ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት

ከመጋቢት 13 እስከ መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል

•  የ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ መመረቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን እና የሰው ልጅ ታሪክ በጀመረበት ምድር የተገነባውን ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ባሳለፍነው ሳምንት መርቀዋል።

በዚሁ ወቅት ሎጁ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት መሠራት የነበረበት ቢሆንም፤ አሁን ስለዘገየን አንቆጭም ማለታቸው ይታወሳል።

ይህን ስለሠራንም አንረካም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሩጫችን ገና ብዙ እንደሆነ፣ አፋር ገና እንዳልተነካ አስበን ይህን ጅማሮ ይበልጥ በማላቅ ለማስቀጠል እንተጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

• ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ ማድረጋቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከቃና ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ከተሞች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የከተማ ፕላን፣ የዘላቂ ልማት እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባንና ሌሎች ከተሞችን እንዴት እየቀየሩ እንደሆነም ገለጻ አድርገዋል።

እንዲሁም የመሠረተ ልማትን፣ የንግድና የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመላው ሀገሪቱ ለማሳደግ ያላቸውን ፋይዳም አንስተዋል።

• ኢትዮጵያ በማላቦው ጉባዔ

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ11ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ ወደ ማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ያቀኑት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

ማላቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢኳቶሪያል ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል  ኡሳ ኡዙዌን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጉባዔው ከመጋቢት 18 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን እስከ መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል።

•  የልማት ሥራዎች ጉብኝት በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት ይበልጥ የሚያጎሉና ግንባታቸው እየተፋጠኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ መሠረተ-ልማት እና የአየር መንገድ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል ሲሉም በወቅቱ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎንደርን የውኃ ጥም ይቆርጣል፤ የገበሬውን መሬት ያጠጣል፤ የአካባቢውን ምኅዳር ይለውጣል የተባለው የመገጭ የመጠጥ ውኃ ግድብ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

በዚሁ ወቅት የሀገር ሀብት ፈስሶባቸው መክነው እና ባክነው የቀሩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ከሞት እያስነሡ ማፋጠን የዚህ መንግሥት ልዩ መለያው ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የመገጭ ግድብ ምስክር መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት መርቀዋል።

በዚሁ ወቅትም በአንድ ወር የግንባታ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ይህ ሞዴል መንደር በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የቆየውን የጤና ጣቢያ፣ የመብራትና የውኃ አገልግሎት ጥያቄ በተግባር መልሷል ብለዋል።

በሀገራችን ከተማው ብቻ ሳይሆን ገጠሩም እኩል እየተዋበ፣ በልማት እየተገነባና በዕድገት ፍኖት ላይ በጽኑ መሠረት እየተራመደ ይገኛልም ነው ያሉት።

ይህ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የማሸጋገር ትልቁ ማሳያችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

• "Invest in Ethiopia 2026" የቢዝነስ ፎረም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት፤ በአዲስ አበባ 4ኛው "Invest in Ethiopia 2026" የቢዝነስ ፎረም ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅትም፤ የምንፈልገው ድጋፍን ሳይሆን አጋርነትን ነው፤ እርዳታን ሳይሆን ኢንቨስትመንትን ነው! ለባለ ሀብቶች ምቹ፣ ግልጽና ተራማጅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ ለችሎታ እና ለዕድል በሯን ወለል አድርጋ መክፈቷንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁን በፍጥነት ወደ ከፍታ እየገሠገሠች ባለችበት በዚህ ታሪካዊ የዕድገት ጉዞ፤ ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያ ለእናንተ ዝግጁ የሆነ፣ በዕድሎችና በስኬቶች የተሞላ ታላቅ የኢንቨስትመንት መሶብ አላት፤ ኑ አብረን እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል!

• የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት

የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በሰጡት መግለጫም፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።

በዚህም ከክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር፣ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀሌ እና በአዲስ አበባ ከ22 ጊዜ በላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ ሂደቱን በክልሉ ለማካሄድ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች ባለመፈጠራቸው፤ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫ ሂደቱ በአዲስ አበባ እንዲከናወን መወሰኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም