ቀጥታ፡

ከመጋቢት ሥጦታዎች መካከል - የጉባ ብሥራቶች  

በዮሐንስ ደርበው

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የለውጥ ብሥራት ከጫፍ እስከ ጫፍ የተሰማበት ነው። በለውጡ የስምንት ዓመታት ፈጣን ጉዞ በየዘርፉ ይበል የሚያሰኙ አመርቂ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በስምንት ዓመት ጉዞ ውስጥ ከስኬት ወደ ስኬት በመሻገር በርካታ ተግባራት ተሠርተዋል። የሀገሪቷን ቀጣይና ዘላቂ እድገት የሚያተልሙ፣ ሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት የተከናወነባቸው ስምንት ዓመታት አልፈዋል። ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ቃል በመግባት የተግባር እርምጃ ተጀምሯል።

•  የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን ተከትሎ ይፋ የተደረጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች - የጉባ ብሥራቶች  

ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

በዚሁ ወቅት ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን ደስ አላችሁ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ታሪክ ሆኖ የሚቀጥል ገድል ነው ብለዋል። 

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ኢትዮጵያ ወደ ሌላ ምዕራፍ እንደምትሸጋገር አብሥረዋል።

በቀጣይ የሚገነቡ ሜጋ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችንም ጉባ ላይ ይፋ አድርገዋል። ለፕሮጀክቶቹ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ይደረጋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶችም፤ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅ፣ የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ሁለተኛው የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ቤቶችን መገንባት የሚሉት ናቸው።

እነዚህ የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየሠራች መሆኗን ያረጋግጣሉ። ለዚህም ማሳያ የጉባ ብሥራቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኢኮኖሚ ዐቅም ያጠናክራሉ።

•  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያኔ ካበሠሯቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል።

ወር ባልሞላ ጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በዚሁ ወቅትም የማዳበሪያ ፋብሪካው በዓመት 3 ሚሊየን ቶን ማዳበሪያ አምርቶ ያቀርባል ማለታቸው ይታወሳል።

ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሐ-ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ በወቅቱ፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት የኃይል ደኅንነትን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርና የረጅም ጊዜ የመቋቋም ዐቅም ግንባታ ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የልማት ተነሳሽነት ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ንጹህ የኃይል አቅርቦት የማመንጨት ዐቅምን በማላቅ በጤና፣ ግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና የምርምር ትግበራ ማዕቀፍ የተቃኘ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

በተመሳሳይ መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይም አስቀምጠዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅ፤ የኢትዮጵያን የናፍጣ እና የቤንዚን ፍላጎት ከ80 እስከ 90 በመቶ የመሸፈን ዐቅም እንዳለው በዚሁ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ አስጀምረዋል።

በወቅቱም፤ አውሮፕላን ማረፊያው በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት እንደሚሆን ተመልክቷል። ይህም ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪዬሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከዓለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መናኸሪያዎች አንዷ የሚያደርጋትን በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ ዐቅም ይኖረዋል።

•  በአጠቃላይ የጉባ ብሥራቶች የኢትዮጵያን ዕድገት በማሳለጥ ሂደት የጎላ ድርሻ አላቸው። 

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ብሎም በኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያበረክታሉ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆንም ያስችላሉ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ያላትን ዐቅም በማሳደግ፤ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ፣ መሠረተ-ልማቶችን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው ይታመናል።

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራ የመጨረስ ዐቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን እያየን ነው። በቀጣይም የጀመረቻቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ባሰበችው ጊዜ እንደምታጠናቅቅ እሙን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም