ምክክር - ወደ መግባባት መሸጋገሪያው ድልድይ! - ኢዜአ አማርኛ
ምክክር - ወደ መግባባት መሸጋገሪያው ድልድይ!
በዮሐንስ ደርበው
በአመለካከት መለያየት ሥሪቱ ተፈጥሯዊ ነው። ሰዎች ልክ በመልክ፣ ቁመት ውፍረት ወይም ቅጥነት ሥብጥር፤ ምድርም በተፈጥሮ አቀማመጥ እና በዓየር ጠባይዋ ወጥ እንዳልሆኑት ሁሉ ማለት ነው።
ለአንድ ሕዝብ እና ሀገር ብልጽግና ሲባል ከተበተነ ይልቅ የተደመረ ሐሳብ በእጅጉ ይጠቅማል። ሀገርኛ ብኂላችን “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” ብሎ መሰባሰብን እንደሚሰብከው።
የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ ይካሄዳል - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ከሥሪታቸው አንጻር ዕሳቤዎች የግድ ተጨፍልቀው አንድ እንዲሆኑ ባይጠበቅም፤ ሀገርና ሕዝብን ወዳስቀደመው በይበልጥ ገዥ ሐሳብ መቅረብ ግን ተገቢ ይሆናል። በአንጻሩ በተለያዩ ዋልታዎች ቆሞ መጓተት ለማን ይጠቅማል?
በምክክር ሁሉንም አሸናፊ አድርጎ መቋጨት እየተቻለ ለበርካታ ዓመታት የሐሳብ ልዩነቶች የወለዷቸው ግጭቶች፤ እንደ ሀገር አያሌ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ-ልቡናዊ እና ማኅበራዊ ክስረቶች ማስከተላቸውን ታሪክ ይነግረናል።
የለውጡ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከቸራቸው ትልልቅ ጉዳዮች የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ አንዱ ነው።
ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች ራሳችንን በታማኝነት ፈትሸን በሐሳብ ልየነቶች ላይ ለመነጋገር መፍቀዳችንን የሚጠይቅ ሂደት እንደመሆኑ፤ በቁጥር የማይተመኑ ረቂቅ የሆኑ ዋጋዎች አሉት። ይህም ፍላጎትን በኃይል ለመተግበር ሕይወትና ንብረት ከሚያወድመው ጦርነት ይልቅ አዋጭ የመግባቢያ መንገድ መሆኑን ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።
እዚህ ደረጃ ከመደረሱ በፊት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ኮሚሽኑ በየጊዜው ማሳወቁም ይታወሳል።
ሀገራዊ ምክክር በአካታችና አሳታፊ ውይይት ወደ የጋራ መግባባት መድረሻ አትራፊ መንገድ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ኃላፊነቱን ለመወጣት ለምክክር በሩን ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ክፍት አድርጓል።
በዚህም መሠረት ከዳያስፖራው፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለያዩ ክልሎች ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩና ሰላምን ከመረጡ ብሎም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ፤ አጀንዳዎችንም ተቀብሏል።
ኮሚሽኑ የመጨሻው የምክክር ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አካታች የምክክር ጉባዔ ለማካሄድ በማንኛውም ጊዜ ወደ ምክክሩ ለሚመጡ አካላት በሩ ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
👉 ሀገራዊ ምክክር ምን ይጠግናል?
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራ በሆነው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 384 ላይ እንደተቀመጠው፤ በሀገረ-መንግሥት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሕዝብ ተመካክሮ፣ የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ፣ የተግባባባቸውን በሕግና በሥርዓት አጽንቶ፤ ያልተግባባባቸውን ለወደፊት ምክክሮች አቆይቶ አልተጓዘም። በዚህ የተነሣ በየጊዜው ቅሬታ፣ ኩርፊያ፣ አብዮት፣ ዐመጽ ይፈጠራል። ነገሮች በተናጠል እየቀረቡ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታ ይመቻቻል። ሁለንተናዊ ዕይታ ይጠፋል። ሀገራዊ ምክክር ይህን የዘመናት ስብራት ይጠግናል።
👉 ሀገሬው ለበለጸገችና ጠንካራ ሀገሩ ምን ይጠበቅበታል?
መንግሥት በኢትዮጵያ የሐሳብ ገበያን ባሕል ለማድረግ እየተከተላቸው ካሉ መንገዶች አንዱ ሀገራዊ ምክክር ነው።
በመደመር መንግሥት መጽሐፍ (ገጽ 383) ላይ እንደሰፈረው ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሐሳቦች በአንድ መድረክ ቀርበው፤ በምክክርና ውይይት ጎልብተው አሰባሳቢና አስማሚ ሆነው የሚወጡበት መድረክ ነው። ስለሀገር የሚያገባው ሁሉም አካል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ አዋጥቶና ተነጋግሮ መግባባት የሚፈጥርበት ምኅዳር መሆኑም ተገልጿል።
ስለዚህ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚከናወነው ለዚህ ታሪካዊ ሁነት መሳካት ኢትዮጵያውያን ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
በሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ለመሳተፍ የተመረጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የባለ ድርሻ አካላት ወኪሎችም ውጤታማ ጉባዔ ማካሄድ የሚችሉበትን ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ሀገራዊ ምክክር በአንድ በኩል፤ አንድነትና ኅብረትን በማጠናከር ልሂቃንና ሕዝብ ለአንድ ከፍ ላለ ዓላማ በአንድ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋል። በዚህም ጥረቶች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ እንዲፈስሱ ያደርጋል። በሌላ በኩል ፖለቲካዊ መረጋጋትና ሰላምን በመፍጠር የመንግሥት ትኩረት፣ ሀብትና ጊዜ ሳይበታተን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ብቻ እንዲውል ያደርጋል (የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 403)።
#እንመካከር! #በምክክር_ከሰፈር_እስከ_ሀገር_የተሻለ_ነገን_እንገንባ!
#ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት
#ኢትዮጵያ_እየመከረች_ነው