በኢዜአ ዐይን …! - ኢዜአ አማርኛ
በኢዜአ ዐይን …!
በገበታ ለሸገር የተገለጠው የተደመረ ዐቅም - ለኢትዮጵያ ስኬቶች እንደማሳያ
(በሙሴ መለሰ)
ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማስፋፋት ስትወጥን የቀደመ ወረቷን፤ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ይዛ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የተሰኙ ትላልቅ ኢኒሼቲቮችን ቀረጸች። ይህን ዕውን ለማድረግ ስትዘይድም የሕዝቧን የፋይናንስ፣ የዕውቀት እና የጉልበት ዐቅም በመደመር መጠቀምን ሻተች።
በዚህም መሠረት በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ኢኒሼቲቮች በርካታ ስኬቶችን አስመዘገበች። ትሩፋታቸውም ሰፊ አበርክቷቸውም በርካታ ሆኖ ብቅ ብሏል።
✍️ ገበታ ለሸገር
በአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻዎችና መናፈሻዎችን ለማልማት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገው ገበታ ለሸገር ኢኒሼቲቭ፤ ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን የሚሸፍን ነው።
የሚሠራበትን ገንዘብ ለማሰባሰብም የገበታ ለሸገር የእራት ምሽት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ተዘጋጀ፤ ባለሀብቶች፣ የንግድ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ድርጅቶችም ተሳትፈዋል።
ኢኒሼቲቩ አንድነት ፓርክን ጨምሮ የእንጦጦ መናፈሻንና ሌሎች የተለያዩ መዲናዋን ያስዋቡ በረከቶችን ችሯል።
ይህም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት በማልማት በርካታ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልኅ አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ለዚህ ሁሉ ስኬት መነሻ የሆኑትን ጉዳዮች ያስጀመሩትም ያስፈጸሙትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለሸገር የተገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ ገበታ ለሀገር የተሰኘውን ኢኒሼቲቭ አበሠሩ።
✍️ ገበታ ለሀገር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻን ለማልማት ያለመ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል። ይህም በአዲስ አበባ ከተሠራው ገበታ ለሸገር ቀጥሎ የተከናወነ ነው።
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገበታ ለሀገር ዓላማ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የቱሪስት መስኅብ የሚሆኑና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ አካባቢዎችን ማዘጋጀት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በገበታ ለሀገር መርሐ-ግብር ባለሀብቶችን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህን ለማሳካት የሀገሪቱን ባለሃብቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ መርሐ-ግብሮች የተሳተፉበት የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ውጤታማ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገበታ ለሀገር ውጥን፤ እንደ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ እና ጎርጎራ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና የተፈጥሮ ሀብቶችን አጉልተው በማሳየት ይበል ያሰኘ ውጤት አስመዝግቧል።
✍️ ገበታ ለትውልድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም ገበታ ለትውልድ የተሰኘ ኢኒሼቲቭ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ይህም ተጨማሪ መዳረሻዎች እንዲለሙ አስችሏል።
በዚህ ኢኒሼቲቭ ሥር በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ነው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዳሴ ግድብ አካባቢና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች እየለሙ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውን የሸበሌ ሪዞርት በይፋ መርቀዋል።
እያንዳንዱ የሪዞርቱ ገጽታ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሐብት የሚያንፀባርቅ ነው። ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ትልቅ ታሪካዊ እጥፋት እንደሆነም ተገልጿል።
ሎጎ ሐይቅ ሪዞርትም ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረቀ ሲሆን፤ ለጎብኚዎች የማይረሳ ትውስታን የሚሰጥ እጅግ ማራኪ ቦታ ሆኖ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቋሚ ምስክርም ነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት።
የቱሪዝም ልማቱን ከተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ፣ ከዘላቂነትና ከአካታችነት ጋር በማቀናጀት፤ ሪዞርቱ የወሎ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ዕሴት ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቅበት ሰፊ ገበታ ሆኖ ያገለግላል።
ታሪካዊ ቦታዎችና የሀገር መገለጫ መሠረተ-ልማቶች ብሔራዊ ትርክቶችንም የሚገነቡ ናቸው።
በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት ብሎም በየአካባቢው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን ለማጎልበት፣ ብዙ ጎብኚዎችን ለመሳብ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
እንዲሁም ነባር ቅርሶችን በማደስና በመጠገን ለትውልድ ለማሻገር ደማቅ ዐሻራ አሳርፈዋል።
በሌላ በኩል የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት የመንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ዐሳይተዋል። ባለሀብቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሀገራቸውን የመሥራት ሚና እንደሚጠበቅባቸው አሥተምረዋል።
ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ብሎም በርካታ የሥራ ዕድሎች በመፍጠር በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በኢትዮጵያም ቱሪዝም መንግሥት ላስጀመረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የማዕዘን ድንጋይ ነው። ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎችም አንዱ የሆነው ለዚህ ነው።
መሠረተ-ልማቶች ከሚገነቡባቸው ጡቦች ባለፈ የነገን ሀገራዊ ማንነት፣ ራዕይ እና መዳረሻን ይበይናሉ። ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ እንኳንም ታሰቡ፤ እንኳንም ተሳኩ። ይህ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ተጨማሪ መዳረሻ ባላገኘች ነበር።