሉ በከተማው የቡርቃ ጭሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር እስማኤል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዕድሜ ጠገቧን ጭሮ ዳግም ወደ ቀድሞ ውበቷ እንደሚመልሳት ተስፋ አላቸው፡፡ ጭሮ ከተማ አሁን ቀን ወጥቶላታል የሚሉት አቶ ከድር ከዚህ በላይ ለከተማዋ የሚያስደስት ነገር ባለመኖሩ በተጠየቁት ሁሉ ልማቱን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ የጭሮ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጀማል ጎሳዬ እንዳሉት በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት እነዚህን ሁለት ዋና የአስፋልት መንገዶች ስፋት በእጥፍ በማሳደግ ወደ 40 ሜትር ከፍ የማድረግ ዓላማ አለው፡፡ ይህም የከተማዋዉን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከማሳለቱም በላይ ለፈጣን የንግድ እንቅስቃሴውም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት በከተማው ለሚገኙ ወጣት ባለሙያዎች ሙያቸውን የሚያዳብሩበት እና በልማቱ ለተሰማሩ ሌሎች ግለሰቦች የስራ ዕድል የተፈጠረበት በተጨማሪም በጥቃቅን የመንገድ ዳር የምግብ አገልግሎት ለሚሰጡ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተቆረቆረች ረጅም አመት ላስቆጠረችውና ለደከመችው ከተማ ዳግም መነቃቃት የፈጠረ እና የከተማዋን እምቅ ኢኮኖሚ በማንሰራራት ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ነዋሪዎቿ ገልጸዋል፡፡ የጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ለማረፍ የሚመርጧት ከተማ በመሆኗም ልማቱ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዘርፈ ብዙ እና የከተማዋን ተስፋ ያለመለመ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው፡፡ ለዚህ ነው ወይዘሮ ሳርቱ አሊ እና ሌሎች የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱን ለማገዝ የሚችሉትን ሁሉ ለመወጣት የተዘጋጁት።
የአፍሪካዋ ግዙፍ መዲና -አዲስ አበባ
Mar 31, 2025 950
አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የገበያ ባለሙያ እና የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ክሪስ ቦራቲን በዴይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ ቋሚ አምደኛ ነው። ክሪስ ቦራቲን በእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ኤክስፕረስ ላይ ስለ መዲናዋ በከተበው ጽሁፍ ላይ። ጋዜጠኛው በጋዜጣው ላይ በዓለም ላይ ሊጎበኙ ይገባቸዋል የሚላቸውን ምርጥ ቦታዎች የተመለከቱ ጽሁፎችን በአምዱ ላይ በስፋት ያቀርባል። የወቅቱ ለጉብኝት ተጠቋሚ ቦታ አዲስ አበባ ሆናለች። ክሪስ “Africa's huge mega-city that's one of the highest capitals in the world” በሚል ርዕስ በጋዜጣው ላይ ባሰፈረው የግል ምልከታ ጽሁፉ ላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ሜትሮፖሊታን ከተሞች አንዷ ናት ሲል ገልጿታል። በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኙት አፍሪካ ከተሞች የዓለምን ቀልብ ስበዋል። ለአብነት ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 355 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የአፍሪካ መዲናዋ ከተማ ትጠቀሳለች። ይህቺ መዲና ማናት ቢሉ በእንጦጦ ጎረብታ ግርጌ በተራሮችና ገመገሞች ዙሪያዋን ተከባ የምትገኘው አዲስ አበባ ናት። አዲስ አበባ ለምድር ወገብ የቀረበች ብትሆንም ቅሉ ከፍተኛ ቦታ ላይ በመገኘቷ ዓመታዊ ሙቀቷ በአማካይ 18 ዲግሪ ሴልሺየስ ገደማ ብቻ ነው። ይህም የዓለማችን 4ኛዋ ከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ከተማ ያደርጋታል። አዲስ አበባ እ.አ.አ በ2025 የህዝብ ብዛቷ ወደ ስድስት ሚሊዮን ይጠጋል። የህዝቡ ቁጥር በየዓመቱ ከአራት በመቶ ላይ እያደገ ይሄዳል። የታዋቂው የምርምር ተቋም ማክሮትሬንድስ መረጃ በዋቢነት አጣቅሷል። ይህም አዲስ አበባን በአፍሪካ እያደጉ ካሉ ፈጣን ከተሞች አንዷ ከመሆኗ ባሻገር በብዙ መመኛዎች እጅግ ግዙፏ ከተማ እንድትሆን እንዳደረጋት አመልክቷል። አዲስ አበባ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ የተቆረቆረች፣ እ.አ.አ በ1889 የኢትዮጵያ መዲና የሆነች ከተማ ናት። ከዛ ጊዜ በኋላ ዋንኛ የፖለቲካ፣ ባህል እና ኢኮኖሚ መናኸሪያ ሆናለች። የብሪሊያንት ኢትዮጵያ የአስጎብኚ ድርጅት ኩባንያ ባለሙያዎች አዲስ አበባ በርካታ ብዝሃ ማንነቶች ያላቸው ህዝቦች እና ዓለዐም አቀፍ ነዋሪዎች የሚገናኙበት ሲል ይገልጻታል። መዲናዋ ከሀገር በቀል ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ እና አረብኛም ይወሩባታል። ክሪስ አዲስ አበባ በርካታ ታዋቂ ስፍራዎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሏት ከተማ መሆኗንም ይገልጻል። በመዲናዋ ሊጎበኙ ይገባቸዋል ያላቸውን ቦታዎችንም በጽሁፉ ላይ ጠቆም አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም በብዛት ከሚጎበኙ ስፍራዎች አንዱ መሆኑንና ጎብኚዎች በዓለም ቀደምት ከሚባሉ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት መካከል አንዷ የሆነችውን ሉሲን የመጎብኘት እድል ያገኛሉ ሲል ተናግሯል። ፀሐፊው ሌላ በከተማዋ መጎብኘት አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ቦታዎች አንዱ የመስቀል አደባባይ ነው። አደባባዩ የተለያዩ ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን ጨምሮ ለተለያዩ ሁነቶች እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል። መስቀል አደባባይ በመስከረም ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች በደማቅ ሁኔታ የተከበረውን የደመራ መስቀል በዓል ማስተናገዱን አውስቷል። የአዲስ አበባ የከፍታ ጫፍ የሆነው እንጦጦ ተራራ ከባህር ጠለል በላይ የ3200 ሜትር ርዝማኔ አለው። ተራራው የእጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና የዳግማሚ ምኒሊክ የቀድሞ ቤተ መንግስት ይገኛል። ቦታው አዲስ አበባን ቁልጭ አድርጎ ለማየት እና ለረጅም የእግር እግር ጉዞ የሚሆኑ መንገዶችን ይዟል። ተጓዡ ፀሐፊ ቡና በኢትዮጵያውያን ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው መጠጥ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉንና በዚህ ረገድም አዲስ አበባ በርከት ያሉ ካፌዎች እና የቡና መጠጫ ስፍራዎች እንዷላት ለመታዘብ መቻሉን ገልጿል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዋና ገበያ ናት ያላት መርካቶ በአፍሪካ ሰፊው ክፍት ገበያ እንደሆነችም በጽሁፉ ላይ አስፍሯል። የደራ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደርግባት መርካቶ በህንጻዎች መካከል ባሉ የመተላለፊያ መንገዶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የመሸጫ ቦታዎች ከቅመማ ቅመም ጀምሮ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ሽያጭ ይከናወንባታል ሲል ተናግሯል። አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች ያለች ከተማ መሆኗን የገለጸው ጉምቱው የጉዞ ፀሐፊ የግንባታ እና የመሰረተ ልማት ስራዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ እንደሚገኝ በመግለጽ ሀተታውን ቋጭቷል።
በክልሉ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ ግንዛቤ እየጎለበተ ነው
Mar 29, 2025 362
ቦንጋ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ የታክስና ጉምሩክ ክበባት ተቋቋመው ግንዛቤ እያጎለበቱ መሆኑ ተገለጸ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አቀፍ የታክስና ጉምሩክ ክበብ ተማሪዎች የጥያቄና መልስ የውድድር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ። ከመሠረቱ የተገነባ ትውልድ ሀገርን ይገነባል" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ውድድሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ነው። በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንዳሉት፣ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ኑሯቸው ታማኝ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ የታክስና ጉሙሩክ ክበባት ሚና የላቀ ነው። ለዚህም በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች ክበባትን በማደራጀት ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተሳተፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ተማሪዎች ላይ መስራት ነገ ሀገርን የሚወድና ግብሩን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድ ማፍራት ነው' ያሉት ሀላፊው ግብርንና ታክስን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል። የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ ልማቶችና የዜጎች ፍላጎት ለመመለስ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ክልሉ ሲመሰረት ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ያልሆነ ታክስ እና ታክስ ያልሆነ ገቢ ሲሰበሰብ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዘንድሮ ወደ 10 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ገቢውን አሟጦ ለመሰብሰብ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመጠቀተም ስልጠናዎች እና ምክክሮች እየተደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ሕይወት፣ ከዚህም ዋናው የትምህርት ትቤቶች የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት መሆናቸውን ገልፀዋል። በየትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት ትውልዱ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደር ምንነትን እና ህጎች ላይ መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው እና ህገ-ወጥነት እና ኮንትሮባንድን የሚፀየፍ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል። የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ስራ የታክስ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋሶ አብዲሳ፣ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ለማሳካትም ግንዛቤ ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ግብር ከፋዩ፣ ማህበረሰቡና ትውልዱ ስለግብር ግንዛቤ እንዲሰፋ በትምህርት ቤት ደረጃም የተለያዩ ክበባትን በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የገቢ አሰባሰብ አቅም እንዲጨምር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በመድረኩ ላይ የክልል አመራሮች፣ ርዕሰመምህራን፣ተማሪዎችና ሌሎች ባለድሻዎች ተገኝተዋል።
የካቲት እና ኢትዮጵያ
Feb 26, 2025 713
በአየለ ያረጋል በየክፍላተ-ዓለሙ ዓመታት በወራት ሲመነዘሩ የራሳቸው መልክና መገለጫ ይኖራቸዋል። እንደየንፍቀ ክበቡ ወቅቶች የራሳቸው ጸባይ፣ ክዋኔ፣ ትውስታና ትዕምርት ይቸራቸዋል። ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባለ13 ወር ጸጋ ናት። ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመርም ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት አላት። በባሕር ሃሳብ ምሁራን የኢትዮጵያን ወቅቶች መጸው(መኸር)፣ ሐጋይ(በጋ)፣ ፀደይ(በልግ) እና ክረምት በሚል አራት ወቅቶችና አውራኅ ይከፍሉታል። ሁሉም አውራኅ፣ እያንዳንዱ ወራት በራሳቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቀለማትን ይጎናጸፋሉ። የወራቱ ቅላሜና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል። ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጳጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል። የኢትዮጵያ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። ከሁሉም ወራት ግን ከታሪካዊ ሁነቶች አንጻር የካቲት ልዩ ገጽታ አለው። አሁን ወቅቱ በጋ ወይም ሐጋይ ነው። ወርኅ የካቲትንም የሐጋይ አውራኅ ደማቁ ገጽ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ወርኅ የካቲትን ያክል በየታሪክ ህዳጉ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የወሰነ ወቅት ያለ አይመስልም። የካቲት የበጋ ወርኅ አልፎ የበልግ ጊዜ መግቢያ ነውና የቋንቋ ሊቃውንቱ 'የካቲት'ን ስያሜ 'የመከር ጫፍ መካተቻ፤ የበልግ መባቻ " ይሉታል። የመኸር ምርት የሚከተትበት ነው። በኢትዮጵያ ዘመን ስሌትም መንፈቅ ዓመት ወይም ስድስተኛው ወር ነው። ወርኅ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አፄ ሠርፀድንግልን፣ የአድያምሰገድ ኢያሱን ልጅ ዳግማዊ አፄ ዳዊት(አድባር ሰገድን)፣ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው” የሚባሉትን አፄ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን አንግሷል። በሌላ በኩል ኢማም አሕመድ ኢብራሂምን(ግራኝ አህመድ)፣ አፄ ሚናስን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ እቴጌ መነንን፣ ንጉስ ወልደጊዮርጊስን፣ ራስ ደስታ ዳምጠውን፣ ራስ አሉላ እንግዳን እና ሌሎች የዓድዋ ብሔራዊ የጦር ጀግኖችን አሳርፏል። ከኪነ-ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኅ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ብዙዎቹ ይስማማሉ። ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ እረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 ነበር። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና በሞት ያጣንበትም ወር ነው። የካቲት ታላቅ የሰማዕትነት ወር ነው፤ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት በወርኅ የካቲት ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጣሊያን ወራሪን በማሳፈር ለጥቁር ሕዝቦች ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድል የተቀዳጀችው በየካቲት መገባደጃ ወቅት ነበር። መልከ-ብዙው ዓድዋ ድል፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ተከውኗል። በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በዓድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፤ መትረየሶች አሽካክተዋል፤ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፤ ጎራዴ ተመዟል፤ ጦር ተሰብቋል። በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል። የዓድዋ ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነፀብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በዓድዋ ጦርነት የተመዘገቡ የይቅርታ፣ የፍቅርና የርህራሄ እሴቶች ከጥቁር ሕዝቦች ድልነት አሻግረው ለእያንዳንዱ ሰው ድል አድርገውታል። ከየካቲት ድሎች ዓድዋ ይድመቅ እንጂ ቅድመ-ዓድዋም ሆነ ድኅረ-ዓድዋ ጦርነት ደማቅ ድሎች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በወርኅ የካቲት የግብጽን ወረራ በጉራ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ፣ ድል ተቀዳጅታለች። የካቲት 12 ጭፍጨፋ እና የካቲት 23 የዓድዋ ድልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችና ተፃራሪ ታሪኮችን አስተናግዷል ይኸው ወርሃ የካቲት። የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ናቸው። ወርኅ የካቲት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ታላላቅ አብዮቶች፣ ታላላቅ ድሎች ተከውነውበታል። ለኢትዮጵያ ሕልውና እንደ ክብር የደም ግብር የቀረበበት፣ በየጋራና ሸንተረሩ የትውልድ መስዕዋትነት የተከፈለበት ጊዜ ነው። የካቲት የድልና የዕድል፤ የደምና ገድል ወር ነው። አሳዛኝም፤ አስደሳችም! የካቲትና የኢትዮጵያ ታሪክ ግንኙነት ድል የተገኘበት፣ መጥፎ ጠባሳዎችንም ያተምንበት ወቅት በመሆኑ ወርኅ የካቲትን በግጥምጥሞሽ የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። የካቲት ወር 2010 ዓ.ም በኢህአዴግ ላይ የነበሩ አመጾች የተባባሱበትና ፖለቲከኞች ከእሥር የተፈቱበት ነው። የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ለፓርቲው መልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡበት ነው። ከኢትዮጵያ አልፈው እንደ ዓድዋ ያሉ ለጥቁር ሕዝቦች ትግል አብነት የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ አብዮት የተካሄደበትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተወሰነባቸው ክስተቶችን ያስተናገደ ወር እንደሆነ ያነሳሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችን ማስተናገዱን አስተናግዷል። የወርሃ የካቲት ሁነቶች ተጻራሪ ታሪኮች እንደሆኑ የካቲት 12 እና የካቲት 23ን ለአብነት ይጠቀሳሉ። በርግጥ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ የመብትና ነፃነት ትግሎች የተስተናገዱበት ሲሆን በአገረ- አሜሪካ ጥቁሮች ለእኩልነትና ነፃነት የታገሉበት ወቅት በመሆኑ የታሪካቸው አካል በማድረግ ያከብሩታል። ለመሆኑ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ጋር የመጣባቱ ምስጢር ምን ይሆን? ለጉዳዩ አመክንዮ የሰጡ የታሪክ ምሁራን ወርሃ የካቲት ገበሬው የሚያርፍበት፣ ወንዞች ደርቀው ሰው የሚገናኝበት በመሆኑ እንዲሁም የጾም ወቅት መሆኑ የውጭ ጠላቶች አስልተው እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሰንበትና በፆም ወቅት የተደረገውን የአድዋ ጦርነት ያነሳሉ። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ገበሬ የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኃ የካቲት ለገበሬው ጥጋብ፣ ለመንግስታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር መሆኑን በማውሳት። ወርኃ የካቲት ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት፣ ሰርግ የሚሰረግበት፣ ሽፍታ የሚበረታበት ወቅት ነው። በ'ግብር ገብር! አልገብርም!' በሚል ግብግብ የገበሬ አመጽ የታየበት ወር መሆኑ ይወሳል። በሌላ በኩል ወቅቱ ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት ነው። በዚህም ተማሪዎችም ለንቅናቄ ይነሳሳሉ። በ1960ዎቹ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎችን ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና ያጣንበትም ወር መሆኑን ለምን ብለን ባንጠይቅም፤ ግጥምጥሙ ግን አጃይብ ያሰኛል። ኢትዮጵያ በየካቲት ወር ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ልትማር፣ ትውልዱም ታሪኩን ሊያውቅ ይገባል።
የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ተምሳሌት - አሊኮ ዳንጎቴ
Feb 20, 2025 662
ቀደምት ፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ህልማቸው በኢኮኖሚና ፖለቲካ የተሳሰረች፣ ራስ በቅ አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር። ጥሬ ዕቃዎቿ ላይ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የሆነች፣ ከውጭ ምርቶች ጥገኝነት የተላቀቀችና በምግብ ራሰ በቅ የሆነች፣ በበይነ-ቀጣናዊ የኢኮኖሚና ንግድ የተሳሰረች አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር ጽኑ መሻታቸው። ለዚህም አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ ማግስት ጀምሮ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል ስትራቴጂ ነድፈዋል። ለዚህ ደግሞ ግዙፍ አፍሪካ በቀል ኩባንያዎችን መስርቶ ምርታማነትን መጨመር፣ ሀገራትን በልማት ማስተሳሰር እና ብርቱ አህጉር አቀፍ የግል ዘርፍ መገንባት የሞከሩ አሉ። ባለሙያዎችም ከመንግስት መር ኢኮኖሚ ልማት ይልቅ ለዘላቂ ዕድገት የግል ዘርፍ መራሽ አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያሻ ይወተውታሉ። የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ትስስር በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ቢቀነቀንም አህጉራዊ የስምምነት ማዕቀፍ ሆኖ የወጣው በአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ ውሳኔ በፈረንጆቹ 2018 ነበር። ይሄውም አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ነው። ከ2021 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ስምምነቱን 54 አባል ሀገራት ፈርመዋል። 48ቱ ሀገራት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀውታል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ ታዲያ የግል ዘርፋን የሚያበረታታ ነው። ይህ ደግሞ በአፍሪ ሀገራት የሚገኙ ከበርቴዎች ከትውልድ ሀገራቸው ተሻግረው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት መልካም ዕድል ይዞ ይመጣል። ናይጄሪያዊው ከበርቴ አሊኮ ዳንጎቴ የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ ቁንጮ ናቸው። በፎርብስ መጽሔት መረጃ በተያዘው ዓመት የ67 ዓመቱ ቢሊየነር ዳንጎቴ 23 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሀብት አካብተዋል። ዳንጎቴ በአፍሪካ ኢንቨስመንትቻውን እያሰፉ ነው። ይህ እንቅስቃሴያቸው ደግሞ የራስ በቅና የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ተምሳሌቱ ቱጃር ያሰኛቸዋል። አሊኮ ዳንጎቴ ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ብለው ለኢትዮጵያ አዳዲስ መረጃዎችን አብስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር መክረዋል። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ያላቸውን የሲሚንቶ ምርት መጠን በዕጥፍ ለማሳደግ ወስነዋል። ከማዕድን(ሲሚንቶ) በተጨማሪም በሌሎችች ኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የአዋጭነት ገበያውን እየፈተሹ ስለመሆኑ እንዲሁ። ለአብነትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባትን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ዘርፎች ለመሰማራት አቅደዋል። በስኳር ልማት እንዲሁ። ናይጄሪያዊው የአፍሪካው ቀዳሚው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በሲሚንቶ፣ የነዳጅ ማፈላለግ፤ የማዕድን ማውጣት፤ የማዳበሪያ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዝ ስራዎች ላይ በስፋት ተሰማርተዋል። ናይጄሪያን ጨምሮ በ20 የአፍሪካ ሀገራት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት አፍስሰዋል። ለአብነትም በሲሚንቶ ዘርፍ ከናይጄሪያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋና እና ኮትዲቭዋር የሲሚንቶ ፋብሪካ ገንብተዋል። በናይጄሪያ ሌጎስ የአፍሪካ ግዙፉን የዳጅ ማጣሪያ ገንብተዋል። ስገንብተዋል። የነዳጅ ማጣሪያው ጋና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ነዳጅ ይልካል። ኩባንያው የአውሮፕላን ነዳጅን ወደ አውሮፓ ለመላክም አቅዷል። ከባድ ናፍጣ የመላክ እቅድ አለው። የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣረያ የአፍሪካ የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ ተስፋ ተሰንቆበታል። ኩባንያቸው በግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ በስኳር፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ መሰረተ ልማትና ኢነርጂ፣ ማዳበሪያ፣ በምግብ እና መጠጥ እና ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ዘርፎች በኢንቨስትመንት ተሰማርቷል። አሁንም አፍሪካን እያካለለ ነው። ቱጃሩ ዳንጎቴ በብረታ ብረት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጤና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎችም ያላቸውን ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የማስፋት ግብ ይዘዋል። የአሊኮ ዳንጎቴ እንቅስቃሴ ከቀደምት ፓን አፍሪካዊያን ህልም ጋር የተጣጣመ ነው። አፍሪካን በአፍሪካ በቀል ኢንዱስትሪ ማልማት፣ ስራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ ምርት ጥገኝነትን መቀነስ፣እሴት የተጨመረባቸወን የአፍሪካ ምርቶች ወደ ሌሎች አህጉራት መላክና አፈሪካዊያን ማስተሳሰር ለዚህ ሁነኛ አብነት ናቸው። ዳንጎቴን መሰል የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ለአህጉራዊ አጀንዳዎች ስኬት የግሉ ዘርፍ ምሰሶ በመሆኑ ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት የመንግስታት እና የግሉ ዘርፍ እጅና ጓንት መሆንን ይጠይቃል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሁልጊዜም ምክረ ሀሳብ ነው።
ጥቂት ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ
Feb 18, 2025 570
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አዲሱ የዓለም የፉክክር መድረክ እየሆነ መጥቷል። በልብወለድ ወይም በምናብ የሚታሰቡ ፈጠራዎች፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እውን እየሆኑም ይገኛሉ። እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት ያሳየው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአሁኑ ጊዜ ከሰዎች የቀን ተቀን ሕይወት ጋር እየተዛመደ መጥቷል። በዕለት ተዕለት የሰዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያዎች እንመልከት። 👉ቻት ጂፒቲ (ChatGPT): ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ሀሳቦችን ለማመንጨት እንዲሁም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዳ ነው። 👉ግራመርሊይ (Grammarly) : በፅሁፍ ውስጥ የግራመር (ሰዋሰው) እንዲሁም የስርዓተ ነጥብ ስህተቶች የሚያርም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው። 👉ካንቫ (Canva) : የተለያዩ ግራፊክስ ስራዎችን በቀላሉ የሚሰራልን መጠቀሚያ ነው። 👉ኦተር ኤአይ (Otter.ai) : በድምፅ የምንናገራቸውን ወደ ፅሁፍ (text) የሚቀይር መጠቀሚያ ሲሆን በአብዛኛው በትምህርት ቤት ውስጥ ለሌክቸር ይጠቀሙታል:: 👉ክራዮን (Craiyon) : ፅሁፍ ብቻ በመፃፍ የምንፈልገውን ፎቶ ለመፍጠር የሚረዳ መጠቀሚያ ነው። 👉ሬፕሊካ (Replica) : የኤ አይ ቻት ቦት ሲሆን ስለ አዕምሮ ህክምና የሚያማክር እንዲሁም የግል የአዕምሮ ህክምና ምክር የሚሰጥ ነው። 👉ማይክሮሶፍት ቱ ዱ (Microsoft To Do): የቀን ሥራዎቻችንን ለማቀድ እና ለማደራጀት የሚያግዝ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው። 👉ሄሚንግዌይ ኤዲተር (Hemingway Editor): የኦንላይን መፃፊያ ሲሆን አፃፃፋችን የጠራ እና ሀሳብን የያዘ እንዲሆን የሚያግዝ መጠቀሚያ ነው። 👉ጎግል አሲስታንት (Google Assistant): የቨርቹዋል አጋዥ መጠቀሚያ ሲሆን የቤት ውስጥ ስማርት መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር፣ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም አስታዋሽ በመሆን ያገለግላል። 👉ጎግል ፎቶ (Google Photos): ፎቶዎችን ለማደራጀት እንዲሁም ለመፈለግ የሚረዳ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው።
የአድዋን መንፈስ እንልበስ- ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ
Feb 18, 2025 525
ወርሃ የካቲት የጥቁሮች ወር ነው። ካሪቢያን ጥቁሮች በጥቁሮች የትግል ታሪክ ጉልህ አሻራ ያላቸው መሰረተ አፍሪካ ህዝቦች ናቸው። ካሪቢያን ዜጎች ኢትዮጵያን አብዝተው ይወዳሉ። ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አንድነትና ትግል ንቀናቄ አድዋን እንደ እርሾና እሴት ያወሳሉ። በቅርብ በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የታደሙት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ በሕብረቱ ጉባዔ ላይ ያደረጉት ንግግር በርካቶችን ያስደመመና ያስደነቀ ነበር። ከመልዕክታቸው ውስጥ ተከታዮቹን ሃሳቦች መዘናል፦ 👉 አድዋ በ24 ሰዓታት ውስጥ የአውሮፓዊያንን የራስ መተማመን ትምክህት ያሽመደመደ፤ የአፍሪካዊያንና ትውልድ አፍሪካዊያንን ልጆች መንፈስ ያጎመራ፣ መልካምነት ድል ያደረገበት፣ ብርሃን በጨለማ ላይ የነገሰበት ሁነት ነው። 👉 ዛሬ እናንተ ፊት የቆምኩት ይህን መንፈስ ታጥቄ ነው። አድዋ የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ ነበር። 👉 የአድዋ ድል ለነጻነትና ትግል እንድንነሳሳ ባቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነጻነት ድል እንድንቀዳጅ ምዕራፍ የከፈተ ድል ነው። አድዋ የአንድነት ውጤት ነው። 👉 እናንተ ፊት የቆምኩት የፓን አፍሪካዊነት ፈር ቀዳጆችን ሕልም ሰንቄ ነው። 👉 እኛ የካረቢያን ትውልዶች ከአፍሪካ ወንድምና እህቶቻችን ጋር ሕብረታችንን ማጠናከር እንሻለን። 👉 ትናንት በእኛ መከፋፈል ራሳቸውን ለበላይነት ያነገሱ ሃይሎችን እያሰብን አንድነታችንን አጠናክረን ነገን እንገንባ ወይም እንደ ትናንቱ ተነጣጥለን እንጥፋ የሚለው ምርጫ የኛ ፋንታ ነው። 👉 ስለዚህ የአድዋን መንፈስ ተላብሰን ከፊታችን የሚጠብቀንን መልከ ብዙ ፈተና በአንድነት እንጋፈጥ። 👉 ከአፍሪካ ውጭ የጥቁሮች ምድር ከሆነችው ባርባዶስ ተነስቼ ኢትዮጵያ የተገኘሁት ለአፍሪካና ካረቢያን ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ጥሪ ነው። 👉 ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥለሴ በዓለም ላይ አንደኛና ሁለተኛ መደብ ዜጋ መኖር የለበትም እንዳሉት ዛሬም በየትውልዱ በዓለም ላይ ኢ-ፍትሃዊነትና አግላይነት ስርዓት ይወገድ ዘንድ መታገል አለብን። ለዚህ ደግሞ የአድዋ ድልና የፓን አፍካዊነት መንፈስን እንልበስ። 👉 የጋራ መዳረሻችንን ለመቀየስ ከወሬ ይልቅ ተግባር ላይ አተኩረን በትጋት እንስራ። የትናንት ቁስልን እያከክን ሳይሆን ብሩህ ነገን ለመገንባት በጋራ እንቁም። 👉 ከፊታችን የተደቀነ አደገኛ ፈተና እንዳለ ተገንዝበን ፈተናውን በአንድነት ለመጋፈጥ ሞራላዊ ግዴታችንን እንወጣ። 👉 የአድዋን መንፈስ እንልበስ!
አዲስ አበባ በአሕመድ ሴኩ ቱሬ አንደበት
Feb 15, 2025 417
(62 ዓመታት ወደኋላ) ________________ አሕመድ ሴኩ ቱሬ ከቀደምት የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ነበር። በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር በነበረቸው የምዕራብ አፍሪካዊነቷ ሀገረ-ጊኒ የነጻነት ታጋይና ፖለቲከኛ ናቸው። ድሕረ ነጻነት የሀገሪቷ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል። በፈረንጆቹ አቀጣጥርግንቦት 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ከታደሙና አስደማሚ ንግግር ካሰሙ መሪዎች መካከል አንዱ ሴኩ ቱሬ ነበሩ። ለዛሬ ከፕሬዝዳንት አሕመድ ሴኩ ቱሬ አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በወቅቱ የገለጹበትን መንገድ እነሆ ብለናል። “…. አዲስ አበባ የታሪክ ክስተት መውጠኛ ስፍራ ናት። በአፍሪካ አወንታዊ የለውጥ ሽግግር ታሪክ መቁጠሪያ ነጥብ ሆናለች። ይህ ቅጽበት የአፍሪካ የተሟላ አርነት ማብሰሪያ ነው፤ የአፍሪካ ሰው ከነምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅሩ ነጻ የሚወጣበት። ይህ ስፍራ አፍሪካዊያን መንግስታትን ውጤታማ የሚያደርግ የፈጠራ ክዋኔዎች የመለኮሻ ዘመንም ነው። ለምን ቢሉ አፍሪካዊያን ወደ አንድ በመመጣት ህዝባቸውን ከሰቆቃ እንዲያገግም፣ የጋራ ስልጣኔ እንዲያንሰራራ፣ ሰብዓዊ እሴቶችና ባህላቸው ፈጣን እመርታ እንዲያመጣ ግብ የሰነቁበት ነውና። የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ነጻ መውጣት በጀግንነት ተዋግተዋል። የሕዝብ ነጻነት እንዲጠበቅ ብሎም ሰዎች ያለማንም የውጭ አካል ጣልቃገብነት መብታቸው ተከብሮ መዳረሻቸውን በራሳቸው ይተልሙ ዘንድ መንገድ የጠረጉ እና የራሳቸውን ጉዳይ በተሟላ ሉዓላዊነት እንዲፈጽሙ በተግባር ያሳዩ ህዝቦች ናቸው። ዛሬ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ የአፍሪካ ጉባዔ እየተካሄደ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ምንጊዜም በአፍሪካ ታሪክ ገጾች ውስጥ ደማቅ አሻራ አንብራለች። መላው የአህጉሪቷ ህዝብ የመለወጥ መሻቱን በቅጡ እንዲገነዘብ የተካሄደ ሁነት ነው። በ1885ቱ(በአውሮፓዊያን አቆጣጠር) የበርሊን ጉባዔ በኢኮኖሚ የጠገቡ ስርዓት አልበኛ የአውሮፓ መንግስታት ስልጣኔያቸውን ለማስፋፋት ሲሉ ያላቸውን ሀይል ተመክተው አፍሪካን እንደ ኬክ ቆራርሰው ሊቀራመቱ ተሰባስበው ነበር። ዛሬ ግንቦት 1963(በአውሮፓዊያን) ግን ምርጥና ሐቀኛ የአፍሪካ ልጆች ስለራሳቸው እና ስለእናት ምድር አፍሪካ ታምነው በንጹህ ማንነት የጋራ መዳረሻ መንገድ ለመቀየስ አዲስ አበባ ተሰባስበው እየመከሩ ነው። የአፍሪካ ትንሳኤዋ ዛሬ ነው። አፍሪካ በአንድ ነጠላ መንግስት ህጋዊ መልክ ትይዝ ዘንድ ልዩ መተዳደሪያ ሰነድ(ቻርተር) ማለትም አፍሪካዊያንን በወንድማማችነት፣ በማይናወጥ አጋርነት፣ በሰዎች መብትና ጥቅም፣ በሰላምና ነጻነት እንዲሁም በፍትህ መርሆች ውህደት የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ነው። የአዲስ አበባ ጉባዔ የዛሬን አፍሪካ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ላይ ብቻ የተወሰነም አይሆንም። አፍሪካ የዓለም አካል መሆኗን ልብ ይሏል። በዓለም ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰው ልጅ ሕይወት፣ ሰላም፣ ደህንንትና ዕድገት መንስኤ የሆኑ የጋራ ተግዳሮቶች ሁሉ አፍሪካን ይገዷታል…”።
የአፍሪካውያን የዛሬ ስራ ለነገ ተስፋቸው
Feb 14, 2025 438
በዓለም በትልቅነቷ በሁለተኝነት የምትጠቀሰው አፍሪካ የህዝብ ቁጥሯ በ2024 (እ.ኤ.አ) አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። አህጉሪቷ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ የሰጡትን የሚያበቅል ለም አፈር ያላት፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ መሆኗም በብዙዎች የተመሰከረለት ነው። ይሁንና አህጉሪቷ ለበርካታ ዓመታት በጦርነት፣ በበሽታ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ስትጠቃ ኖራለች። ከተመሰረተ 50 ዓመታትን የተሻገረው የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት "እ.ኤ.አ በ2063 መሆን የምንፈልገው" ብለው የተለያዩ እቅዶችን ነድፈው ወደ ተግባር ገብተዋል። ''እኛ አፍሪካውያን በ2063 መሆን የምንፈልገው'' በሚል ባሰፈሩት አጀንዳ በርካታ የአህጉሪቷ የልማትና የብልጽግና ትልሞች ተቀምጠዋል። በዚህም ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተረጋገጠባት፣ በልማትና በኢኮኖሚ የተዋሃደች፣ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ የጎለበተ አህጉር መፍጠር ይገኙበታል። በኢኮኖሚ የፈረጠመች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹና አስተማማኝ አህጉር የማድረግ እቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረዋል። የአገራቷ መሪዎችም እነዚህን የልማት እቅዶች ከየአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለገቢራዊነቱ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። አፍሪካ በ50 ዓመታት ለማሳካት የያዘችው አጀንዳ ሁሉን አቀፍ የልማት እቅድ፣ ከዓለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታና በአፈጻጸም ቁርጠኝነት ክፍተት እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያለመመዝገቡም ይገለጻል። መሪዎቹ ይህን እቅዳቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የነበራቸው ቁርጠኝነት ማነስ፣ የውጭ ተጽእኖ ማየል ዕቅዶቹ እንዳይሳኩ ምክንያት ሆነዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖን የምታስተናግደው አፍሪካ አሁንም ቢሆን ተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍን እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዜጎቿን እየፈተኑ ይገኛሉ። የምርትና ምርታማነት እጥረት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት አጀንዳዋን ለማሳካት ብዙ ይቀራታል። አፍሪካ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመሳካት ያቀደችውን በተግባር ለማጠናቀቅ 38 ዓመታት ይቀሯታል። በዚህ ረገድ የተወሰኑ አገራት የተሻለ ኢኮኖሚ በማስመዝገብ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና፣ መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂን በማሟላት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገባቸው ይነገራል። በአህጉሪቷ በተመሰረቱ የተለያዩ ጥምረቶች አገራት እርስ በእርስ በመሰረተ ልማትና በሃይል በማስተሳሰር ረገድ መልካም የሚባሉ ጅምሮች ታይተዋል። ይሁንና የዓለምን ተለዋዋጭ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች በአግባቡ በመረዳት የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መቀየር፣ ሰላማዊ፣ በኢኮኖሚ የዳበረች፣ በዓለም መድረክ እኩል ድምጽ ያላት አህጉር የመፍጠር እቅዱን እውን ለማድረግ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው። እያንዳንዱ አፍሪካዊ ዜጋ አጀንዳ 2063ን በአግባቡ ተገንዝቦ ለትግበራው የድርሻውን መወጣት እንዲችልም በቂ የግንዛቤ ስራ ሊሰራ ይገባል። የአፍሪካ መሪዎች በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦች በትክክል እንዲተገበሩ ዜጎቻቸውን አስተባብረው በቁርጠኝነት መስራት ግድ ይላቸዋል። የአጀንዳ 2063 እውን መሆን ዋነኛ ተጠቃሚ የሚያደርገው የአህጉሪቷን ዜጎች እንደመሆኑ እቅዱን ለማሳካት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። የአፍሪካ አገራት የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከርና የአህጉሪቷን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ በአንድ ጥላ በሚያሰባስባቸውና በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ይገናኛሉ።
ኢትዮጵያ እና የሕብረቱ ወሳኝ አካል የሆነው ምክር ቤት
Jan 17, 2025 1088
የአፍሪካ ሕብረት ቁልፍ ተቋም ነው- የሕብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት። የፊታችን የካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ በሚደረገው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከሚቀረቡ ዝርዝር አጀንዳዎች አንዱ የዚህ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እንደሚሆን ይጠበቃል። ኢትዮጵም በቅርቡ ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ፍላጎቷን ይፋ አድርጋለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ያላትን መሻት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች አብስረዋል። ለመሆኑ የሕብረቱ የሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ስራው ተልዕኮና ሚና ምንድነው? አባላቱም እንደ ሀገር ምን ፋይዳ ይሰጣቸው ይሆን የሚለውን እንናስቃኝዎ! የምክር ቤቱ ለመመስረቻ ጥንስስ የተጠነሰሰውና የማቋቋሚያ ሕግ ማዕቀፍ የጸደቀው በአውሮፓዊያኑ 2002 በደርባን(ደቡብ አፍሪካ)በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ስብስባ ነበር። በአውሮፓዊያኑ ታኅሣሥ 2003 ወደ ስራ ገባ። ባለፈው ዓመት (ግንቦት 2016 ዓ.ም) ምክር ቤቱ 20ኛ ዓመት የምስረታ ቀኑን በአዲስ አበባ አክብሯል። ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው። በአህጉሪቷ ለሚከሰቱ ግጭቶች ጊዜውን የጠበቀ እና በቂ ምላሽና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ (African Peace and Security Architecture) ቁልፍ ምሰሶ ነው። የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተልዕኮና ሚና ከአወቃቅር አኳያ ምክር ቤቱ ዕኩል ድምጽ ያላቸው 15 አባል አገራት ይኖሩታል። አባላቱም በሕብረቱ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ይመረጣሉ። በመሪዎች ጉባዔ አባልነታቸው ይጸድቃል። ከአባላቱ መካከል አምስቱ ለሶስት ዓመታተ፤ ቀሪዎቹ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስልጣን አላቸው። ምክር ቋሚ አባል አገር የለም። የአባልነት ጊዜ የጨረሱ ሀገራት ግን ድጋሚ የመመረጥ መብት አላቸው። አባላት የሚመረጡት ግን በቀጣናዊ ውክልና እና በተራ ቅደም ተከተል መርህ ነው። ይኼውም ማዕከላዊ፣ ምሥራቃዊ፣ ደቡባዊ እና ሰሜናዊ ቀጣናዎች ሶስት አባል ሀገራት ሲሆኑ የምዕራብ ቀጣና ግን አራት አባል አገራት ይኖራቸዋል። በምክር ቤት ሕገ ደንብ መሰረት ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ይሄውም የአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን በማስተዋወቅና በማረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ፣ በቀጣናዊና በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር እና በሰላም መፍጠር ውስጥ ያለው ሚና፣ ቀጣናዊና አህጉር አቀፍ የግጭት መፍቻ ኢኒሺቲቮች ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት እና ኃላፊነት ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ፣ ለሕገ መንግስት አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብቶች ያለው ከበሬታ እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት የፋይናንስ መዋጮ ግዴታዎች ያለው ተገዢነት እና ቁርጠኝነት አንድን አገር አባል ሆኖ እንዲመረጥ የሚያስችሉት መስፈርቶች ናቸው። ምክር ቤት ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር በመጣመር ከስር የተመላከቱ ስልጣንና ተግባራቱ ተሰጥቶታል። . ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊያመራ የሚችል የግጭት አዝማሚያን መተንበይ፣ አስቀድሞ በመከላከልና የግጭት መንስዔዎችን ለይቶ ፖሊሲ መቀየስ። የጦር ወንጀሎች፣ ዘር ማጥፋት እና የሰብዓዊነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለመሪዎች ጉባዔ ሕብረቱን ወክሎ ጣልቃ መግባት የሚችልበትን ምክረ ሀሳብ ያቀርባል። . ለግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ በማስቻል ሰላም መገንባት ላይ ይሰራል።የአፍሪካ ሕብረት አጠቃላይ የጋራ የመከላከያ ፖሊሲ ይተገብራል። . ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ፈቃድና ስምሪት ይሰጣል፤ የሰላም አስከባሪ ኃይል የስራ ኃላፊነት ጨምሮ ተልዕኮውን የተመለከቱ መመሪያዎችን ያወጣል። . በአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ኢ-ሕገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሲኖር ማዕቀብ ይጥላል። . የፀረ-ሽብርተኝነትን ዓላም አቀፍ ስምምነቶች የአባል ሀገራት ትግበራን ይከታተላል። በመልካም አስተዳደር፣ በሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነጻነቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ያደርጋል። ቀጣናዊና አህጉራዊ የተቀናጀ የሰላምና ደህንነት አሰራርን መፈጸሙንም እንዲሁ። በጦር መሳሪያ ቁጥጥርና ትጥቅ የማስፈታት የሕግ ማዕቀፎችን ትግበራ ይደግፋል። . የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራትን ነጻነት እና ሉዓላዊነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ የኃይል እርምጃዎችን በመመርመር እርምጃ ይወስዳል። . በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ለሰብዓዊ ድጋፍ ያስተባብራል። አፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሰላምና ደህንነት የስራ ክፍል ውስጥ የሚገኘው የምክር ቤቱ ሴክሬተሪያት ለምክር ቤቱ የኦፕሬሽን ስራዎች የቀጥታ ድጋፍ ያደርጋል። ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ “Panel of the Wise” በተሰኘው የአፍሪካ ሕብረት የማማከር አደረጃጀት፣ በአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እና የሕብረቱ የሰላም ፈንድ ድጋፍ ይደረግለታል። በምክር ቤቱ በስሩ ያሉት ወታደራዊ አባላት እና የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴዎች፣ የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ማዕቀፍ (APSA)፣ የአፍሪካ የሴቶች ግጭት መከላከል እና የሰላም ድርድር ኔትወርክ (FemWise–Africa) እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ማስከበር ተልኮዎች ሌሎች ደጋፊ አካላት ናቸው። ምክር ቤቱ ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት እና ከሌሎች ቀጣናዊ አደረጃጀቶች ጋር ግጭትን አስቀድሞ መከላከል፣ አስተዳደር እና መፍትሄ ላይ በጋራ ይሰራል። ከተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና ሌሎች መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም ፓን-አፍሪካ ፓርላማ እና የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች ጋር በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይም በትብብር እየሰራ ይገኛል። የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊነቶች፣ አደረጃጀቶች እና የቅንጅት አሰራር ማዕቀፎች በአህጉሪቷ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁልፍ የውሳኔ ሰጪነት አቅም የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ እና ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ለመወዳደር የፈለገቸው ለሶስት ዓመት (በአውሮፓዊያኑከ2025 እስከ 2027) ድረስ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች ለአፍሪካ የዋለችውን ታሪካዊ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት በውሳኔ ሂደቱ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በርግጥ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ያላት ቁልፍ ሚና ተገቢነቱ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት ሰርታለች። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ሄኖክ ጌታቸው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና ማገልገሏን ያስታውሳሉ። ምክር ቤቱ የአሁኑን ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት በቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ማዕቀፍ ከእ.አ.አ 1993 እስከ 2000 ባለው ጊዜ አባል ሆና ማገልገሏን ገልጸዋል። በአፍሪካ ሕብረት ደግሞ በአውሮፓዊያኑ ከ2004 እስከ 2010 እንዲሁም ከ2014 እስከ 2016 አገልግላለች። ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና ብትመረጥ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿንና ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ እና አንጻር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንደምታገኝ ሄኖክ(ዶ/ር) ይናገራሉ። የምክር ቤቱ አጀንዳዎች ከብሔራዊ ጥቅሞቿ ጋር አጣጥሞ ለመሄድና ፍላጎቶቿን የሚጻረሩ ጉዳዮች ለመከላከል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላትም በማንሳት። የአፍሪካ ዋንኛ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አብዛኛውን ትኩረቱን አፍሪካ ቀንድ ከማድረጉ አንጻር ኢትዮጵያ በአካባቢው ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት ከፍተኛ ተመራማሪው። ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስብ መሆኑ ያሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩሏን ድርሻ መወጣት እንደምትችልም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ አባልነት የሕብረቱ የመመስረቻ ቻርተርና የህግ ማዕቀፎች እንዲጠበቁ፣ አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማራመድ፣ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈንና በቀጣናው ከምትጫወተው ሚና አንጻር በርካታ ጠቃሜታዎችን እንደምታገኝ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን የተሻለ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንዳላት ያነሳሉ። ለምን ቢባል አንድም ኢትዮጵያ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በላይበሪያ፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በሰላም ማስከበር ተሳትፎ በማድረግ ያላት ልምድ ነው። አንድም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ መሆኗና ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ የነበራት ግልጋሎት እንደ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንድታገኝ ያስችላታል። አባልነቷን ለማረጋገጥ ግን ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችና ሌሎች የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይጠበቃል ይላሉ። ምከር ቤቱ በሕብረቱ የሰላም እና የደህንነት ምክር ቤት የአፍሪካ የሰላምና ደህንት ጉዳዮች ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል በመሆኑ አባል ብትሆን ካላት ታሪካዊ አበርክቶ አኳያ ይበልጥ ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና እንደምትጫወት ዕሙን ነው።
ወንዞቿን ከብክለት ወደ ትሩፋት ለመለወጥ የተነሳችው አዲስ አበባ
Jan 13, 2025 914
አዲስ አበባ ከተቆረቆራች አንድ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ልትደፍን ጥቂት ዓመታት ይቀራታል። ከተማዋ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ዑደት አስኳል ሆና ሁሉን አስተናግዳለች። ዕድል ቀንቷት ከኢትዮጵያዊያን አልፋ የአፍሪካዊያን መዲና ሆናለች። ዘመን ችሯት የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል። ከአፍሪካ ወደ ዓለም፤ ከዓለም ወደ አፍሪካ መግቢያና መውጫ በር ናት። የሀገሪቷ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት የስበት ማዕከል ናት። በፍጥነት ያደገችና ነዋሪቿን ያበዛች፤ ምጣኔ ሀብትን ያጎለመሰች ከተማ ናት። ዳሩ የከተሜነት መዋቅራዊ ፕላኗ አኳያ ውስንነቶች እንደሚስተዋልባት በባለሙያዎች ዘንድ ይነሳል። ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ዘመን ተሻጋሪ፣ ለኑሮ ምቹና ስሟን የሚመጥን የክትመት ዕቅድ ይዛ ባለመጓዟ ውበትም፤ ኑረትም፣ ምቾትም አጉድላለች። በጽዳትና ውበቷ ረገድ በእንግዶቿም ዘንድም ለትቸት ተጋልጣ ታውቃለች። ከአዲስ አበባ ድክመቶች አንዱ የብዙ ወንዞች ባለቤት ሆኗ አንዱንም እሴት ጨምራ ወደ ሀብትትነት አለመቀየሯ ነው። ፈሳሽ ወንዟን አልምታ በውበት አለመፍሰሷ። በመዲናዋ ከ76 ያላነሱ ዋና እና ገባር ወንዞች ይገኛሉ። ዳሩ በየዘመኑ የከተማ ልማት ዕቅዶች የወንዝ ዳርቻን ታሳቢ ባለማድረጋቸው ወንዞቿ ለገጽታዋ ውበት ሳይሆን ሳንካ ሆነዋታል። የከተሜነት ወጓ ከወንዞቿ ልማት ጋር አልተመራም። የሰዎች አሰፋፈር ከዓለም አቀፋዊ የከተሜነት ልክን አልጠበቀም። ይህ ደግሞ ወንዞች ለነዋሪዎቿ ጠንቅ እንጂ ትሩፋት እንዳይሆኑ አድርጓል። በርካታ ሀገራት ከተሞች ጥቂት ወንዞቻቸውን ለጌጥም፤ ለበረከትም አውለዋል። ባለበዙ ወንዞች ባለቤቷ አዲስ አበባ ግን "ጽድቁ ከርቶ..." እንዲሉ ከወንዞቿ ጥቅሟ ቀርቶ፤ ጠንቋ በዝቶ ቆይታለች። ወንዞቹን ለምተው ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት ከመዋል ይልቅ ለብክለት ተጋልጠው ለሕዝብ ጤና ጠንቅ ነበሩ። በክረምት ወራትም ጎርፍ እየተሞሉ ነዋሪዎችን ለአደጋ አጋልጠዋል። እነሆ አሁን የዘመናት ክፍተቷን ለመቅረፍ ተነስታለች። ከተማ አቀፍ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ተጀምረዋል። የመዲናዋን ወንዞች ከሕዝብ ጤና ጠንቅነት ወደ ጥቅም የመለወጥ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከሚፈሱ ወንዞች መካከል እስካሁን አንድ ወንዝ ለቱሪስት መስህብነት፣ ለመዝናኛነትና ለሌላ አገልግሎት ለማዋል የተሰራ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ ነው። የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበርካታ ሀገራት ከተሞች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ወንዞችን አልምተው ለቱሪስት መነሃሪያ እንዲሆኑ በማስቻል ለቱሪዝም ዘርፍ እመርታ ወሳኝ ድርሻ እንዲይዙ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። አዲስ አበባ ግን በርካታ ወንዞችን ታቅፋ ይህን መልካም ዕድል አልምታ ሳትጠቅም በመቆየቷ ቁጭት የሚፈጥር ጉዳይ እንደሆነ ያነሳሉ። እናም እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የህብረተሰቡን አኗኗር ብቻ ሳይሆን ለተፋሰስ ልማትም ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ወንዞች ከጠንቅነት ወደ ህዝብ ጥቅምነት የመለወጥ ስራዎች እንደቀጠሉ ከንቲባዋ አብስረዋል። በዚህም አዲስ አበባ ካሏት 76 ወንዞች መካከል አንድ ሶስተኛው ትልልቅ ወንዞቿ ለቱሪስት መዝናኛ አገልግሎት መዋል የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ከነዚህም መካከል እስካሁን ሁለት ወንዞችን በወንዝ ዳርቻ ልማት በማስገባት ወደ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የመለወጥ ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል። በትናንትናው ዕለት የከተማዋ አመራሮች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶችን ጎብኝተው ነበር። ከተጎበኙ የከተማ ልማት ስራዎች መካከል የቀበና ቁጥር-1 እና 2 እንዲሁም ከእንጦጦ-ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት ይገኝበታል። ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የወንዝ ዳርቻ ልማት ከብክለት ነጻ አካባቢን በመፍጠር፣ ከተማዋን ጽዱና አረንጓዴ በማድረግና በሽታን በመከላከል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። የእንጦጦ-ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት የተለያዩ ፓርኮችን በማስተሳሰር በፕላን የተገነባ ከተማን እውን ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ በማብራራት። በቀበና ቁጥር 2 እንዲሁም ከእንጦጦ- ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ አፍንጮ በር አካባቢ የመጓተት ችግሮችን በመቅረፍ ስራው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 70 ደረጃ እና 40 ደረጃ ታሪካዊ ቅርስነታቸውን ጠብቀው እየታደሱ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከዕይታ ተደብቆ የቆየውን የራስ መኮንን ሀውልት ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ዕድሳት ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ፒያሳ አካባቢ እየተሰራ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሩጫ፣ የሳይክል፣ የመዋኛና ሌሎች ቦታዎችን ነው። ልማቶቹ አለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችንና ሁነቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ እንደሆኑ ከንቲባዋ በጉብኝቱ ወቅት አብራርተዋል። የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ፓርኪንግ፣ የታክሲ ተርሚናል፣ ሱቆችንና ሌሎች ልማቶችን አካቶ እየተሰራም ነው። ፕላኑን የጠበቀ ዘመናዊ ከተማን እውን የሚያደርግ ከንቲባዋ ጠቁመዋል። የወንዝ ዳርቻን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የልማት ስራዎች ዘመናዊ ከተማን ያሟሉ በመሆኑ ለአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ይጨምራሉ።