በቻይና ይህም አለ! - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና ይህም አለ!

በአብነት ታደሰ
በርግጥ ከዓለማችን የጥንት ስልጣኔ ምድሮች አንዷ ናት- ቻይና። በታሪክ ገጾች ‘የግኝት ምድር’(Land of Invention) የሚል ተቀፅላ የሰፈረላት የሺህ ዘመናት ባለታሪክ ሀገር።
የጥንት ቻይኖች አያሌ ‘ግኝቶችን’ ለዓለም አካፍለዋል። ወረቀት ፈብርከው ዘመናቸውን ጽፈዋል፣ ማተሚያ ቁስ ፈጥረው አትመዋል፤ ኮምፓስ ፈልስመው አቅጣጫ ጠቁመዋል።በ221 ዓመተ-ዓለም አንድ ወጥ ስርወ መንግስት መስርተው በሀገረ መንግስት የታሪክ ዑደት ከፍታንም ዝቅታንም አይተዋል። በቻይና አያሌ ስርወ መንግስታት ተፈራርቀዋል።
ቻይናውያን ክፉውንም ደጉንም ችለው አልፋዋል። የሕዝቡ ጽናት፣ ጥበብ፣ ቱባ ባህል፣ ታሪክና ብልሃት በቻይና ግንብ ይመሰላል። ግንቡም ዝም ብሎ የጡብ ክምር አይደለም፤ የመሰረተ-ጽኑነታቸው ትዕምርት(symbol) እንጂ።
ሲሶውን ሕዝቧ በያንግትዝ ወንዝ ተፋሰስ ጉያ አቅፋ፣ ጥንተ ማንነቷን ሸክፋ ዕልፍ ዘመናትን ተሻግራለች። የቻይና ስርወ መንግስታት ከስመው የዛሬዋ ኮሚኒስት ሪፐብሊክ ቻይና ከተመሰረተች ገና አንድ ምዕተ ዓመቷ ነው። ቅድመ ልደተ ክርስቶት በ221 ዓመተ-ዓለም የተመሰረተው ወጥ-ስርዎ መንግስት በመልከ ብዙ ምክንያቶች ተዳከመ። በፈረንጆቹ 1912 የመጨረሻው የቻይና ስርዎ መንግስት ተንኮታኮተ።
ዘመናዊቷ የቻይና ሪፐብሊክ በዚህ ዘመን ተመሰረተች። ዳሩ ለውጡ አልጋ በአልጋ አልሆነም። ለሺህ ዘመን የጽኑ ስርዓተ መንግስት ባለቤቷ ሀገር ቻይና በአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ታመሰች። ወረራንም፣ ዕልቂትንም አስተናገደች።
በዘመኑ ማኦ ዘዶንግ የሚባል ባለራዕይ መሪ በቻይና ምድር ተነሳ። አርቆ አሰበ፤ ሀሳቡንም አሰረጸ፤ በዓላማ ጸንቶ ክፉ ዘመን ተሻገረ። ማኦ እና ተከታዮቹ ለቻይና ትንሳኤ ታተሩ። በጽናት ታገሉ። ለመስዕዋትነት ቆርጠው ተነሱ፤ ዋጋም ከፈሉ።
በአውሮፓዊኑ ዘመን አቆጣጣር በ1949 የዛሬዋን የቻይና ሕዝባዊ ኮሚኒስት ሪፐብሊክ መሰረተ። ሃሳቡን ወደ ፖሊሲ ቀየረ፤ ተገበረውም። ቻይናን በኢንዱስትሪና ግብርና ምርት በንቅናቄ የማስፈንጠር ፕሮግራምንም (Great Leap Forward) ገቢራዊ አደረገ። ሆኖም ፖሊሲው በአንዴ ፍሬ አላፈራም። በወቅቱ በተፈጥሯዊና በሌሎች ምክንያቶች ቻይና በረሀብ ጠኔ ተመታች። ቻይናዊያን ተራቡ፤ ጎረቤት ሀገራትን ደጅ ጠኑ፤ ታላቁን ረሀብ መሻገር ያልቻሉ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናዊያን በረሀብ አለቁ።
በቻንግሻ የሚገኘው የማኦ ዘዶንግ ግዙፍ ሐውልት
መራራ ጽዋን ተጎነጩ። የሀገሪቷ መሪ ማኦ ዘዶንግ በወቅቱ ፈተና ተስፋ ሳይቆርጥ ሀገር አሻጋሪ ፖሊሲውን ገቢራዊ አደረገ። ልመናን ለትውልድ ላለማውረስ፣ ንቅዘትን(ሙስናን) ነውር የሚያደርግ ስርዓት አጸና። ስራን ወንጌል፤ ሙስናን ወንጀል ያደረገ ጽኑ ስርዓተ መንግስት ገነባ። ከራሷ አልፋ ለዓለም የተረፈችዋን የዛሬዋን ቻይና በጽኑ መሰረት ላይ አነበረ።
የዛሬዋ ቻይና ከዓለማችን ቁንጮ ልዕለ ሃያል ሀገራት አንዷ ናት። ከራሷ አልፋ ለዓለም ተርፋለች፤ የቻይና ቴክኖሎጂ ምጥቀትና ርቀት ዓለም ጉድ አሰኝቷል።
በቅርቡ ሀገረ ቻይናን ከጎበኙ ጋዜጠኞች አንዷ ሆኜ ‘መልክዓ ቻይና’ን በወፍ በረር ቃኘሁ። በዚህ ማስታወሻዬ በቻይና የቴክኖሎጂ ልህቀትና ምጥቀት ላይ ብቻ አተኩራለሁ።
ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ባላት፣ በ14 ሀገራት በምትዋሰነው፣ በአንድ ኮሚኒስት ፓርቲ በምትመራው ሀገር ቻይና በነበረኝ የ15 ቀናት ቆይታ ቻይና እንደ ጥንተ ታሪኳ ሁሉ በዘመኑ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ላይ ያላትን የመራቀቅ ጥግ ታዘብኩ። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን የመቅደም እሽቅድድሟ ‘አጃይብ’ ያሰኛል።
በሀገሪቷ ርዕሰ መዲና ቤጂንግ እና በማዕከላዊ ቻይዋ በምትገኘው የሁናን ግዛት ዋና ከተማ ቻንግሻ ምልከታዬ ቻይና ’ከተባለላት በላይ’ የቴክኖሎጂ ምጥቀቷ አስደንቆኛል። ምናልባትም የመጀመሪያ ጉዞዬ መሆኑም ነገሩን በአንክሮት እንድመለከት ሳያስገድደኝ አልቀረም።
የሀገሪቷ ርዕሰ መዲና ቤጂንግ እና ጥንታዊቷ ቻንግሻ
ከ22 ሚለዮን የሚልቅ ህዝብ በጉያዋ የታቀፈችው ታላቋ ቤጂንግ ከተማ ከዓለማችን ግንባር ቀደም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ማዕከላት አንዷ ናት። የአዲስ አበባ እህት ከተማ በዚህ ወቅት ሞቃታማ አየር ጸባት አላት።
ቤጂንግ የ21ኛው ክፍል ዘመን የኪነ ህንፃና ክትመት ቴክኖሎጂ ያበበች ብቻ አይደለችም፤ ይልቁኑም በዛፎች ሀመልማላዊ ገጽታ የተላበሰች ውብ መዲና እንጂ። በሕንፃዎችም፣ በዛፎችም የተደነነች ከተማ። በተፈጥሮ የበቀሉ የሚመስሉ ሰማይ ታካኪ ሕንጻዎች፤ የመንገድ መሰረተ ልማት ስፋት፣ ጽዳትና ጥራት ‘ኩልል’ ያለች፣ ‘ምልል’ የምታደርግ ከተማ ያደርጋታል።
ቤጂንግ ከተማ
ከዘመናችን አስደናቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ በሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት(አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሕይወትና ኑሮን እንዴት እንዳቃለለ የቤጂንግ የዕለት ከዕለት ክዋኔ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ቻይኖች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጠበዋል፤ መጠበብ ብቻም ሳይሆን ኑባሬያቸውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት መር አድርገዋል። ከሮቦት መስተንግዶ እስከ ሰው ሰራሽ ፀሐይ መራቀቅ ይስተዋላል።
ካረፍኩበት ሆቴል (15ኛ ወለል ላይ ከሚገኘው መኝታ ክፍሌ) ሆኜ ያዘዝኩት ምግብ በቅጽበት አስተናጋጇ ‘ከች’ ብላ ትደውላለች። ፍጥነቷ ስትገረም፤ አስተናጋጆች ሮቦቶች መሆናቸውን ስትመለከት ይበልጥ ትደነቃለለህ።
በክፍሌ ውስጥ ማብሪያ ማጥፊያ ስጫን መጋረጃው ሲከፈት መደንገጤን አልሸሽግም፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት ፀሐይ አለመጥለቋን ስመለከት ‘የቻይና ሰው ሰራሽ ፀሐይ ወጣች እንዴ?’ ማለቴ አልቀረም።
በነገራችን ላይ የቻይና የሰው ሰራሽ ፀሐይ ሳይንሳዊ ፈጠራ ሁለት ግዜ ተሞክሮ ያለምንም እንከን እንደሚሰራ ነግረውናል። የሰው ሰራሽ ፀሐዩ ሃይድሮጅን እና ዱተሪየም ጋዞችን እንደ ሀይል ማመንጫ ነዳጅነት በመጠቀም ንጹህ ኢነርጂን ለማመንጨት ታስቦ ዲዛይን እንደተደረገና ሰው ሰራሽ ፀሐይ በርሐን ከተፈጥሮ ፀሐይ 13 እጥፍ ያክል ሙቀት እንደሚያመነጭም ሰምተን ተደንቀናል። የቻይና ሰው ሰራሽ ፀሐይ ፕሮጀክት የሥራ ሰዓትን ከ13 ሰዓት ወደ 24 ሰዓት ለመጨመርና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ የሰነቀ ነው።
በቻይና በሰዉ ቅርፅ የተሰሩ ሮቦቶች በእግር ኳስ ጨዋታዎች ተወዳጅነት አትርፈዋል። ቤጂንግ የሚገኘው ሂዩማኖይድ የተሰኘ የሮቦት ቡድን የሰራቸው ሮቦቶች አመርቂ ውጤት ከራቀው የሀገሪቷ እግር ኳስ ቡድን ይልቅ የሀገሬውን ቀልብ እንደሳቡ ይነገራል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት በታገዘ የሮቦቶች ውድድር አያሌ ቻይናዊያን ይታደማሉ። ሮቦቶቹ በጨዋታ መሐል ቢወድቁ በራሳቸውን ይነሳሉ፤ ቢጎዱም ከሜዳ የሚወጡበት ስርዓት ተዘርግቷል። የታላቋ ቻይና ሰዎች ቴክኖሎጂን ከችግር መፍቻነት ወደ መዝናኛነትም አልቀውታል።
በሀገራችን እንደ አዲስ ቴክኖሎጂ በንግዱ ስርዓት ውስጥ እየተዋወቀ ያለው የፈጣን ምላሽ መለያ ወይም ኪው አር ኮድ(Quick Response code) በቻይና ዕለታዊ ከዋኔዎች ቅንጦት አይደለም። በቻይና ማንኛውም ግልጋሎት በዚህ በዲጂታል ስርዓት ይከወናል። እንደሌሎች ስልጡን ሀገራት ሁሉ በንክኪ የሚደረግ ገንዘብ ዝውውር ቀርቷል።
በቤጂንግ ጎዳናዎች በኪው አር ኮድ(QR Code) በሚንቀሳቀሱ ሞተር ሳይክሎችን በየመንገዱ ተሰድረዋል፤ የፈለገ መንገደኛ ሳይክሎችን በመጠቀም ወደ ፈለገበት ስፍራ ተንቀሳቅሶ ክፍያውን በኪው አር ኮድ ከፍሎ ይሄዳል። ሌላውም እንዲሁ። በአዲስ አበባ መኖሪያ ሰፈሬ የነበሩ ሳይክሎኝ ከደጃችን ደብዛቸው እንደጠፋ ሳስብ በቻይኖች ብልሃት፣ ታማኝነትና የከተሜነት ልህቀት ቀናሁ።
በርግጥ በቻይና ኪው አር(QR) ኮድ ለተገለገልንበት መክፈያ ብቻ ሳይሆን ለልመናም መዋሉን ሲመለከቱ ፈገግ ሊሉ ይችላሉ። በቻይና ይህም አለ በማለት። በርግጥ በቤጂንግ የሰው እጅ ከሚያይ ይልቅ ጆሮቸውን ቢቆጥርጣቸው የሚሰሙ የማይመስሉ አዛውንቶች ሳይቀር በስራ ላይ ተጠምደው ይስተዋላሉ።
ከቻይናውያን ጋር ለመግባባት በተለይም በንግድ ማዕከላት የቻይንኛ ቋንቋ መረዳት ግድ ይላል። “ሃው ማቺ፣ ጉዳ ጉዳ፤ ሺሼ፣ ኢ፣ አር…” እና መሰል ቃላት ማወቅ ይበጃል። ከዚህ ባለፈ በምልክት መግባባት አልያም በቋንቋ ተርጓሚ መተግበሪያ መጠቀም ያሻል።
የቻይና ሰራሽ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርቶች በራሳቸው ብራንድ፣ ቋንቋና መልክ እየተመረቱ በተመጣጣሽ ዋጋ ለህዝቦቿ ተደራሽ እየተደረጉ ነው።
የቻይና የራስ-በቅነት ጥረት ያስቀናል። በቴክኖሎጂ፣ በባሕልና በኢኮኖሚ ተጽዕኖ ተላቀው በራሳቸው ለመቆም የሄዱበት ርቀት ግሩም ነው። ግብይቶች በራሳቸው ገንዘብ ብቻ ይከወናል። በወቅቱ ምንዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር ሰባት የቻይና ገንዘብ(ዩዋን) ነው። ከምዕራባዊያን ማህበራዊ ትስስር ገጾች(ለምሳሌ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ) በሕግ በማገድ የራሳቸውን መተግበሪያ አበልጽገው ገቢራዊ አድርገዋል። ‘ዊቻት’ የተሰኘው መተግበሪያ ሁሉም ቻይናውያን መገልገያ ነው።
ከቤጂንግ ሌላ ያስደነቀችኝ ጥንታዊቷ ቻንግሻ ከተማ ነች። ቻንግሻ ስመ-ብዙ ነች። ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ጠገቧ የሁናን ግዛት ርዕሰ መዲና ቻንግሻ ‘የከዋክብት ከተማ’ ትሰኛለች። በነገራችን ላይ ማኦ ዘዶንግ ትውልዱ ሁናን ግዛት ውስጥ ነው። ቻንግሻ በስራ ከተማነቷ ‘የማታንቀላፋው መዲና’ ትባላለች። በመዝናኛ ስፍራነቷ ‘የተዝናኖት መነሃሪያ’ የሚል ተቀጥላ ስም አላት። ‘የሚዲያ ጥበብ’ ስፍራም ትሰኛለች። በኢንዱስትሪ፣ በጥንታዊ ሐውልቶች፣ አብያተ መቅደሶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎች መገኛ በመሆኗ በቱሪስቶች ተወዳጅ ከተማ ናት።
ትናንትና ዛሬን ያዋደደች፣ ታሪክና ባህል ባዛነቀችዋ ቻንግሻ የአምስት ቀናት ቆይታዬ ብዙ ገጽታዋ አስደምሞኛል። የሻንግ ወንዝን ተንተርሳ፣ በተራራማ፣ በሜዳማና ኮረብታማ መልክዓ ምድር በማዛነቅ የተቆረቆረች በመሆኗ የስብት ማዕከል ሆናለች። እንደ ቤጂንግ በደን የተከበበች፣ በዘመነኛ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እና በታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎች የተጌጠች ከተማ ናት። ከዚህ ባሻገር የአምራች ኢንዱስትሪዎች መናገሻም ናት። የምቹ ከተሜነትና ጠንካራ የስራ ባህል በግላጭ የሚስተዋልባት ከተማ። የዓለማችን ገዙፉ
በጣም ሞቃታማ አየር ጸባይ ባላት ቻንግሻ ሌት ከቀን ይሰራል። ፋብሪካዎቿ አይተኙም። ሌትና ቀኑ የሚታወቀው በሰዓት ብቻ እንጂ የስራና የንግድ ድባቡ እኩል ነው። ብርሃናማዋ ቻንግሻ ‘የቻይዊያን መስቀል’ በተሰኘው በቀይ በተቀለመው መስቀልም ትታወቃለች። በርግጥ ከዓለማችን ግዙፍ ማማዎች አንዱ የሆነው ሕንጻም መገኛ ናች።
በጥቅሉ የቻይና ጉብኝት ትዝብቴ የገናና ታሪክ ባለቤቷ ሀገር ከባድ ውጣ ውረዶችን አልፋ ዛሬ ዓለምን እየቀደመች መሆኑን ሳስብ፤ እንደቻይና ሁሉ የሺ ዘመናት ገናና ታሪክና አኩሪ ገድል ያላት ኢትዮጵያስ የሚል ተጠየቅ እንዳውጠነጥን አድርጎኛል። ቻይናዊያን የዘመን የፈተና ቋጠሮዎቻቸውን ፈታተው ከዛሬ ከፍታ ሰገነት ላይ ወጥተዋል። ከዛሬም በበለጠ ነገን በጽኑ መሰረት ላይ እየገነቡ ነው። እኛስ? ብዬ ሳስብ በቁጭትና በተስፋ ተዋጥኩ!
ሰላም!