ትውልዱ ዛሬንም ነገንም በሚጠቅመው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ ዛሬንም ነገንም በሚጠቅመው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል
በኢዜአ ዐይን…!
በዮሐንስ ደርበው
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ጥቅም ንጥልም ቀላልም አይደለም፤ በተለያዩ ዐውዶች ገዝፎ ይገለጣል እንጅ።
ለአብነትም፤ የደን ሽፋንን በማሳደግ የዓየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ ብሎም በመከላከል፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ እንዲሁም በመከላከል ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የከተማ ውበት መጠበቅን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅሞችን በቀጥታ ለሰው ልጆች ይቸራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልጽግና አሠናሥሎ የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ነው። የደን፣ የሰብልና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅጣጫም ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ - ለዓየር ንብረት ለውጥ ላለመበገር የሚደረግ ትጋት
ጽንሰ ሐሳቡ ከችግኝ ተከላ የተሻገረው አረጓዴ ዐሻራ
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ መነሻ፤ የተራቆተ አካባቢን ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ከማድረግ የላቀ ድርብርብ ግብ ያለው ሰፊ መርሐ-ግብር ነው።
በዚህም መሠረት፤ እንደየ ሥነ-ምኅዳሩ የሚላመዱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላላቸው ችግኞች፣ ለደን ሽፋን ማደግ የጎላ ሚና ለሚኖራቸው ችግኞች፣ ለከተማ ውበትና ለማረፊያ ጥላ ለሚሆኑ ዛፎች፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚችሉ ዛፎች የሚተከሉበት ነው።
ይህም አንድን አካባቢ አረንጓዴ ከማድረግ ልቆ በረሃማነትንና የዓየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ፣ ምርታማነትን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ በቀጥታ ሕብረተሰቡን የሚጠቅም ትልቅ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ያስረዳል።
የተለያዩ ክፍላተ-ዓለማት አንድም በካፋ ቅዝቃዜ እንዲሁም መደበኛ የኑሮ ሁኔታን በሚያናጋ አደገኛ ሙቀት ብሎም በድንገተኛ ጎርፍ እና ሰደድ እሳት በሚታመሱበት ጊዜ፤ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለማረቅ አንዱ መፍትሔ አረንጓዴ ዐሻራን በስፋት ማከናወን መሆኑ ይታመናል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነትና ቁርጠኛ አመራር ሰጭነት ባለፉት ዓመታት በብርቱዎቹ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤ ውጤቱንም ሕዝቡ ዐይቷል።
ከውጤቶቹ መከካልም ለአብነት፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉ፣ የምርታማነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መጨመር ብሎም ውብና አረንጓዴ ከተሞች መስፋፋት የሚሉት ይነሳሉ።
በሕዝቡ ዘንድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተፈጥሮን የመንከባከብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ጭምር ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።
የአረንጓዴ ዐሻራን ውጤት ላጣጣመ ሥራውን በንቃት እንዲከውን መካሪ ባያሻም፤ ካለፈው የበለጠ ውጤት እንዲገኝ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጠው የአረንጓዴ ዐሻራ በነቂስ መሳተፍ እና ባሕላቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ከአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች መካከል
• በሰብል፣ ፍራፍሬ፣ ቡና ምርታማነት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነት በ2011 ዓ.ም ጅማሮውን ያደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ አሁን ዘርፈ-ብዙ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተገለጠ ነው።
ከበርካታ ትሩፋቶቹ መካከልም የምርታማነት ማደግ ተጠቃሽ ነው። ይህን ተከትሎም የሕብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አድጓል። ይህን ሐሳብ በአኃዝ አስደግፎ ብናየው፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፊት (በ2010 ዓ.ም) በሔክታር የሚመረተው ስንዴ 22 ኩንታል፣ በቆሎ 30 ኩንታል፣ ጤፍ 17 ኩንታል እንዲሁም ገብስ 23 ኩንታል ነበር።
ከኢንሼቲቩ ትግበራ በኋላ ደግሞ (በ2017 ዓ.ም) ስንዴ በሔክታር 36 ኩንታል፣ በቆሎ 46 ኩንታል፣ ጤፍ 20 ኩንታል፣ ገብስ 30 ኩንታል ማምረት ተችሏል። በዚህም መሠረት በ2017 ዓ.ም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 280 ሚሊየን ኩንታል ማምረት ተችሏል።
ስንዴን በትጋት በማምረትም ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረን 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፍራፍሬው ዘርፍ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በዚህም ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ሕብረተሰቡ (አምራቹ) ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ በዚያው ልክ እንዲያድግ አስችሏል።
ኢትዮጵያም በአፍሪካ አቮካዶን በቀዳሚነት ወደ ውጭ የምትልክ ሁለተኛዋ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።
ሌላኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ትሩፋት የቡና ልማት መስፋፋትና የውጭ ምንዛሬ ማደግ ነው። ይህን በአሥረጂ አስደግፈን ብንመለከት፤ በ2011 ዓ.ም በ600 ሺህ ሔክታር ላይ ቡና ተተክሏል። 500 ሺህ ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ተሰብስቧል። 738 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ ቡና ተተክሏል። 1 ነጥብ 58 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ተሰብስቧል። 2 ነጥብ 65 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢም ማግኘት ተችሏል።
እንዲሁም ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ጋር በተያያዘ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ከላይ የተጠቀሱ ማሳያዎችን (ናሙናዎችን) ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በቀጥታ ለሕዝቡ ጥቅም የቆመ መርሐ-ግብር መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።
ስለዚህ በቀጣይ ሕብረተሰቡ በዚህ ኢኒሼቲቭ ላይ ያለጠባቂነት በንቃት በመሳተፍ እና ባሕሉ በማድረግ ተጠቃሚነቱንም በዚያው ልክ ለማሳደግ መትጋት ይጠበቅበታል።
ሕጻናትን ለውስብስብ ችግር የሚዳርገው ህመም
ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ አበርክቶዎች መካከል
• በመሬት መራቆት መቀነስ፣ በደን ሽፋን ማደግ፣ በውኃማ አካላት መስፋፋት ረገድ
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ፤ የአካባቢ መራቆትን በመቀነስና በመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል፣ በደን መጨፍጨፍ ምክንያት ይከሰት የነበረን የበረሃማነት መስፋፋት ቀንሷል፣ የደን ሽፋንን ጨምሯል፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ መሬት እንዲያገግም በማድረግ ምርታማነትን ጨምሯል።
በተጨማሪም የውኃማ አካላትን መመናመን ቀንሷል (ደርቀው የነበሩ ስፍራዎች ወደ ቀድሞ ውኃማ ይዘታቸው እንዲመለሱ አስችሏል)፣ የአካባቢ መራቆትና የዓየር ንብረት ፈተናዎችን በመቀነስ ረገድም የራሱን ከፍተኛ ሚና አበርክቷል።
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ትግበራዋ ስኬታማነት ዓለም ዕውቅና ችሯታል
በሀገር አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማትና መሪዎች ዘንድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ትግበራ ተወድሷል።
ከእነዚህ ዕውቅናዎች መካከል፤ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአግሪኮል ሽልማት መስጠቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) Outstanding African Leadership Award ማግኘታቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ።
እንዲሁም፤ ኢትዮጵያ 2ኛውን የአፍሪካ የዓየር ንብረት ጉባዔ ተመርጣ ማስተናገዷ፣ ኢትዮጵያ 2ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የሥርዓተ-ምግብ ጉባዔ ማስተናገዷ፣ በ80ኛው የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ጉባዔ ለዘላቂ ደን ልማት የተሰጣት ዕውቅና እንዲሁም ኢትዮጵያ ኮፕ-32 (COP- 32) ለማስተናገድ መመረጧ በዘርፉ ላከናወነችው አርዓያነት ያለው ተግባር የተሰጡ ዕውቅናዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ስኬታማውን የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ትልሟን ለሀገራት ማጋራቷ
ኢትዮጵያ በራሷ ሐሳብ አመንጭነት ሕዝቧን አስተባብራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እየተሰጠ ባለ ያልተቆራረጠ ጠንካራ አመራር በአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፍ ያስመዘገበችውን ስኬት፣ አሠራር (ልምድ) እና ችግኝ ለተለያዩ ሀገራት አጋርታለች። ይህም እየሄድችበት ያለው መንገድ ሁሉ ተባብሮ ማደግን ያነገበ ለመሆኑ አሥረጂ ነው።
በዚህም መሠረት፤ በ2012 ዓ.ም ለፑንትላንድ፣ በ2012 ዓ.ም ለፓኪስታን፣ በ2012 ዓ.ም ለጂቡቲ፣ በ2013 ዓ.ም ለደቡብ ሱዳን፣ በ2013 ዓ.ም ለሩዋንዳ እና ለሌሎችም በዘርፉ ያላትን የተመሠገነ ልምድ አጋርታለች።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የተመራበት ሂደት
የኢኒሼቲቩ ሐሳብ አመንጭ እና አመራር ሰጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው። ወደ ክልል፣ ዞን ወረዳ እና ቀበሌ በማውረድም በተቀናጀ ትጋት በመመራቱም ስኬታማ መሆን ችሏል።
በዚህም መሠረት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነትና አመራር ሰጭነት፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት፣ በክልል ርዕሳነ-መሥተዳድሮችና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ቅንጅት፣ በየደረጃው በተዋቀረ የቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት፣ በተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ አማካኝነት የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በስኬት እየተተገበረ ይገኛል።
ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በተያያዘዘ የቀጣይ አቅጣጫዎች
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የለውጡ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ላለፉት ዓመታት በተቀናጀ አግባብ ተመርቷል፤ አሁንም እየተተገበረ ነው። በቀጣይ ደግሞ ኢኒሼቲቩ እንዴት መከናወን እንዳለበት ግቦች ተቀምጠዋል።
በዚህም መሠረት፤ የሕዝብ ባለቤትነትን አጠናክሮ ማስቀጠል (አረንጓዴ ባሕል መገንባት)፣ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ሥራዎችን ማስፋትና በደን ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፣ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለይቶ በጥናት መመለስ የሚሉት የቀጣይ አቅጣጫዎች ናቸው።
በተጨማሪም፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፣ በክረምት ወራት የሚተከሉ ችግኞችን በበጋ ወራት በአግባቡ መንከባከብ ከቀጣይ አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ በሆኑበት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ወቅት አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከል ሲሉ ለሀገሬው ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተገለጠ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም መጀመሩም የሚታወስ ነው።
#አረንጓዴ_ዐሻራ #ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency #ተስፋን_እንትከል