በኢዜአ ዐይን …! - ኢዜአ አማርኛ
በኢዜአ ዐይን …!
በዮሐንስ ደርበው
የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት በቀጣይ ...!
በየአዝማናቱ ሕዝብን በኅብረት ያሥተሣሠሩ ክስተቶች ይስተዋላሉ። ታሪክ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን በየጊዜው አንድ በሚያደርጓቸው ሀገራዊ ጉዳዮች መለያየት አይሆንላቸውም። እንደውም በመሃላቸው የሚከሰቱ አለመግባባቶች ሁሉ እንደጉም ተነው በጋራ መቆም የሠርክ ተግባራቸው ነው።
በዓድዋ፣ በካራማራ እና በሌሎችም ስፍራዎች ያደረጓቸውን ፀረ ባዕዳን ትግል ጨምሮ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባሉት የልማት ሥራዎች ያስመዘገቧቸው ድሎች በማሳያነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት የሚካተቱ ናቸው።
እነዚህ የኢትዮጵያን ኅልውና ለማስጠበቅ ሕዝቡ በአንድነት በመሰለፉ የተቀዳቻቸው ድሎች ናቸው። አንድነት ባይኖር ድሎቹ አይታሰቡም።
የጀግኖች አያቶቻቸው ልጆች በዚህ ዘመንም ትልቅ ድል አስመዝግበዋል፤ በቀጣይ ደግሞ ሌላ።
የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት የተገለጠበት ዘርፈ-ብዙ ፀጋ
ካላቸው ላይ ዕጃቸውን ያልሰበሰቡ፤ ኪሳቸውንም ያልዘጉ ኢትዮጵያውያን፤ በቁጭት፣ በደም፣ በላብ እና በጥሪታቸው ሀገራቸውን በክብር ያስጠራ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የመሰለ ሜጋ ፕሮጀክት ገነቡ። ፍሬውንም ማጣጣም ከጀመሩ ሰነባበቱ።
ይህ ጥቅመ-ብዙ ግድብ ከቀዳሚ ዓላማው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የተሻገሩ በርካታ ትሩፋቶች አሉት።
አንድነትን በማጠናከር ረገድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተደፈረ ጊዜ በዓድዋ ዘመቻ ወገን በኀብረት እንደቆመው ሁሉ፤ የሕዳሴው ግድብ በግንባታ ጊዜው የሀገሬው ኅብረት ማሠሪያ ሆኗል። በዚህ ዘመንም ለአንድ ዓላማ መቆምን በማስረጽ የራሱን ዐሻራ አኑሯል።
የሀገራቸውን ብልጽግና በሚሹ ታታሪዎች ርብርብ እንደመገንባቱ፤ ከምረቃ በኋላም የሚጠበቅበትን የኤሌክትሪክ ኃይል በማምረት ለሁሉም መሆኑን በተግባር አሳየ።
ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ባሏት የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ተደማሪ መስኅብ ሆነ። ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ፍሰት እየጎመራ የሕዝቡ ተጠቃሚነት እንዲያድግ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል።
እንደ ዜጋ ግድቡ በቁርጠኝነትና በብልኅ አመራርነት ለስኬት መብቃቱ ደስ ያሰኛል፤ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የጎብኝ መዳረሻ መሆኑ ደግሞ ተጨማሪ ፀጋ።
ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባል፤ አንድም አካባቢውን በመጎብኘት እንዲሁም ለጎብኝ ምቹ ሁኔታዎችን በማስፋፋት።
ምክንያቱም፤ የግድቡ ታሪካዊ አሠራር …ቁጭቱ…ቁርጠኝነቱ…አንድነቱ ... ራሱን የቻለ ታሪክ ነውና ይህን ሠንዶ ለጎብኝዎች በሚሆን መልክ ማንበር ያስፈልጋል።
የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት በቀጣይስ?
በሀገሪቱም በአኅጉሪቱም በዘርፉ ሜጋ የሆነውን ይህን ፕሮጀክት ለመልከ-ብዙ ፈተናዎች ሳይበገሩ በስኬት የቋጩ የዓድዋ እና ካራማራ ድሎች ባለቤት የሆኑት የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት በቀጣይ እንደ ባሕር በር ባለቤትነት ባሉ ትላልቅ የኅልውና ጉዳዮች ላይ ሊገለጥም ይገባል።
የባሕር በር ባለቤትነት የትውልድ ጥያቄ ነው። የሕዝብ ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ልዩነት አያሻም። “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር” ነውና ብኂሉ… ተባብሮ ኅልውናን ማስቀጠል እንጂ….
ደግሞም ይህ ታሪካዊ ስህተትን የማረቅ ሂደት ነው። በታሪክ፣ በሠነድ እና በሌሎችም ማሥረጃዎች ኢትዮጵያ ሐቅ አላትና።
በጥቃቅን ነገሮች የማይጠቅም የልዩነት በርን መክፈት አያሻም። ብርቱዎቹ ለልዩነት ዕድል ያልሰጡት በዓድዋ በካራማራ በኅብረት አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋል። የአሁኑ ትውልድም ኅልውናውን ለማቆየት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ የግድ ይለዋል።
ታሪክን መዘከር ተገቢ ነው፤ ጠብቆ በማቆየት መማርም። አሁንም ዳግም ታሪክ መሥራት ይገባል። ለዚህም በቁጭት መነሳት…የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ።
#ዓድዋ #ካራማራ #የብርቱዎቹ_ልጆች_ብርታት #ታላቁ_የኢትዮጵያ_ሕዳሴ_ግድብ #የባሕር_በር #ቀይ_ባሕር #የትውልድ_ጥያቄ #በኢዜአ_ዐይን