ቀጥታ፡

ለልብ ህመም አጋላጭ መንስዔዎች ምንድናቸው?

የጤና ነገር …

በዮሐንስ ደርበው

የሰው ልጅ ሊሻሻሉ በሚችሉ እና በማይችሉ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለልብ ህመም ሊጋለጥ እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና የአዋቂ የልብ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ብርሃኑ ሞገስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የልብ ህመም ከተወሳሰብ ዘላቂ የጤና እክል እስከ ድንገተኛ ኅልፈት ያደርሳል።

ለልብ ህመም አጋላጭ መንስዔዎች

ሰዎች ማሻሻል በሚችሏቸው (ሞዲፋይብል) እና ማሻሻል በማይችሏቸው (ነን ሞዲፋይብል ወይም ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች) ለልብ ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ ዶክተር ብርሃኑ ይገልጻሉ።

መሻሻል ከሚችሉ አጋላጭ ምክንያቶች መካከል፤ ከፍተኛ ጭንቀት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ህመም (በአግባቡ መድኃኒቱ ካልተወሰደ)፣ተገቢ ያልሆነ የስብ ክምችት፣ ከፍተኛ ውፍረት (ክብደት)፣ በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጤናማ አመጋገብ አለመኖር እንዲሁም አብዝቶ ስኳር፣ ጣፋጭና አልኮል መጠቀም የሚሉትን ይጠቅሳሉ፡፡

እንዲሁም ሰዎች ማሻሻል ከማይችሏቸው (ተፈጥሯዊ) አጋላጮች መካከል፤ በቤተሰብ የሚተላለፍ መኖሩን፣ በዕድሜ መጨመር የሚከሰት መሆኑን (ለምሳሌ፡- ወንድ ከ45 ሴት ከ55 ዓመት በላይ ሲሆናቸው ለልብ ህመም ሊጋለጡ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን) እንዲሁም ወንዶ ከሴቶች በይበልጥ ለልብ ህመም ተጋላጭ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡

የልብ ህመም ምልክቶች

የደረት ውጋት በግራ በኩል ወይም መሐል ላይ፣ ከወትሮው የተለየ ድካም፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ከመደበኛው የተለየ የልብ ምት መኖር፣ የሰውነት በተለይም እግር አካባቢ እብጠት፣ ራስን መሳት እና ሳል የልብና ተያያዥ ህመም ምልክት ሊሆኑ እንደሚችሉ አብራርተዋል።

የልብን ጤናን ለመጠበቅ

በተቻለ መጠን ጤናማ አመጋገብን መከተል እንደሚገባ የሚመክሩት ዶክተር ብርሃኑ፤ አትክልት ማዘውተር፣ ምግብ ሲዘጋጅም ፈሳሽ ዘይት መጠቀም፣ ስኳር፣ ጨው እና ጣፋጭ ነገሮችን መገደብ ከተቻለም ማስወገድ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህም ብስክሌት መንዳት፣ በእግር እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ዋና መዋኘት፣ እስከሚያልብ እና የልብ ምት እስከሚጨምር ብሎም እስከሚደክሙ የአካል ብቃት መሥራት የልብን ጤና ለመጠበቅ አስተዋጽዖ አለው ነው ያሉት፡፡

ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ማድረግ ተገቢ መሆኑን ያነሱት የሕክምና ባለሙያው፤ “ቦዲ ማስ ኢንዴክስ (ቢ ኤም አይ)” ከ18 ነጥብ 5 እስከ 25 እንዲሆን ይመከራል ብለዋል፡፡

ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል አለመጠቀም፣ የስኳር ህመምና ከፍተኛ ደም ግፊት ካለም የመድኃኒት አወሳሰድን አለማስተጓጎል፣ አመጋገብ ላይ ስብ አለማብዛትና አብዝቶ አለመቀመጥ የልብ ህመምን ለመከላከል እንደሚያግዙ ነው ያስረዱት፡፡

ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ጤናማ ሰዎች ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ባሉ ጊዜያት አንድ ጊዜ፣ ዕድሜያቸው ከ45 በላይ የሆኑ በየዓመቱ እንዲሁም የልብ ህመም ያለባቸው እንደሁኔታው በየጊዜው ክትትል እንዲያደርጉም መክረዋል፡፡

ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሳቸውን ከልብ ህመም እንዲጠብቁ መክረው፤ ከዚህ ያለፈ ችግር ሲኖር ቶሎ የሕክምና ክትትል ማድረግ እና “ዛሬ ነገ” በማለት ጊዜ እያባከኑ ህመሙ ውስብስብ ደረጃ እስኪደርስ መጠበቅ እንደማይገባቸው አሳስበዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ጤና #የልብ_ህመም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም