ቀጥታ፡

በኢዜአ ዐይን…! 

  
በዮሐንስ ደርበው
 
ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡበት ጠቅላላ ምርጫ  
 
• እንደ መነሻ

ባሳለፍነው ወርኃ ግንቦት ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካሂዳለች።
 
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መታያ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ገቢራዊነት መገለጫ፤ ሕዝባዊ መንግሥትን አንባሪ ብሎም በሕዝባዊ ምርጫ ብቻ ወደሥልጣን የሚመጣበት መንገድ  ነው።
 
ለሀገራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ቁልፍ ነው።
 
 ቅድመ ምርጫ
 
ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ባለድርሻ አካላት ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውነዋል። ለአብነትም፤ የምርጫ ሕጉን ከማሻሻል ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥርዓቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በተጨማሪም የምርጫ ትምህርትና ግንዛቤን ለማስፋት ለሚሠሩ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል።
 
የምርጫ ሂደትን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥም በርካታ ድርጅቶች በታዛቢነት ተመዝግበዋል።
  
የመራጮች ምዝገባም፤ በመደበኛ የመራጮች ምዝገባ (ማኑዋል)፣ ምርጫዬ በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ እና በድረ ገጽ አማራጭ በመቅረቡ በርካታ መራጮችን አሳትፏል።
 
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በ24 ሬዲዮ፣ በ20 ቴሌቪዥን እና በ6 ጋዜጦች በሕዝብና በንግድ ሚዲያዎች ነጻ የአየር ሠዓት ተደልድሏል፤ ሐሳባቸውንም ተደራሽ አድርገዋል።

 • በምርጫ ወቅት
 
በምርጫ ካርድ ሀገር የሚመራን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ ከሥልጣኔ መገለጫዎች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። የመራጮች ንቁ ተሳትፎም የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ያጎለብታል።
 
ምርጫ፤ ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ፣ ተቋማዊ አሠራሮች  እንዲጠናክሩ ቁልፍ በመሆኑ ጠቅላላ ምርጫው ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው።
 
የሕዝቡን ትጋት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክትም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተዓምረኛም ሕዝብ ነው፤ ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው? የዳበረ ባሕል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል ብለዋል።
 
ታሪካዊ በሆነው ዕለትም፤ የሌሊቱ ብርድና ጨለማ ያላስፈራቸው፣ የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛ ዝናብ ያልበገራቸው፣ ሠርግ፣ ኀዘን፣ ወሊድና ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶች ያላገዳቸው፣ ረጃጅም ሰልፎች ያላታከታቸው፣ የአካል ጉዳት ድምጽ ለመስጠት ያልገደባቸው፣ ሕመም እና እርጅና የሀገር ተስፋን ከማየት ያላገዳቸው፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ጨቅላ ልጃቸውን ማዘል ያላደከማቸው፣ ከምንም በላይ የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ያላስቆማቸው ዜጎች፤ በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል ያሳዩት ጽናት ለዴሞክራሲና ለሀገር ሕልውና የተከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ከዚህ ሁሉ የሥልጡን ሕዝብ ትጋት በኋላ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ አረጋግጠዋል።
 
ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ዜጎች በነቂስ ወጥተው ከማለዳው 12፡ 00 ሠዓት ጀምሮ ድምፃቸውን መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
 
ረጃጅም ሰልፍ የነበረባቸውን የምርጫ ጣቢያዎችም እስከ ሌሊቱ 6 ሠዓት በማራዘም መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉን አመላክተዋል።
 
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ የ7ኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በተመለከተ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በነፃነት እና በሙሉ ፈቃዳቸው እንደተጠቀሙበትም ልዑካቸው ታዝቧል።
 
ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በተግባር አሳይተዋል፤ ያለምንም ጫና የሚፈልጉትን ፓርቲ መርጠዋል፤ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ እና በተዓማኒነት የተሞላ ሂደት ነው ብለዋል።
 
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብታቸውን በመጠቀም ድምጻቸውን መስጠታቸውን ዐይተናል ብለዋል።
 
የምርጫ ሂደቱ በተቀናጀ መንገድ መካሄዱን፣ በምርጫ ጣቢያዎችም ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ልጆቻቸውን የያዙ እናቶች፣ ወጣቶች እና አዛውንቶች ሳይቀሩ ከማለዳው ጀምሮ ድምጽ ሲሰጡ እንደነበር መታዘባቸውን ተናግረዋል።
 
በሁሉም አካባቢ የድምፅ መስጠት ሒደቱ በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን በመጠቆም፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የታየበት መሆኑን አስታውቀዋል።
  
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈፀም ዐቅም እያደገ መምጣቱ የታየበት ስኬታማ ምርጫ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን ናቸው።
 
ምርጫውን መታዘባቸውን በመጥቀስ፤ ምርጫው በርካታ ዜጎች የተሳተፉበት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በምርጫው አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ድምጻቸውን እንደሰጡም ነው የገለጹት፡፡
 
ይኸውም የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና ይበልጥ አካታች ተሳትፎን እያጎለበተ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።
 
አክለውም፤ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም አጋር አካላት ለምርጫው ስኬታማነት ሚናቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
 
የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት እንዲጠናከሩ በትኩረት መሠራቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ በመሆን የማስፈጸም ዐቅሙ እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
 
• ድኅረ ምርጫ
 
ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ፤ የ1 ሺህ 8 የምርጫ ክልሎች ውጤት ወደ ቦርዱ የማረጋገጫ ማዕከል መግባቱን ተናግረዋል።
 
የምርጫ ጣቢያዎች የውጤት ቆጠራ ተጠናቅቆ በምርጫ ክልሎች የማዳመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
ከ501ዱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች 446ቱ ወደ ማዕከል መድረሳቸውንና ቀሪዎቹ የክልል ምክር ቤቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
 
በሌላ በኩል በመጠለያ ጣቢያዎችና በካምፖች የድምፅ አሰጣጥ መከናወኑን ጠቁመው፤ ውጤት የማዳመር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
 
#ምርጫ #ኢዜአ #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት #Ethiopian_News_Agency #በኢዜአ ዐይን

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም