ከሮም እስከ አዲስ አበባ 

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ይካሔዳል።

የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ፣ የምግብ ስርዓት ሽግግር ሁለንተናዊነትና የተገቡ ቃሎችን ከመፈጸም አንጻር ያለውን የተጠያቂነት ስርዓት ማጠናከር ጉባኤው ትኩረት ያሚያደርግባቸው ሀሳቦች ናቸው።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተምግብ ጉባኤ በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በጣልያን ሮም የተካሄደው የመጀመሪያ የተመድ ስርዓት ምግብ ላይ የተገቡ ቃሎች ትግበራ ሂደትን መነሻ በማድረግ የሚካሄድ ነው።

በመጀመሪያው ጉባኤ ላይ የ182 ሀገራት ተወካዮች፣ 21 የሀገራት መሪዎች እና 126 ሚኒስትሮችን ጨምሮ 3 ሺህ 300 ተሳታፊዎች ታድመውበታል።

በጉባኤው ላይ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሀገራት እና ተቋማት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ስድስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርገው ነበር።


 

የምግብ ስርዓት ስትራቴጂዎችን ከብሄራዊ ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር፣ ሁሉን አቀፍ የምግብ ስርዓት አስተዳደር መገንባት፣ በጥናት፣ ዳታ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፣ ሁሉን አቀፍ የእቅድ ዝግጅት እና ትግበራን ማጠናከር፣ በምግብ ስርዓት ውስጥ የንግዱ ማህበረሰብ ያለውን ድርሻ ማሳደግ እና የአጭርና የረጅም ጊዜ የአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

ኢንቨስትመንት፣ የበጀት ድጋፍ እና የእዳ አስተዳደር ሌላኛው የትኩረት መስክ ነው።

በጉባኤው ላይ 300 ገደማ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የምግብ ስርዓት ሽግግርን እውን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በተለይም እ.አ.አ 2030 የማይበገር፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የምግብ ስርዓት መገንባት እንዲሁም ምግብ ለሁሉም የሚለውን ግብ ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርጉ ሀገራት ቃል ገብተዋል። 


 

ሁሉን አሳታፊ ነው በሚል አድናቆት ያገኘው ጉባኤው በስርዓት ምግብ ላይ ግንዛቤን ከማሳደግ እና አቅምን ከመገንባት አንጻር ውጤታማ እንደነበር ይነሳል።

የምግብ ስርዓት ሽግግር አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ እንደሆነም በጉባኤው ተወስቷል።
 
ኢትዮጵያም በስርዓተ-ምግብ ጉባኤው ላይ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ ነበር። በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ልምደችን አቅርባለች። 
በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና በስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማምጣት እየወሰደች ባለው የፖሊሲ እርምጃና ውጤቶች ዙሪያ ገለጻ አድርገውም ነበር።

ኢትዮጵያ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ለየስነ ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን፣ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል።


 

በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርት እና በሌማት ትሩፋት እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ለጉባኤው አቅርበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታታትም ሆነ በስርዓተ-ምግብ ሽግግር ለማድረግ አዲስና የተለየ የፋይናንስ ሞዴል ያስፋልጋል በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል።

ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግር አቅጣጫዎች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም በፋይናንስ አቅርቦት፣ በዓለም አቀፍ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም በትብብር በመስራት በኩል በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የገለጹት። 

በመሆኑም ሀገሮች በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአነስተኛ እርሻ ስር-ነቀል ለውጥ በማምጣት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንኦት አንስተዋል። 

ለዚህም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እንዲያሳድጉና ለግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል ።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ-ምግብ ጉባኤ የመጀመሪያውን ጉባኤ መነሻ በማድረግ በተለያዩ አጀንዳዎች ይመክራል። 

ቀዳሚ ትኩረቱ ከመጀመሪያው ጉባኤው በኋላ የምግብ ስርዓትን አስመለክቶ ያሉ ለውጦች ምንድን ናቸው? የሚለው ነው።

በጉባኤው ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ ያገኟቸውን ስኬቶች እና የጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ።

በተለይም የምግብ ስርዓት ሽግግሩ ሁለንተናዊነት እና ሁሉን አሳታፊነት ዋንኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ሁለተኛው የጉባኤው አጀንዳ በመንግስታት፣ የምግብ አምራቾች፣ የንግድ ማህበረሰቡ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር ነው።

የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው ታምኖበታል። 

በተጨማሪም ሀገራት እና ተቋማት በሮሙ ጉባኤ የገቧቸው ቃሎች የደረሱበትን ደረጃ የሚገመገም ሲሆን ቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ለምግብ ስርዓት ሽግግር የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት እና የኢንቨስትመንት መጠንን መጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ጉባኤው ይመክራል። 

ለምግብ ስርዓት ሽግግር ስራዎች በአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ፣ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም እና ሀገር በቀል የፋይናንስ መሰብሰብ አቅምን ማጎልበት ላይ ምክክሮች ይደረጋሉ ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በሮም በነበረው ጉባኤው ላይ ይፋ ያደረጓቸው ስድስት የትኩረት መስኮች አፈጻጸም ግምገማ ሌላኛው አጀንዳ ነው።

በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች፣  ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አርሶ አደሮች፣ አምራቾች እና የምግብ ስርዓት ሽግግር ተዋንያንን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው። 

በጉባኤው ላይ ከዋናው ሁነት ጎን ለጎን የምግብ ስርዓት ትራስፎርሜሽን እና የስርዓተ ምግብ ሽግግርን አስመልክቶ በርካታ የጎንዮሽ ስብስባዎች ይደረጋሉ። 

ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ሽግግር ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶም በጉባኤው ተሳታፊዎች የመስክ ምልከታ ይደረጋል።
 
ኢትዮጵያ በስርዓት ምግብ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በግብርናው ዘርፍ ባደረጋቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ጉባኤውን እንድታስተናግድ የተመረጥችባቸው ምክንያቶች  ናቸው።

ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ሽግግር እየተወጣች ያለው የመሪነት ሚና እና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗ ተመድ ዓለም አቀፉን ከፍተኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። 

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ የማስገንዘብ ስራ ታከናውናለች።

ተባባሪ አዘጋጇ ጣልያን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በምግብ ስርዓት ሽግግር ውጤታማ ተሞክሮ ያላት ሀገር ናት።

የደቡብ አውሮፓዊቷ ሀገር ከኢትዮዮጵያ ጋር በመሆን ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን እየሰራችም ትገኛለች። 

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ተሳታፊዎች ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እየጠበቀች ትገኛለች። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም