ቢልጌትስ ታላቁን የኢትዮጵያ የክብር ኒሻን እንዴት ተቀዳጁ?

በሀገረ አሜሪካ ሲያትል ውስጥ ተወልደው ያደጉት ቢል ጌትስ የዕውቁ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮ ሶፍት መስራችና ባለቤት ናቸው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ከአጋራቸው ፖል አለን ጋር የመሰረቱት ማይክሮሶፍት ቢልጌትስን ከምድራችን ግንባር ቀደም ቱጃሮች አንዱ አድርጓቸዋል።

ቢልጌትስ ከኮምፒዩተር ቴክኖሎጂው ማይክሮሶፍት ባሻገር በፈረንጆቹ 1990 በቀድሞ ስሙ ‘ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሸን’ በአሁኑ መጠሪያው ‘ጌትስ ፋውንዴሽን’ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ የሰው ልጆች ሁሉ ዕኩል ዕድልና የተሻለ ነገ ይኖራቸው ዘንድ በተለይም በግብርና እና በጤናው ዘርፍ መልከ ብዙ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ተግብሯል። 

የጌትስ ፋውንዴሸን ተልዕኮ “ሁሉም ሰው ጤናማና ምርታማ ሕይወት የሚመራባት ምቹ ዓለም መፍጠር” የሚል ነው። የጌትስ ፋውንዴሽን በስፋት ድጋፍ ካደረገባቸው ሀገራት መካከል ታዲያ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2000 ስራ የጀመረ ሲሆን እ.አ.አ በ2012 ቢሮውን በአዲስ አበባ በመክፈት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እና ለጋሾች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል። 


 

ኢትዮጵያውያን ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸውና የኑሮ ዘይቤያቸው እንዲሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን መደገፍ የፋውንዴሽኑ ግብ ነው።

ከለጋሾች በተገኘ ድጋፍ የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ለውጦች መታየታቸውንና በእናቶችና ህጻናት ጤና፣ ትምህርት እና ግብርና ምርታማነት አመርቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያመለክታል።

ፋውንዴሽኑ ጥረቶቹን ከኢትዮጵያ መንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር በማሰናሰን በስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት፣ በፋይናንስ አካታችነት እና በንጽህና አጠባበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል።

ለዚህ ተግባሩም በኢትዮጵያ ከ777 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ከጌትስ ፋውንዴሽን ስራዎች መካከል በጤናው ዘርፍ የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም አማካኝነት በገጠራማ አካባቢዎች ዜጎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን እንዲያገኙ ማስቻል ይጠቀሳል። የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የሳምባ ምች እና ወባ በሽታዎችን በምርምር፣ በገንዘብ ድጋፍ እና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለመከላከል እየሰራ ነው።

በግብርና ዘርፍ ደግሞ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ አላማ ላነገበው የስንዴ ክላስተር እርሻ ኢኒሼቲቭ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን አምራቾች ከቤት ፍጆታነት ወደ ገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያገኙ ደግፏል። 

አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች የዶሮ ጫጩቶችን ለሚያቀርበው የግል ኩባንያ ኢትዮ ቺክን ድጋፉን ለግሷል።

የፋውንዴሽኑ መስራችና ሊቀመንበር ቢል ጌትስ ባሳለፍነው መስከረም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የክላስተር የስንዴ ማሳዎችንና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ስራዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ቢል ጌትስ ከጉብኝቱ በኋላ ባሳተሙት መጣጥፍ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በግብርናው ዘርፍ የመጣው እመርታ እንዳስደነቃቸው አስፍረዋል።በኢትዮጵያ ያልታረሱ ማሳዎችን በማረስ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቅምና ሌሎች የሪፎርም ስራዎችን በመተግበር በቅርብ ዓመታት ተምሳሌታዊ የሆነ ምርትና ምርታማነት መመዝገቡን ገልጸው ነበር።


 

በዚህም ፋውንዴሽኑ ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያን ግብርና ዘርፍ በመደገፉ ትልቅ ኩራት ይሰማዋል ብለው ነበር ቢል ጌትስ ።

ጌትስ ፋውንዴሽን በሌሎች የልማት ኢኒሼቲቮች ለአብነትም የኢትዮጵያ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ በፋይናንስ አካታችነት፤ በመረጃ አሰባሰብ፣ ምርምር እና ፖሊሲ ትግበራ የሀገር በቀል አቅሞችን የመገንባት ስራዎችን ይደግፋል።

ኢትዮጵያም ጌትስ ፋውንዴሽን በተለያዩ መስኮች ላለፉት 25 ዓመታት ላከናወናቸው ስራዎች እውቅና ሰጥታለች።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን ታላቁን የክብር ኒሻን ለቢል ጌትስ ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቤተመንግሥት በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ሸልመዋል።

ይህ የከበረ ሽልማት የጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተፅዕኖዎችን ያከበረ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በንግግራቸው ለቢል ጌትስ ፋውንዴሽን የ25 ዓመታት አሸጋጋሪ ሥራዎች ምስጋና አቅርበዋል።
 
ቢል ጌትስ ከቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅነት ወደ በጎ አድራጊነት ያደረጉትን ጉዞ በማውሳትም ዝቅ ብሎ በማገልገል፣ በአክብሮት እና በእኩልነት እምነት ላይ የተመሠረተውን አገልግሎታቸውን አድንቀዋል።

ፋውንዴሽኑ በጤና፣ በግብርና፣ በዲጂታል መታወቂያ የሚያደርገው ብርቱ ድጋፍ ብሎም በመከባበር ላይ የተመሠረተ የፋውንዴሽኑ የትብብር ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወስቷል።

ቢል ጌትስ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ የሰዎችን ጤናና ምርታማነት ለማሻሻል በፋውንዴሽናቸው አማካኝነት ላደረጉት በጎ ድጋፍ ኢትዮጵያ የክብር ኒሻን ሸልማቸዋለች። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም