የዋጋ ንረት ምን ማለት ነው?

የዋጋ ንረት በንፅፅር ለምሳሌ አምና 26 በመቶ ዘንድሮ 14 በመቶ ሲሆን ምን ማለት ነው? ለምሳሌ የአንድን የ100 ብር ዕቃ ወስደን ብንመለከት ካቻምና ከነበረበት 100 ብር አምና 126 ብር ሆኖ ነበር ማለት ነው። ስለዚህ የዕቃው ዋጋ በአመት ብር 26 ጨምሯል ማለት ነው። በተመሳሳይ መንገድ አምና 100 ብር ዋጋ ያለው ዕቃ ዘንድሮ 14 በመቶ ካደገ ዘንድሮ 114 ብር ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ስሌት የዕቃው ዋጋ ካምና ወደ ዘንድሮ የጨመረው በ14 ብር በመሆኑ አምና ከጨመረበት ብር 26 ጋር ሲነፃፀር ጭማሪው ቀንሷል ማለት ነው።


ዋጋን ያየን እንደሆነ ግን 100 ብር የነበረ ዕቃ 114 በመሆኑ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም። የዋጋ ንረት ጨመረ የሚባለው ደግሞ ለምሳሌ አምና 26 በመቶ የጨመረው ዘንድሮ 14 በመቶ ሳይሆን 30 በመቶ ቢሆን የጨመረው አምና 100 ብር የነበረው ዕቃ ዘንድሮ 114 ሳይሆን 130 ብር ይሆናል ማለት ነው። ይህ አምና ከጨመረበት የ26 ብር ይበልጣል ማለት ነው። ስለዚህ ካቻምና 100 ብር የነበረው ዕቃ አምና 26 ብር ጨምሮ 126 ከሆነ በኋላ ዘንድሮም 14 ብር ስለጨመረ በቀላል ቀመር ዘንድሮ 140 ብር ሆኗል ማለት ነው። ስለዚህ በሁለት አመታት የዕቃው ዋጋ 40 ብር ጨምሯል። የዕቃው ዋጋ አልቀነሰም በየአመቱ የጨመረበት ምጣኔ ግን ካምና ዘንድሮ ያነሰ ነው። ይህ ነው የዋጋ ንረት ቀነሰ ማለት።

ዋጋ ቀነሰ ማለትስ ምን ማለት ነው?

ዋጋ ቀነሰ የሚለውን ከማየት በፊት የዋጋ ንረት የለም ማለት ምን እንደሆነ በዛው 100 ብር ዋጋ ባለው ዕቃ እንመልከት። ይህ ባለፈው አመት ብር 100 የነበረ ዕቃ ዘንድሮም እዛው 100 ብር ላይ ቢቆይ የዋጋ ንረት ዜሮ ነው። ስለዚህ የዕቃው ዋጋ አልተለወጠም ማለት ነው። 


ዋጋ ቀነሰ ማለት ግን የዋጋ ንረት ከዜሮ በታች ይሆናል ማለት ነው። በምሳሌው ለማስረዳት አምና 100 ብር ዋጋ ያለው ዕቃ ዘንድሮ 90 ብር ቢሆን የዋጋ ንረቱ ወይም ለውጡ ከዜሮ በታች 10 በመቶ ነው። በዚህ ግዜ የዋጋ ንረት ቀነሰ ሳይሆን ዋጋ ቀነሰ ይባላል።


እነዚህ ሶስቱ የዋጋ ለውጦች ለሸማቾችና ለአምራቾች ምን ማለት ናቸው?  ለሸማቾች ከሁሉም የሚመረጠው ዋጋ ሲቀንስ ማለትም 100 ብር የነበረው ዕቃ 90 ብር ሲሆን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ተመራጩ ዋጋ ንረት ሳይኖር አምና 100 ብር የነበረው ዕቃ ዘንድሮም ሳይለወጥ በዜሮ ንረት 100 ብር ላይ ሲቆይ ነው። ሶስተኛው  የተሻለ አማራጭ አምና 100 ብር የነበረ ዕቃ ዘንድሮ በ26 በመቶ ጨምሮ ብር 126 ከሚሆን በ14 በመቶ ጨምሮ ብር 114 ሲሆን ነው። ይህ ሶሰተኛው  አማራጭ በሁለቱም ዋጋ ስለሚጨምር በትንሽ የጨመረው ተመራጭ ይሆናል  ማለት ነው።


ከአምራቾች አንፃር ሲታይ ከላይ ለሸማቾች የተሻለ አማራጭ በቅደም ተከተል ያስቀምጥነውን ገልብጠው ማንበብ ነው።


አሁን ብሔራዊ ባንክ እያለ ያለው የዋጋ ንረት ወይም አመታዊ ጭማሪው ቢበዛ ከ10 በመቶ እንዳይበልጥ የሚረዳ የገንዘብ  ፖሊሲ እተገብራለሁ ነው። የባንኩ አላማ የዋጋ ንረት ዜሮ ወይም ከዜሮ በታች እንዲሆን ሳይሆን 1) ከ10 በመቶ በታች እንዲሆን ሲሆን 2) የትረጋጋና ተገማች እንዲሆን ነው። የተረጋጋ ማለት ከወር ወር ወይም ካመት አመት ዋጋ የሚለወጥበት ሁኔታ በጣም የተራራቀ ያልሆነ ማለት ነው። ለምሳሌ ካንዱ ወር ወደ ቀጣይ ወር ጭማሪው 0.5 በመቶ ሆኖ በቀጣይ ወር ደግሞ የ5 በመቶ ጭማሪ ከዚያም በቀጣይ ወር ከዜሮ በታች የ2 በመቶ ወርሃዊ ለውጥ ቢመዘገብ ያልተረጋጋ ወይም ተገማች ያልሆነ የዋጋ ለውጥ አለ ማለት ነው። ሰለዚህ የተረጋጋና ተገማች የዋጋ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ የባንኩ ሁለተኛው አላማ ነው ማለት ነው።


ብሔራዊ ባንክ በጣም ዝቅተኛ የዋጋ ንረት ወይም ከዜሮ በታች የዋጋ ለውጥ እንዴት ያየዋል ብለን ያየን እንደሆነ ነገሩ እንዲህ ነው። ቅድም ከላይ እንዳየነው የዋጋ ንረት ከሸማቾችና ካአምራቾች አንፃር የሚታየው በተቃራኒ መንገድ ነው። ስለሆነም ምንም እንኳን የዋጋ ንረት በጣም ዝቅተኛ ወይም ከዜሮ በታች ቢሆን ለሸማቾች ጥሩ ቢሆንም አምራቾችን ግን የማያበረታታ ስለሚሆን ማምረት ያቆማሉ ሠራተኛ ይቀንሳሉ አጠቃላይ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ይገታና ጭራሽ ከምርት እጥረት የተነሳ የዕቃዎች ዋጋ መናር ይከሰታል ሥራ አጥነት ይበዛል። ስለዚህ መንግስት ሥራ እንዲፈጠር ኢኮኖሚ እንዲነቃቃም ስለሚፈለግ የተረጋጋና ዝቅተኛ ሸማቹን የማይጎዳ አምራቹንም የሚያበረታተ የዋጋ ሁኔታ እንዲኖር ይሰራል ማለት ነው።


ለአንድ ኢኮኖሚ ትክክለኛው የዋጋ ንረት ስንት ነው? ይህ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ግን ከባድ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለለስ ከሚረዱት ሁኔታዎች አንዱ ኢኮኖሚው ያለበት ደረጃ ነው። ምን ማለት ነው በጣም ባደገና የበለጠ የማደግ እድሉ ጠባብ ለሆነ ኢኮኖሚ 1 በመቶ ወይም 2 በመቶ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ ገና የማደግ እምቅ አቅም ላለውና በማደግ ላይ ላለ ሀገር ነጠላ አሃዝ የዋጋ ንረት እንደ ሁኔታው የሚለያይ ሆኖ ተመራጭ ሊሆን ይችላል። ስንት ነው የሚለው ግን በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጥ  አለበት። ለምሳሌ የሀገራችንን threshold inflation or optimal inflation level ለማወቅ እኔን ጨምሮ የባንኩ ሠራተኞች በሳይንሳዊ መንገድ ለማወቅ ተሞክሯል። በኔ ጥናት 7 በመቶ ሲሆን በሌሎቹም ከዚሁ ያልራቀ ውጤት እንዳለ አይቻለው የመረጃ አጠቃቀምና የሜቶዶሎጂ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። ሰለዚህ በነዚህ ጥናት መሰረት ብሔራዊ ባንክ የነጠላ አሃዝ የዋጋ ንረት አላማ አድርጎ መንቀሳቀሱ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ማለት ነው ለኛ ኢኮኖሚ።  ለማጠቃለል የዋጋ ንረት ምንነትን በተመለከተ ያለውን ውዥምብር ለማጥራት ይህ አጭር መግለጫ  ያግዛል ብዬ እያመንኩ የበለጠ መብራራት ካለበት ወይም ጥያቄ ካለ አንባቢዎች በአስተያየት መስጫው ላይ ማሰቀመጥ  ትችላላችሁ።


አቶ ፈቃዱ ደግፌ የብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም