ቀጥታ፡

የጤና ነገር … 

በጾምና ጾም በማይኖርበት ወቅት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት በሰውነት ጤና ላይ የየራሱ ተጽዕኖ ስላለው በአግባቡ መደረግ እንዳለበት ይመከራል።

👉 ከወትሮው በተለየ በጾም ወቅት እንዲዘወተሩ የሚመከሩ ምግቦች አሉ?
 
o  የምግብ ሳይንስና ኒውትሬሽን መምህር፣ ተመራማሪ እና ደራሲ ይሁኔ አየለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጾም ወቅት ሰውነት ይደክማል፤ በሚፈልገው ልክ ፈሳሽ ያለማግኘት ሁኔታም ሊያጋጥመው ይችላል። ለዚህ ደግሞ በቀላሉ የሚፈጩ እና ሰውነት የሚፈልገውን ፈሳሽ ማስገኘት የሚችሉ ምግቦችን መጠቀም ይመከራል ነው ያሉት።

o  በዚሁ መሠረት ከጾም በኋላ ምግብ በሚበላበት ሠዓት እንደ ጭማቂ (ጁስ)፣ ሾርባ፣ አጥሚት፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ተልባ፣ ኑግ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መጠቀም ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተጨማሪም በፕሮቲን ይዘታቸው የበለጸጉ የጥራጥሬ ዓይነቶችን (ባቄላ፣ አተር፣ ምሥር፣ …) በማብሰል መጠቀም እንደሚመከርም ነው ያመላከቱት።

o  ጾም ከመፍታት በፊት (ከምግብ በፊት ውኃ መጠጣት) ድርቀት የነበረበትን የሰውነት ክፍል እርጥበት እንዲኖረውና ለተሳለጠ የምግብ መፈጨት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

o  ሥብጥራቸው በርከት ያሉ የምግብ ዓይነቶችን መመገብ አንዱ የሌለው ንጥረ ነገር ከሌላኛው ስለሚገኝ በዚህ አግባብ መመገብ ለጤናማ ሕይዎት እንደሚመከርም ያስረዳሉ።

✍️ ጥናቶች ስለ ጾም ምን አሉ?
 
o  ጾም በሳይንስ የተደገፉ ጥቅሞች እንዳሉትና የጤና አንድ አጋር እየሆነ መምጣቱን ተመራማሪው ገልጸዋል። አክለውም፤ ከበርካታ በሽታዎች እራስን በመጠበቅ ጤናማ ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ታውቆ በስፋት የኑሮ ዘይቤ አካል እየሆነ መምጣቱን ነው ያመላከቱት።

o  በጾም ወቅት ሰውነት እራሱን ያጸዳል፤ ይህም በብዙ መልኩ ጤናማ ሕይወት እንዲኖር ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

o  ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ወይም በይበልጥ እንዳይወሳሰቡ ለማድረግ ጾም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ማመላከታቸውንም ጠቁመዋል።

o  በተለይም ክብደትን እና በሰውነት ውስጥ ያለ የስብ ክምችትን ለመቀነስ ብሎም ከፍተኛ ደም ግፊትን እንዲሁም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ጾም አንድ የሕይዎት ዘይቤ እየሆነ ነው ይላሉ ተመራማሪው።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ጤና #የጾም_ወቅት_አመጋገብ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም