ቀጥታ፡

በኢዜአ ዐይን …!  

በዮሐንስ ደርበው

የሥልጣኔ ቁንጮ -በምርጫ ካርድ መሪን መምረጥ! 

በያዝነው ዓመት ወርኃ ግንቦት በባተ 24ኛው ቀን ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ቀን ቆርጣለች። ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅና የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት ወደ ትግበራ ምዕራፍ ገብታለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ተዓማኒ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን፤ ቀሪ ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል። ለዚህም የምርጫ ሕጉን ከማሻሻል ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥርዓቶች ወደ ሥራ መግባታቸው በአሥረጂነት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የምርጫ ትምህርትና ግንዛቤን ለማስፋት ለሚሠሩ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መሰጠቱ፤የምርጫ ሂደትን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥም በርካታ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች በኦንላይን ሥርዓት በታዛቢነት መመዝገባቸውን አስረድቷል።

በኢዜአ ዐይን …!

በገበታ ለሀገር የተገለጠው የተደመረ ዐቅም - ለኢትዮጵያ ስኬቶች እንደማሳያ

የጤና ነገር …

እንዲሁም ዐለም ዐቀፍ ታዛቢዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  አማካኝነት መጥተው ፈቃድ የሚወስዱበት ዝግጅት እየተደረገ ነው። 

ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ምዝገባ አወዳድሮና ገለልተኝነታቸውን በፖለቲካ ፓርቲዎች አስተችቶ ያሠለጠናቸውን 187 ሺህ 28 የምርጫ አስፈጻሚዎች አሠማርቷል።

ለመራጮች ምዝገባ የተዘጋጁ 46 ሺህ 757 ጣቢያዎች እና ተጨማሪ በርካታ ንዑስ ጣቢያዎችም ተሠናድተዋል።

እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ፤ 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘንድሮው ምርጫ ለውድድር ተመዝግበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ 73 ዕጩዎች በግል ለውድድር መቅረባቸው ተገልጿል።

ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ የሚከናወነው ሁሉም ፓርቲ ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደሆነ ያስማማል። የምርጫው ስኬት የሚረጋገጠውም ቦርዱ ለብቻው በሚያደርገው ጥረት ሳይሆን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዕኩል ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል መሆኑ ይታመናል።

በመሆኑም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰባት ምዕራፎችና በ30 አንቀጾች የቀረበውን የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈርመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሂደት የዜጎችን ተሳትፎ ለማበረታታት “ምርጫችን ነው-ሀገር ያለኛ” የተሰኘ የምርጫ ኅብረ-ዝማሬ ማስመረቁ ይታወቃል። በዚሁ ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ኅብረ-ዝማሬው አካታች ተሣትፎን ለማበረታታት መሠናዳቱን አስገንዝበዋል።

የልዩ ልዩ ድምጾች ኅብራዊነት ያለውን የጋራ ጥንካሬ በማሳየት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የዜጎችን ተሳትፎ ማጎልበት የኅብረ-ዝማሬው ዓላማ መሆኑም ተገልጿል። 
በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫም “የሀገር ካስማ” የተሰኘ ኅብረ-ዝማሬ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በግንቦት ወር ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ነው። እስካሁን ባለው መረጃ ምዝገባው እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይቀጥላል።

የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ የሚገኘውም፤ በመደበኛ የመራጮች ምዝገባ (ማኑዋል)፣ ምርጫዬ በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ እና በድረ ገጽ ነው። ከአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17 ሺህ ያህሉ የዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ተደራሽ ለማድረግ ሲሠራ መቆየቱን ቦርዱ ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በማንዋልና በዲጂታል አማራጭ በተከናወነ የመራጮች ምዝገባ ከ28 ሚሊየን 365 ሺህ 310 በላይ መራጮች ተመዝግበዋል።

በኢትዮጵያ የምርጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 37(7) ላይ ቦርዱ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች ምሥልና የመለያ ምልክቶችን አቀማመጥ፣ ቅደም ተከተልና እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ግልጽ በሆነ መንገድ በመመሪያ እንደሚወስን ይደነግጋል።

በዚህም መሠረት ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን ቅደም ተከተል ለመወሠን የሚያስችለውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ባሳለፍነው መጋቢት 14 ቀን በይፋ አስጀምሯል።

የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት የሚከናወነው በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች ምሥልና የመለያ ምልክት አቀማመጥን የሚወሥነው የዕጣ ማውጣት ሂደት መጠናቀቅን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የዓየር ሠዓት ድልድል የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል። 

በዚህም መሠረት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ24 ሬዲዮ፣ በ20 ቴሌቪዥን እና በ6 ጋዜጦች በሕዝብና በንግድ ሚዲያዎች ነጻ የዓየር ሠዓት ተድልድሎላቸዋል። 

የሠዓት ድልድሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የግል ዕጩዎችም አማራጭ ሐሳባቻቸውን እንዲያጋሩና የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ብሎም ከመራጩ ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል የሚሰጥ ነው።

ይፋ በተደረገው ነፃ የዓየር ሠዓት የተመዘገቡ 46 የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች በኃላፊነት ስሜት እንዲጠቀሙ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ በምርጫ ካርድ መሪን መምረጥ ከሥልጣኔ ቁንጮዎች አንዱ ሆኖ ይነሳል። የመራጮች ምዝገባ ሂደትም የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ያጎለብታል።

ምርጫ፤ ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ፣ ተቋማዊ አሠራርን እንዲያጠናክሩ ብሎም በካርዳቸው ይሁንታ የሚመራቸውን መምረጫ ቁልፍ ነው።

ኢትዮጵያ በወሳኝ የምርጫ ወቅት ላይ ናትና፤ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

#ምርጫ #ኢዜአ #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት #Ethiopian_News_Agency #የመራጮች_ምዝገባ #በኢዜአ_ዐይን

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም