የሺህ ሀይቆች ምድር

የሺህ ሀይቆች ምድር

(በራሔል አበበ)

በርካታ መገለጫዎች አሏት። የሺህ ሀይቆች መፍለቂያ። አረንጓዴ ምድር። 75 በመቶ የአገሪቱ ገፀ-ምድር በደን የተሸፈነ። የአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ። በአውሮፓ ከበለጸጉ አገራት አንዷ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በዓለም ቁጥር አንድ የደስተኞች አገር በመባል የተሰየመች ሰሜን አውሮፓዊት አገር - ፊንላንድ።

በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋባዥነት በአዲስ አበባ የአገሪቱ ኤምባሲ አስተባባሪነት በቅርቡ ፊንላንድን የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር። በጉብኝቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፤ ሞዛምቢክ እና ዛምቢያ ጋዜጠኞች ተሳትፈናል።

የአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ምንም እንኳን የትም አገር ስሄድ ቀድሜ መረጃ የማየት ልምድ ቢኖረኝም በመጀመሪያው ዕለት ለእራት ስንወጣ ያየሁት በምሽት ያልተለመደ የፀሐይ ፍካት ግን እራቱ ቁርስ እንዲመስለኝ አድርጓል። ከዚያ በኋላ ለመድሁት። በእርግጥ በአንድ ወቅት በስፔንም ፀሐይ እስከ እኩለ ሌሊት የማትጠልቅበትን ክስተት ተመልክቻለሁ። በፊንላንድ ያየሁት ግን ተለየብኝ። ፀሐይ ፈጽሞ ለጨረቃ ቦታ መልቀቅ አትፈልግም። ምሽቱ የሚደምቀው በመብራት ሳይሆን በፀሐይ ነው። ሌሊቱ ብርሀን ነው። ሰማይ አይጠቁርም። በየዕለቱ ሳይጨልም ይነጋል።

በዚህ ወቅት በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ሰማይ ላይ የሚታየው ሰሜናዊ የቀለማት የብርሀን ፀዳል ሌላው የፊንላንድ መድመቂያ ነው። የሰሜን አውሮፓ/ኖርዲክ አገራት በተፈጥሮ የታደሉ ናቸው። እኔ ደግሞ የተፈጥሮ አድናቂ ነኝ። ያለማጋነን በፊንላንድ ተፈጥሮ ከነክብሯ ተጠብቃ አይቻለሁ። ንጹህ አየሯ የዚህ ውጤት ነው። አድናቆቴ የጀመረው ከኤርፖርት እስካረፍኩበት ሆቴል 15 ኪሎ ሜትር ያህል በመኪና ስንጓዝ የከተማዋን አረንጓዴነትና የምድሪቱን ልምላሜ ስመለከት ነበር። በጉብኝቴም በተግባር አረጋገጥሁ። የአገሪቱ አብዛኛው መሬት በደንና በውሃ ተሸፍኗል። በዋና ከተማዋ ሄልሲንኪና በዙሪያዋ በሚገኙ ውብ ደኖች መሀል ስንጓዝ መሬቱ ለም ስለመሆኑ ዓይን ብቻ ሳይሆን እግርም ምስክር ነው። ሲራመዱ የመሬቱ ምቾትና እንደ ስፖንጅ ስምጥ ስምጥ ማለት ለምነቱን ይናገራል።

በሄልሲንኪ ሴኔት እና ካንሳላስቶሪ አደባባዮች እንደእኛዎቹ አራት እና ስድስት ኪሎ አደባባዮች ናቸው። ቤተ-መንግስት፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ፓርላማ፣ ቤተ-መጽሐፍት እና ቤተክርስቲያንን አጎራብተው ይዘዋል። የሄልሲንኪ ሕንጻዎች እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ውብና የሥነ-ሕንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ናቸው። የነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ከተማዋ አልተጨናነቀችም። በአስፋልትና ደረጃውን በጠበቀ ኮብልስቶን የተሰራው የከተማዋ አውራ ጎዳና ከዘመናዊ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የህዝብ አውቶቡስና የኤሌክትሪክ ባቡር ያስተናግዳል። ለአውሮፓ ከተሞች አዲስ የሆነ ሰው ኮብልስቶኑ የእግረኛ መንገድ መስሎት መሐል የመኪና መንገድ ላይ ሊገኝ ይችላል። እኔም የተረፍሁት እንዲህ አይነቱን የመኪና መንገድ በአንድ ወቅት በኢጣልያ በማየቴ ነበር።

የተፈጥሮ ውበት ደምቆ የሚታይባት ፊልናልድ ሲልቨር በርች የተሰኘው ብርማ ቀለም ቅርፊት ያለው ዛፍ እና ቡናማ ድብ ብሔራዊ መለያዎቿ ናቸው። በረጃጅሞቹ ዛፎች መሐል ከእንስሳት ባሻገር ስትሮበሪና እንጉዳይን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ዕጽዋት ይገኛሉ። በፊንላንድ ብዙ አይነት የእንጆሪ/ስትሮበሪ ዝርያ አለ። ወቅቱ ፍሬ የሚደርስበት አልነበረም እንጂ ከጫካዎቹ መሐል ገብቶ በተለያዩ የስትሮበሪ ፍሬዎች ቅርጫት ሞልቶ መውጣት የተለመደ መሆኑን ተረድቻለሁ።

ፊንላንድ የሺህ ሀይቆች ምድር ተብላም ትሞካሻለች። ለቁጥር የሚያዳግቱ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀይቆችና የውሀ አካላት ከተፈጥሮ ሀብቶቿ መካከል ናቸው። ለጉብኝት በሄድኩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚቀርብልኝን ኩልል ያለ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በፍቅር ነበር የምጠጣው። ግዴታ ካልሆነ የፋብሪካ ውሃ በፊንላንድ ቦታ የለውም። ንጹህ የተፈጥሮ የምንጭ ውሃ ከቧንቧ ይቀዳል። ጽድት ከማለቱ ጣዕሙ።

ፊኒሾች ለባህልና ቅርስ ትልቅ ቦታ አላቸው። በተለይ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ቁርኝት አስገራሚ ነው። በአብዛኛው አፍሪካ ውስጥ የሚነገር አፈ-ታሪክና ተረት በፊንላንድም ከተፈጥሮ በተለይም ከዛፎችና ከእንስሳት ጋር ተያይዞ ሲተረትና የመድረሻቸው መነሻ እንደሆነ ሲነገር ተደንቄያለሁ።

በጉብኝታችን በአንዱ ቀን ኑኪሲኦ ብሔራዊ ፓርክ ሄድን። ይህ ደግሞ እጅግ የተለየ ተፈጥሮን ማያ ስፍራ ነው። በረዣዥም ዛፎች መሐል ካደረግነው ጉዞ በኋላ የቀረበልን ባህላዊው የፊንላንድ የሳውና እና የዋና ግብዣ ነበር። ሳውና የፊንላንድ ባህል ነው። በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለ የፊኒሽ ቃልሳውናእንደሆነ ይነገራል። ዛሬ በዓለም ላይ በተለይም በባለኮከብ ሆቴሎች በስፋት የምናገኘው ሳውና መነሻው ፊንላንድ ናት። በርካታ የሳውና ስፍራዎች ከመኖራቸው የተነሳ የሳውና ቁጥር በአገሪቱ ከተመዘገቡ መኪኖች ቁጥር ይበልጣል ይባላል። ግብዣውን ሁላችንም በደስታ ነበር የተቀበልነው። በባህሉ መሰረት ሳውና ውስጥ በቅጠል እየተጠበጠብን ከፍተኛ ሙቀት ሲሰማን ከፊት ለፊት ባለው ቀዝቃዛ የተፈጥሮ ሀይቅ ውስጥ በመግባት ዋና የሚችል ዋኝቶ የማይችል ደግሞ በመነከር ሰውነቱን አቀዝቅዞ እንደገና ወደሳውናው ይመለሳል። የተለየ ነው።


 


 

የጉብኝቱ ዋና አስተባባሪ አና ላሚላ ትባላለች። 35 ዓመት የስራ ልምድ ያላት ብስል ዲፕሎማት ናት። በተለያዩ አገራት ፊንላንድን ወክላ ሰርታለች። አሁንም በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አምባሳደር ነች። ትክክለኛ የኮሙኒኬሽን ሰው ናት። አንቺ ያልኳት በአንቱታ ላርቃት ባለመፈለጌ ነው። ለነገሩ ስትታይም 35 ዓመት ወጣት እንጂ 35 ዓመት የስራ ልምድ ያላት አትመስልም። አንድ ቀን አንመኮንንበሚለው የአያቴ ስም እየጠራችኝ ስምሽ እኮ የፊኒሽ/የፊንላንድ ነው ይህን ታውቂያለሽ? ከእኛ ጋር ዝምድና ይኖርሽ ይሆን?" አለችኝ ፈገግ ብላ። "ኸረ በፍፁም ኢትዮጵያዊት ነኝ" አልኳት። ትክክል ነበረች። አጭር የፅሁፍ መልዕክት የመለዋወጥ ሀሳብን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቀውማቲ መኮንንየተባለ ፊንላንዳዊ ኢንጂኒየር ነው።

የቴክኖሎጂ ነገር ከተነሳ አብዛኞቻችን ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር ስንተዋወቅ የያዝነው ኖኪያ የፊንላንድ ምርት ነው። የመኮንንን ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት ለዓለም ይፋ ያደረገውም ኖኪያ ነው። አሁንም ኖኪያ በኔትወርክ ዝርጋታ ጭምር እየሰራ ያለ ግዙፍ የቴሌኮም ተቋም ነው።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ የረዥም ዓመታት የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው 66 ዓመታትን ተሻግሯል። ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ከእርዳታና ትብብር ባሻገር በተለያየ መስክ በጋራ ትሰራለች። በጉብኝቴ ወቅት ያገኘኋቸው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሌና ቫልቶነን ይህን ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት መኖሩን ነግረውኛል። ከንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ኖኪያን ከመሰሉ ኩባንያዎች ጋር የሚደረግ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና በአገሪቱ ቴክኖሎጂ መዘመኑን የተረዳሁት በአገሪቱ ብሔራዊ የሚዲያ ተቋም ይሌ ያለማንም እርዳታ ዜና ቀርጾ የሚያሰራጭ ሰው አልባ ሮቦትድ የስቱዲዮ ቴክኖሎጂ ስመለከት ነበር።

ፊንላንድ በትምሕርት ጥራትም ስሟ በቀዳሚነት ይነሳል። በአገሪቱ 800 በላይ፤ በመዲናዋ ደግሞ 40 የሚጠጉ ቤተ-መጻሕፍት አሉ። ከአገሪቱ ፓርላማ አቅራቢያ የሚገኘውና አገሬው የእኩልነት ተምሳሌት ነው የሚለው የሄልሲንኪ ግዙፉ ማዕከላዊ ቤተ-መጽሐፍት ኦዲ ይባላል። በውስጡ በርካታ አገልግሎቶችን ይዟል። ንባብ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የባህልና ፈጠራ ታለንቶችን ያስተናግዳል። ከልጅ እስከ አዋቂ ለሁሉም ቦታ አለው።


 

ፊንላንድ ዜጎቿ በደስታ ግብር የሚከፍሉባት አገር መሆኗን የአገሪቱ የታክስ አስተዳደር ሲናገር በኩራት ነው። ግብር መሰወር፤ ክፈሉ ብሎ በየግዜው መቀስቀስን የመሳሰሉ ነገሮች እዛ ቦታ የላቸውም። የኩባንያም ሆነ የግለሰብ ግብር ከፋዮች በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በወቅቱ እንደሚወጡ አስተዳደሩ ይገልጻል። ይህም የዜጎች ፍላጎትን ለማሟላት በተሰራ ስራ የተፈጠረ መሆኑን የተመለከትኳቸው ተቋማት ሃላፊዎች ይገልጻሉ። ዜጎች በመንግስት ላይ ከፍተኛ እምነት አላቸው። በፊንላንድ የዜጎች ደስተኝነት የሰላምና ነጻነት መገለጫ እንደሆነ ምሁራኖቻቸው በጥናት ስራዎቻቸው ጭምር ይመሰክራሉ።

የደስታቸው ምንጭ ነጻና ጥራት ያለው ትምሕርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፤ በፍትህና እኩልነት፤ በበጎ አድራጎት ተግባር፤ የእናቶችና ህጻናት ጤናን ጨምሮ አርአያ የሚሆኑ ጠንካራ የማሕበራዊ ደህንነትና ትስስር ስራዎች የመጡ ውጤቶች እንደሆኑ ይገለጻሉ። በጾታ እኩልነት ሴቶች በሁሉም መስክ ጥሩ ስፍራ አላቸው። በፖለቲካውም ከወንዶች ተቀራራቢ ቦታ እንዳላቸው የአገሪቱን ፓርላማ ስንጎበኝ ተረድቻለሁ። 200 የምክር ቤት አባላት 91 ሴቶች ናቸው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ፊንላንድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደስተኛ አገራት ደረጃ ላይ ለስምንት ተከታታይ ዓመታት የከፍታ ስፍራዋን ሳትለቅ በቁጥር አንድ ላይ እንድትቆይ አድርጓታል። ዜጎቿ በቀጣዩ ዓመትም ለዘጠነኛ ጊዜ የዓለም የደስተኞች አገር ሆና ትቀጥላለች የሚል እምነት አላቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም