በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ምን አሉ?

በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ምን አሉ?

17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ እየተካሄደ ይገኛል

 ጉባኤው እየተካሄደ የሚገኘው “ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የደቡብ ንፍቀ ዓለም” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በጉባኤው ላይ ተሳታፊ የሆኑ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በዓለም አንገብጋቢ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

  • ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል።
  • ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት በሚያስችል ሁኔታ አፋጣኝ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው።
  • በብሪክስ አዳዲስ አባላት መጨመራቸው የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ አላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል።
  • እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በአለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ ታደርጋለች።

የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊስ ኢግናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ

  • የዓለምን የአስተዳደር ስርዓትን ለመቀየር የሚያስችል መሰረተ ልማትና የጋራ ትብብራችንን ማጠናከር ይገባል።
  • ብሪክስ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚሆን አዲስ የብዝሃ ዓለም አስተዳደር የመፍጠር ቁልፍ ሚና አለው።
  • ከጦርነት ይልቅ ሰላም ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ትርፋማ ያደርጋል።
  • የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ቃል የገቡትን ገንዘብ መስጠት አለባቸው።

የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ

  • ብሪክስ በዓለም ፍትሃዊ እና መርህን ያከበረ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር የመሪነት ሚናውን መወጣት አለበት።
  • ለብሪክስ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ልማት ትልቅ ድርሻ ያለው የእድገት ምሰሶ ነው።
  • በብሪክስ ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ልውውጥ እና የጋራ መማማር የበለጠ ማሳደግ ይገባል።
  • ብሪክስ በዓለም ደረጃ ያሉ ግጭቶች በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ በማድረግ የሰላም ኃይል መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት ይኖርበታል።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን (በበይነ መረብ)

  • ሊበራሊዝም መር የሆነው የዓለም የሉላዊነት አስተዳደር ስርዓት ጊዜው አልፎበታል፤ አዲስ የባለብዝሃ የዓለም ስርዓት እያቆጠቆጠ ነው።
  • በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ የመገበያያት ልምምዳቸውን ማጠናከር አለባቸው።
  • የብሪክስ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብት፣ ሎጅስቲክስ፣ ንግድ፣ ፋይናንስ እና በሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አለባቸው።
  • በሚሸፍነው መልክዐ ምድር፣ በያዘው የህዝብ ብዛት እና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ባለው ድርሻ ብሪክስ ትልቅ ኃይል ሆኗል።

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

  • ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍትሃዊ ውክልና በሚያረጋገጥ መልኩ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ሊደረግበት ይገባል። የ21 ክፍለ ዘመን ሶፍትዌር በ20ኛ ክፍለ ዘመን የታይፕ ራይተር ማሽን ላይ ግልጋሎት ሊሰጥ አይችልም።
  • የሰው ልጅ እና የዓለማችን የምንግዜውም ትልቅ ስጋት ሽብርተኝነት ነው። ሽብርተኝነት መከላከል እና ማውገዝ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ነው።
  • የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መጠቀም እና ማስተዳደር በጣም አስፈላጊ ነው።
  • ህንድ በዓለም ደረጃ ያሉ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲ፣ በሰላም እና በንግግር እንዲፈቱ በቁርጠኝነት ትሰራለች።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ

  • የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወቅታዊ የዓለም ነባራዊ ሁኔታን መሰረት ያደረገ አፋጣኝ ማሻሻያ ያስፈልገዋል።
  • ብሪክስ ዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ውጥረቶችን ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና አሳታፊ የደህንነት ማዕቀፎችን ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ አሰራር መፍጠር አለባቸው።
  • ደቡብ አፍሪካ የብሪክስ የፀረ-ሽብርተኝነት ስትራቴጂ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመተግበር ቁርጠኛ ናት።
  • የብሪክስ መስፋት ንግድ ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አዳዲስ የትብብር አማራጮችን ይፈጥራል።

የኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት ብራቦዎ ሱቢያንቶ

  • ብሪክስ በደቡብ-ለደቡብ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የዓለም ጤና እና የከባቢ አየር ትብብር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
  • የዓለም የብዝሃ ወገን ተቋማት እኩልነትን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል።
  • በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አማካኝነት በብሪክስ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ሚዛናዊ ትብብር መፍጠር ይገባል።
  • በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ እና ጦርነት እንደ አማራጭ መጠቀም ሊቆም ይገባል። ዓለም አቀፍ ፍትህ እና ሰላምን ማስፈን ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

  • ዓለም ከምንጊዜውም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል። ግጭቶችን በውይይት እና በንግግር መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
  • የሰውን ህይወት እና ኢኮኖሚ በፍጥነት እየቀየረ ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለእኩይ አላማ እንዳይውል በከፍተኛ ኃላፊነት እና ጥንቃቄ መጠቀም ይገባል።
  • ብዝሃ ዓለም የባለብዝሃ ወገን አስተዳር ስርዓት ያስፈልገዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና የዓለም የፋይናንስ መዋቅርን ጨምሮ የዓለም የአስተዳደር ስርዓት ከጊዜው ጋር ተራማጅ መሆን አለበት።
  • በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም ኢኮኖሚ እና አስተዳደር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ ይገባል።

ሁለተኛ ቀኑን የያዘው 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም