ማህበራዊ
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከንቲባዎች በአዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስራዎችን ጎበኙ
May 12, 2024 69
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፡- ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከንቲባዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስራዎችን ጎበኙ። ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከንቲባዎችና የዓለም ዓቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል። በቆይታቸውም በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ የትውልድ ግንባታ ስራዎችን ጨምሮ ዋና ዋና የልማት ስራዎች ዙሪያ ልምድ የሚካፈሉ ይሆናል። በዛሬው እለት በማለዳም በአዲስ አበባ የተሰሩ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የተለያዩ አገራት ከንቲባዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና ሌሎችም የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም የወላጆችና ተንከባካቢዎች የምክር እና አቅም ግንባታ አገልግሎት የሠለጠኑ የ2ኛ ዙር ስልጣኞች የምረቃ መርኃ ግብር ላይም ተገኝተዋል። በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው መርሃ ግብር 3 ሺህ 85 ስልጣኞች ተመርቀዋል።
ለጽዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የገቢ ማሰባሰቢያ (ዲጂታል ቴሌቶን) መካሄድ ጀመረ
May 12, 2024 91
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2016(ኢዜአ)፦ ለጽዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የገቢ ማሰባሰቢያ (ዲጂታል ቴሌቶን) በይፋ መካሄድ ጀምሯል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት ክብርን ጠብቆ የመፀዳዳት ባህልን ለማዳበር ዜጎች በንቅናቄው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። በዚህ ንቅናቄ እስከ አሁን ድረስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ ተቋማትና ሰራተኞቻቸው እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ዜጎች የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ድጋፍ በማበርከት አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለት እየተከናወነ ላለው ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የገቢ ማሰባሰቢያ (ዲጂታል ቴሌቶን) ኢትዮጵያዊያን የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያበረክቱ መልዕክት ሲተላለፍ ቆይቷል። በዚህም በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መካከል ላይ ውብ ሆኖ በተሰራው የመንገድ ፕሮጀክት ላይ በርካታ ዜጎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው የአንድ ጀምበር 50 ሚሊዮን ብር ዲጂታል ቴሌቶን ለማካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀው በይፋ መካሄድ ጀምሯል። በዝግጅቱም ኢትዮጵያውያን ለጽዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የገቢ ማሰባሰቢያ (ዲጂታል ቴሌቶን) ከዚህ በታች በተመላከተው ሂሳብ ቁጥር የሚችሉት ድጋፍ እንዲያበረክቱ ተጋብዘዋል። ለ#ጽዱኢትዮጵያ For a #CleanEthiopia በንግድ ባንክ በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር 1000623230248፣ በብሔራዊ ባንክ የዶላር አካውንት 0101211300016 እና በስዊፍት ኮድ NBETETAA የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄን ይቀላቀሉ።
በሀረሪ ክልል 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን በተሳካ መልኩ ለማክበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገለፀ
May 11, 2024 80
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ በቀጣይ ወር በታላቅ ድምቀት በሀረር ከተማ የሚከበረው 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን በተሳካ መልኩ ለማክበር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል። የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀንን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ አለም አቀፍ የሀረር ቀን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአለም ሀገራት ሲከበር መቆየቱን ጠቁመዋል። በቀጣይ ወር በሀረር ከተማ የሚከበረው የዘንድሮው 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን የተሳካ እንዲሆን የክልሉ መንግስት በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ንኡሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱን ገልፀው በአሁኑ ወቅትም ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። በዓሉ በሀረር ከተማ መከበሩ በውጭ የሚኖሩ ሀረሪዎችና የሀረር ተወላጆች ታሪኮቻቸውን፣ ባህሎቻቸውንና እሴቶቻቸውን በአግባቡ እንዲያውቁ ከማገዙም ባለፈ ከሀገራቸውና ከህዝባቸው ጋር ያላቸው ትስስርና አብሮነት እንዲያጠናክር ያስችላል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሀረሪዎች እና የሀረር ተወላጆች ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን በማስተባበር በክልሉ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በዓሉ ሀረር ከተማ መከበሩም መልካም ገጽታ ለመገንባት፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትና የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመላክተዋል። የክልሉ መንግስትም 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን መርሃግብር የተሳካ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በተለያዩ አለማት የሚገኙ ሀረሪዎችና የሀረር ተወላጆችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሶስተኛው ትውልድ ያስተላለፉትን ጥሪ በመቀበልና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።  
አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ ለማድረግ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
May 11, 2024 110
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 03/2016(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ እንዲሁም ወላጆችና አሳዳጊዎች በእውቀት ልጆቻቸውን አሳድገው ለወግ ማዕረግ የሚያበቁባት ለማድረግ በትጋት ማገልገላችን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ በማህብራዊ ትስስር ገጻቸው በትውልድ ግንባታ ዙሪያ እየሰራን ካለነው ስራ ልምድ ለመቅሰም ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመጡ እንግዶችን ዛሬ ተቀብለናል ሲሉ አስፍረዋል። አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ ለማድረግ ግልፅ ራዕይ አስቀምጠን በዚያ ላይ በመመርኮዝ እስከ 2018 ድረስ ምንም ገቢ የሌላቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሁሉን አቀፍ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያገኙ ህጻናትንና 330 ሺሕ የሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችና ህጻናትን ማዕከል ያደረገ የተመጣጠነ ምግብ ፣ የትምህርት ፣ የጤናና የስነ ልቦና ግንባታ ቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል። ይህ የትውልድ ግንባታ ስራ የሚተገበረው ከጽንስ ጀምሮ እስከ ስድስት ዓመት ባሉ ህጻናት ላይ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ለእናቶች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ 5000 ባለሞያዎችን በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባታቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች 4000 የሚሆኑ መምህራንን በቅድመ መደበኛ ሙያ በማሰልጠን ወደ ተግባር እንዲገቡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል። እስከ አሁን በተገኘ ውጤት ለሕጻናት ጤና አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ የጤና ተቋማትን ማሸጋገር፣ መምህራንን በማሰልጠን ሕጻናትን በጨዋታ እንዲያስተምሩ ማድረግ ፣ ከ597 በላይ የህጻናት መዋያ ቦታዎችን በግልና በመንግስት ተቋማት መገንባት ፣ ለልጆች መጫወቻ እንዲውሉ 305 መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ ማከናወን እና 114 መንገዶችን በመለየትና ዝግ እንዲሆኑ በማድረግ ለህጻናት ግልጋሎት እንዲውሉ አድርገናል ብለዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ እንዲሁም ወላጆችና አሳዳጊዎች በእውቀት ልጆቻቸውን አሳድገው ለወግ ማዕረግ የሚያበቁባት ለማድረግ በትጋት ማገልገላችን እንቀጥላለን ነው ያሉት።  
በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረትና ሆዳቸው የተጣበቀ ሕፃናት ተወለዱ
May 11, 2024 90
አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፦ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረትና ሆዳቸው የተጣበቀ መንትያ ሕጻናት መወለዳቸውን ሆስፒታሉ አስታወቀ። የሆስፒታሉ የጽንስና ማህፀን ስፔሻሊስት ዶክተር አረጋኸኝ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት በሆስፒታሉ በደረትና ሆዳቸው ላይ የተጣበቁ ሕፃናት ተወልደዋል። ሕጻናቱ የተጣበቁ እንደሆነ የታወቀው በ8ኛው ወር ወላዷ ለእርግዝና ክትትል በመጡበት ወቅት በአልትራሳውንድ ምርመራ መሆኑን ተናግረዋል። ሕጻናቱ የተጣበቁ በመሆኑ በምጥ ማዋለድ እንደማይቻል የገለጹት ዶክተር አረጋኸኝ፣ ቀኑ ሲደርስ በቀዶ ሕክምና ለማዋለድ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። ነዋሪነታቸው በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ የሆኑት ወላድ እናት ቀናቸው ደርሶ እንደመጡ የሆስፒታሉ የሕክምና ቡድን ትናንት ባካሄደው ከአንድ ሰዓት በላይ የወሰደ የቀዶ ሕክምና ሕጻናቱን ያለምንም ችግር በሰላም ማዋለድ መቻሉን ገልጸዋል። ተጣብቀው የተወለዱት ሕጻናት በጾታ ወንድ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር አረጋኸኝ፤ ጭንቅላት፣ እጆችና እግሮቻቸው የተለያየ ቢሆንም የጋራ አንድ ልብና አንድ እትብት እንዳላቸው አስረድተዋል። የደረትና ሆድ መጣበቅ በሙያ ቋንቋ ቶራኮ ኦምፓሎፓገስ (Thoraco-Omphalophagus) በሚል መጠሪያ እንደሚታወቅም አመልክተዋል። እንደ ዶክተር አረጋኸኝ ገለጻ፣ እንደዚህ አይነት ክስተቶች ከ100 ሺህ እናቶች መካከል በአንዷ ላይ ሊከሰት ይችላል። የሕጻናቱን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በተመለከተም በከፍተኛ የሕክምና ተቋም ሕጻናቱን ማለያየት የሚቻልበት ዕድል እንደሚኖርም ዶክተር አረጋኸኝ ተናግረዋል። ነገር ግን የአንዱን ህይወት መታደግ እንደማይቻል አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የእናትየው እና የሕጻናቱ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝና አስፈላጊው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የፍትህ ዘርፉን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል - ቢሮው
May 11, 2024 71
ደሴ፤ ግንቦት 3/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የፍትህ ዘርፉን በማዘመን ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በደሴ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም እንደገለጹት በዘርፉ ያሉ አሰራር መመሪያዎችንና አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡   ለዚህም አዲስ የፍትህ ተቋማት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተው፤ በሪፎርሙ አሳሪ መመሪያና ደንቦችን በማሻሻል ተደራሽና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት ወራት ኅብረተሰቡን በማወያየት ሪፎርሙን የሚያጠናክሩ ግብዓቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ በሂደትም ክፍተቶችን በማስተካከል የህግ የበላይነት እንዲከበር በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። እንዲሁም ሀሰተኛ ምስክርን ለመከላከል፣ የፍትህ ተደራሽነትንና ጥራትን የሚያሳድጉ ተግባራት በተሻለ ሁኔታ መከናወናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የደንበኞች የአቤቱታ መዝገቦችን በፍጥነት በማየት ውሳኔ እየተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም የማሻሻያ ሥራዎቹን በማስቀጠል የፍትህ ስርዓቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደበበ ቸሬ በበኩላቸው በዞኑ በየደረጃው ባሉ ተቋማት የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም የወንጀል መዛግብት ምርመራ 98 በመቶ እንደተከናወነ ገልጸዋል።   ይህም የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ሪፎርም አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ተችሏል ብለዋል፡፡ የህዝብና የመንግስት ሀብት በመጠበቅ ፍትህ ለማስፈን በተደረገ ጥረት በዞኑ ሊመዘበር የነበረ 72 ሚሊዮን ብር በማሳገድ ከዚህ ውስጥ 11 ሚሊዮን ብር ወደ መንግስት ካዝና ገቢ የተደረገ ሲሆን ቀሪው ገንዘብ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ''ለወረዳዎች ድጋፍ በማድረግ ዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው'' ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሰይድ ናቸው፡፡   ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የግምገማ መድረክ የምስራቅ አማራ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች አመራር አባላት፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡  
በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው
May 11, 2024 71
አዳማ ፤ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፡- በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ። የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ብዙ ወጪ ሳያወጡ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ምቹ እድልን እየፈጠረ ሲሆን ህክምና ባለማግኘት የሚያጋጥም ዘላቂ የጤና ችግርን ለመግታትም ዓይነተኛ ሚናን እየተወጣ ነው። የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በአገልግሎቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ በአገልግሎት አሰጣጥና በአቅርቦት ማነስ ምክንያት ቅሬታ እየቀረበ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተካናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች በሁሉም ወረዳዎች እንዲከፈቱ ማድረግና በተለየ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ማበራከት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የአባላት ቁጥር የመጨመር ስራ በሚጠበቀው ልክ አለመሰራቱ እንዲሁም ከማህበረሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ በጊዜ ወደ ባንክ አለማስገባት ሌላው ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የጤና መድህን አገልግሎት የሚመራበትን የአሰራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት በሁሉም ደረጃ ያለ አመራር ቀዳሚ ስራ እንዲሆን በጤና ሚኒስቴር በኩል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከጤና መድህን አባላት የሚሰበሰበው ገንዘብም ከማህበረሰቡ ከተሰበሰበ በኋላ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ባንክ ገቢ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለክልል ጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች የህክምና መሳሪያዎችና ተሽከርካሪ ማሟላት፣ ጽህፈት ቤቶች ማደራጀትና ምቹ የጤና አገልግሎት መስጫ አካባቢን በመፍጠር በኩልም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የህዝብ ቅሬታን ለመፍታት ያግዛል ተብለው በቀጣይ ከተያዙ እቅዶች አንዱ ለጤና ባለሙያዎቹ ምቹ የስራ አካባቢን የመፍጠር ስራ በትኩረት እንደሚከናወንም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው የአገልግሎቱን ጠቀሜታ የማስረዳት ስራ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።   በዚህ ወቅት በአገሪቷ በሚገኙ 3 ሺህ 631 ጤና ተቋማት የጤና መድህን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በህዝብ አቅም በተገነቡ 472 ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እየቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል። የማህበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ አባላትን ቁጥር ለመጨመር ከተሞችን፤ የመንግስት ተቋማትና ጡረተኞችን የማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በቀጣይ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች አገልግሎቱ እንዲጀመር አስፈላጊ ድጋፎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡    
የሐረሪ ክልል ማረሚያ ኮሚሽን የላቀ የስራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጠ
May 11, 2024 58
ሐረር ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፦ የሐረሪ ክልል ማረሚያ ኮሚሽን የላቀ የስራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል። የማዕረግ እድገቱን የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በክሪ አብደላ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ፣ የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለታ በዳዳና ሌሎች የክልሉና የማረሚያ ቤት የስራ ሃላፊዎች ሰጥተዋል።   የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በክሪ አብደላ በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የማዕረግ እድገቱ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል ነው። የማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ መኮንኖቹ በቆይታ ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፆ ምስጋና ያቀረቡት አቶ በክሪ፣ ለሌሎች አባላት ዓርዓያ ሆነው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።   የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለታ በዳዳ እንደገለጹት፤ ዕድገቱን ያገኙት የማዕረግ የቆይታ ጊዜያቸውን የሸፈኑና የላቀ የስራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መኮንኖች መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይ ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን በስነ-ምግባርና በሙያ እንዲታነጹ በሚያከናውነው ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል። በዚህም የማረሚያ ቤቱ ለ26 ከፍተኛ መኮንኖች የኮማንደር ማዕረግ እንዲያገኙ መደረጉን ኮሚሽነር ለታ ተናግረዋል። ማረሚያ ቤቱ እያከናወነ የሚገኘውን የህግ ታራሚዎችን የማረምና የማነጽ ተግባርና ሃላፊነትን ባግባቡ እንደሚወጣም አመልክተዋል።  
የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት ያስተላልፋል
May 11, 2024 67
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት ለባለ ዕድለኞች በእጣ የሚያስተላልፍ መሆኑ ተገለጸ። መከላከያ ሠራዊቱን የቤት ባለቤት ለማድረግ በሠራዊቱ ፋውንዴሽን በኩል ፍጥነት የተሞላበት የቤቶች ግንባታና ልማት ላይ ሠፊ ሥራ በመሥራት ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ እንደሚያስተላልፍ ተመላክቷል። የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ከዚህ በፊት ተመዝግበውና ቆጥበው መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ የሠራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ ስድስት ቤቶች በእጣ ያሥተላለፈ መሆኑ ይታወቃል።   በዛሬው እለትም ተጨማሪ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ሠላሳ ስድስት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በእጣ የሚያሥተላልፍ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል። በጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብረሃም በላይ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ጄኔራል መኮንኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የኦቪድ ኮንስትራክሽን ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም የሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለ "ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ ድጋፍ አደረጉ
May 10, 2024 92
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ በበይነ መረብ ባዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። በፕሮግራሙ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሰፊው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ባካሄደችው በርካታ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያሳየው ከፍተኛ ድጋፍ በእጅጉ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል።   አያይዘውም ይህ ንቅናቄ የአገራችን ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ንቅናቄው ለአካባቢ ንጽህና እና ጤና ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በስብሰባው የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ታላቅ ዓላማ መሳተፋቸው ደስ የሚያሰኛቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መሳካት የሚቻላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በዕለቱ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ በአጠቃላይ በዓይነት 18 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 12 መጸዳጃ ቤቶችን ለመስራት ቃል የተገባ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ 17ሺህ 945 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም 74 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መሰብሰቡ ተጠቅሷል። በኤምባሲው የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞችም ለንቅናቄው ከደመወዛቸው መለገሳቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል
May 10, 2024 92
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር እንደሚገባቸው ተገለጸ ። ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ (ሜይ 12) እየተከበረ ይገኛል ፡፡ እለቱ በየዓመቱ የዘመናዊ ነርሲንግ እናት በምትባለው እንግሊዛዊት ፍሎሬንስ ናይንትንጌል የልደት ቀን ይከበራል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ59ኛ ጊዜ የሚከበረው የነርሶች ቀን በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል "የእኛ ነርሶች፤የእኛ የወደፊት ፤ የእንክብካቤ ኃይል "በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል ። በመርኃ ግብሩ ላይ የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ደጉማ፣የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሆስፒታሉ ነርሶች ተገኝተዋል ። ዶክተር ደረጀ ደጉማ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በበሽታ መከላከልና ጤና ማበልፀግ ፣ አክሞ ማዳንና በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች የማይበገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው መስኮች ናቸው ፡፡ ነርሶች ታካሚን በመንከባከብ ፣ቤተሰቡንና ቤተዘመዱን በማንቃትና በማስተማር ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ዕውቅናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል ፡፡ በዚህም ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ በበኩላቸው ነርሶች ታማሚው ከህመሙ በአካልም ሆነ በመንፈስ እንዲፈወስና የጤና ፖሊሲው ተግባራዊ እንዲሆን አበክረው የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዚሁ ተግባራቸው ህብረተሰቡ ነርሶችን ማመስገን እንዳለበት በመናገር ነርሶችም የአኩሪ ሙያ ባለቤት በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባችኋል ብለዋል። የዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን በበኩላቸዉ ነርስ ማለት ተንከባካቢ ፣ ፈዋሽ ፣ መንፈስ አዳሽ ፣ በሽታ እንዳይመጣ የሚከላከልና በፈውስ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ባለሙያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በሆስፒታሉ ለረዥም ጊዜ በነርሲንግ ላገለገሉና በስራቸዉ ታታሪና ምሳሌ ለሆኑ ባለሙያዎች ዕውቅናና ሰርትፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የነርሶችና የሚድ ዋይፎችን ሳምንት አክብሯል ፡፡ በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር አንዷለም ደነቀ፤ባለሙያዎች ቀኑን ከማክበር በዘለለ ህክምና በቅን ልብና በትህትና የሚሰራ ስራ መሆኑን ተረድተው ህብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል። በመርኃ ግብሩ ተቋሙን ከ40 ዓመት በላይ ላገለገሉ ባለሙያዎች የዕውቅና ሽልማት በመስጠት ሶስት ሰራተኞችን በክብር ሸኝቷል። የሚድ ዋይፎች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንቦት 5 የሚከበር ሲሆን በአገራችን ሚያዚያ 30 ''አዋላጅ መር ቀጣይነት እንክብካቤ''በሚል መሪ ቃል ተከብራል። በተመሳሳይ የነርሶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ሜይ 12 የሚከበር ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ''ነርሶች ለወደፊት የኢኮኖሚ ሃይል ትልቅ አቅም ናቸው'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሮ ውሏል።  
ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ለሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ሰጥቷል
May 10, 2024 248
ጂንካ ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት መስጠቱን ገለጸ። ስድስተኛው ዙር የምርምር ጉባዔ ''ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥ'' በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ በተጓዳኝ የማህበረሰብን ችግር በዘላቂነት የሚፈቱና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት በሚሆኑ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጓል። በተለይም የአከባቢው ማህበረሰብ መሰረታዊ ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ግኝቶች አማካኝነት ለማመላከት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በዩኒቨርሲቲው ከተሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች በዋናነት በአካባቢው በብዝሃ ባህሎች ውስጥ የሚገኙ አገር በቀል ዕውቀቶች ጎልተው እንዲወጡ መደረጉንና አካባቢው በተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ በመሆኑ ድርቅን የሚቋቋም ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙና መፍትሄ የሚያመላክቱ ስራዎች መሰራታቸውን እንደ አብነት አንስተዋል። እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰተውን የምርት መቀነስ ችግር መፍታት የሚያስችሉ እና ምርታማነትን በእጥፍ የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር በማላመድ የአካባቢው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ሌሎች በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለሚሰሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ግብአት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች መሰራታቸውን በማከል። ኮንፈረንሱም ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ በቀጣይ ችግር ፈቺ የሆኑ ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በጋራ ለመስራት እና ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ ዓመት 20 የሚሆኑ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ ዓለሙ ናቸው። እነዚህ የጥናትና ምርምር ስራዎች በይዘት ከፍ ያሉ ከመሆናቸው ባለፈ ለትምህርት ጥራቱ አጋዥ ከመሆን ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች የሚፈቱና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።   በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በኮንፈረንሱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጥናትና ምርምር ስራዎች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች እንዲጎለብቱ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል። በሀገሪቱ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማስመዝገብና ዘላቂ የልማትና የእድገት ግቦችን ለማሳካት ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ስራዎች ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው በማከል። በመሆኑም ምሁራን አገር የሚያሻግሩና የአገር ብልፅግናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ በይዘታቸውና በጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሰርተው ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በጀት ከመመደብ አንስቶ ለምርምር ስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በሟሟላት ተመራማሪዎችን እና የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ምሁራን ማበረታታት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባዔ በአገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ከ40 በላይ ጥናት አቅራቢዎች የጥናትና ምርምር ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።                  
የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
May 10, 2024 115
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፡- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር ተፈራረመ። ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋንፎል ተፈራርመዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ስምምነቱን አስመልክቶ እንደገለጹት በርካታ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት በህገ ወጥ መንገድ ይሸጋገራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ስደተኞች ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም ይተላለፋሉ ብለዋል። በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች ለእንግልትና ለተባባሰ ችግር እንደሚዳረጉ ጠቅሰዋል። መንግስት በዚህ ረገድ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት። ለዚህም በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የአምስት ዓመት እቅድ አንዱና ዋነኛው ሲሆን እቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የአጋር አካላት ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። ከዓለም የፍልሰት ድርጅት ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ቀደም ሲል በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን ለማጠናከርና ለቀጣዩ የአምስት አመት እቅድ አተገባበር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው በየትኛውም አገራት የሚገኙ ሰዎች ህገ-ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ መጀመራቸውን ጥናቶች ማመላከታቸውን ገልጸዋል። በተለይም ለመሸጋገሪያነት አመቺ ናቸው ተብለው በሚታመኑ አገራት የፍልሰተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመው በዚህም ስደተኞች ለተባባሰ ችግር የሚዳረጉባቸው እድሎች ሰፊ መሆናቸውን አክለዋል። በመሆኑም በፍልሰትና የስደተኞች ደህንነት ማረጋገጥ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በርብርብ በመስራት ጉዳቱን መግታትና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ድርጅታቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።      
የታላቁ አል ነጃሺ 00 መንደር ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ቀደምት የአብሮነት ታሪክ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው - አደም ካሚል 
May 10, 2024 65
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፡- የታላቁ አል ነጃሺ 00 መንደር ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ቀደምት የአብሮነት ታሪክ ለዓለም የሚያስተዋውቅ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል ገለጹ። በኢትዮጵያ እስልምና የተጀመረበትን፣ የታሪኩን መነሻና መገኛ ለመጠቆም ታላቁ አል-ነጃሺ 00 መንደር ግንባታ የጅማሮው ማብሰሪያ መርሀ ግብርም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል። በመንደሩ የተለያዩ ንዑስ ፕሮጀከቶች የታሰቡ ሲሆን የሙዚየም፣ ሃላል ሆቴሎችና ሎጆች፣ የአምልኮ ስፍራዎችን ጨምሮ የጥናትና ምርምር ተቋማት የሚገነቡ ይሆናል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲና ሌሎች የትምህርትና የህክምና ተቋማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የመሰብሰብያ አዳራሾች እንደሚገነቡም እንዲሁ። ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል የአል ነጃሺ ታሪክ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሙስሊሞች ታሪክ ነው ይላሉ። በተለይም ነብዩ መሀመድ ተከታዮችን በመቀበል ሲያጋጥማቸው የነበረው ችግር እንዲቀረፍ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል። ይህ ታሪክ ለኢትዮጵያውያን ክብር በመሆኑ ስፍራውን የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ስራ የሚደገፍ መሆኑን አንስተዋል። በሀገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሰላምና እውነት ምድር እንደሆነች ነብዩ መሀመድ እንደመሰከሩላት ተናግረው፤ በጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በተሰደዱ ወቅት በተወለዱበት ቀዬ ያጡትን ሰላም ከኢትዮጵያ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ታላቁ አል ነጃሺ 00 መንደር ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ቀደምት የአብሮነት ታሪክ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ታሪክ ለማሳወቅ፣ ማዳበርና በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ለማድረግም መድረኮችን ከማመቻቸት አንፃር ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።                                        
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ነው
May 10, 2024 579
ዲላ ፤ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተከትሎ ለጎርፍና ለአፈር ናዳ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጋንታ ጋምአ ለኢዜአ እንደገለጹት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የበልግ ዝናብ ስርጭት በክልሉ የጎርፍና የአፈር ናዳ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል። በተለይ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ አሌ እና አሪ ዞኖች ለጎርፍና ለናዳ እንዲሁም ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶና ጌዴኦ ዞኖች ለጎርፍ አደጋ የመጋላጥ ስጋት ያለባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በመሆኑም በክልሉ የአደጋ ተጋላጭ አካባቢዎችን በመለየት ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ 148 ቀበሌዎች ከ75 ሺህ በላይ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ለአደጋ ተጋላጭነታቸው ተለይቶ የቅደመ መከላከል ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በጋሞና ወላይታ ዞኖች የናዳ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ከ600 በላይ አባውራዎችን አንስቶ ከስጋት ነጻ በሆኑ አካባቢዎች የማስፈርና መልሶ የሟቋቋም ሥራ መከናወኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል። እንዲሁም በገጠር የጎርፍ መቀልበሻ በከተሞች ደግሞ ቱቦዎችን የማጽዳቱ ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የቅድመ መከላከል ሥራ አደጋን ለመቀነስና ለማስቀረት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ፣ ህብረተሰቡ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ራሱንና ንብረቱን በማራቅ የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉም አሳስበዋል። በክልሉ የአደጋ ሥጋትን በዘላቂነት ለመቀነስም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ኮሚሽነር ጋንታ ተናግረዋል።   የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነው የዝናብ ስርጭት በበልግ የለማን ሰብል ለጉዳት ይዳርጋል የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ወደማሳው የሚገባ ውሃን በማፋሰስና የውሀ መቀልበሻ በመስራት ሰብሉን ከጉዳት መከላከል እንዳለበት ተናግረዋል። እንደ ደቡብ ኦሞ ዞን ያሉ በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ተፋሰሶችን ከደለል ነጻ የማድረግ፣ ኩሬዎችን የመቆፈር እና መሰል የቅድመ መከላከል ሥራዎችን መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። እንደ ሃላፊው ገለጻ፣ አደጋን ከመከላከል ባለፈ አጋጣሚውን ለመጠቀም በክልሉ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ለቀጣይ የሰብል ልማት የሚሆን ውሃ የመያዝ ሥራ እየተከናወነ ነው። በተለይ እየጣለ ያለውን ዝናብ በማቆር ለእንስሳትና ለመስኖ ልማት በማዋል ስጋቱን ወደመልካም አጋጣሚ ለመቀየር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።  
ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ መሳካት በሀገራዊ ባለቤትነትና በሃላፊነት መስራት ከሁሉም ይጠበቃል - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
May 9, 2024 110
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ መሳካት በሀገራዊ ባለቤትነትና በሃላፊነት መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ። የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ታድመዋል።   በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ የማዘጋጀቱ ስራ ባለፉት 15 ወራት በገለልተኛ የሙያተኞች ቡድንና ባለድርሻ አካላት ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ረቂቅ ፖሊሲው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁም አይዘነጋም፡፡ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ለዘመናት ለቆዩ ችግሮች የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል። ለዚሁ የተሳካ ትግበራም በሀገራዊ ባለቤትነት መንፈስ ሁሉም መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ፤ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ቂምና ቁርሾዎችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የሽግግር ፍትህ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።   በመሆኑም ፖሊሲው የሌሎች ሀገራትን ልምድ በመቅሰም ካለው ሀገራዊ ልምድና ተሞክሮ ጋር በማጣጣም መተግበር ይገባል ብለዋል። በሂደቱም፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ሲቪል ማህበራትና ህብረተሰቡን የሚወክሉ አደረጃጀቶች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። ከትችትና እርስ በእርስ ከመነቃቀፍ በመውጣት ለነገዋ ኢትርዮጵያ ተቀራርቦ መስራት ተገቢ ነው ሲሉም አንስተዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ የሽግግር ፍትህ መሰረታዊ ግቡ በኢትዮጵያ ለተፈፀሙ በደሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡   በሂደቱ የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እውነትን ማረጋገጥ፣ የተጎዱትን መጠገን ወይም የማካካሻ ስርዓት ማበጀትና ተገቢውን ክብር መስጠት መሆኑን አስረድተዋል። በደሎች እንዳይከሰቱ መከላከልና ብሔራዊ መግባባቶችን ማሳለጥ በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ መሆኑንም ገልጸዋል። መንግስት የተሟላና ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለማዘጋጀት አስቀድሞ የገለልተኛ ሙያተኞች ቡድን በማዋቀር ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል። ከ80 በላይ ህዝባዊ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ማህበረሰቡ በስፋት ሃሳብ እንዲሰጥ መደረጉንም ገልጸዋል። በመሆኑም ለፖሊሲው ውጤታማነት መላ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡    
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋራ እሴቶችን በምርምር በማጎልበት በሠላም ግንባታና ዕድገት የሚጠበቅበትን ለመወጣት እየሰራ ነው
May 9, 2024 95
ሀዋሳ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋራ እሴቶችን በምርምር በማጎልበት በዘላቂ ሠላም ግንባታና ዕድገት ላይ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ አስታወቁ። ዩኒቨርሲቲው ብዝኃነት፣ የጋራ እሴትና ሠላም በኢትዮጵያ ዘላቂ እድገት ያላቸው አበርክቶ በሚል ሀሳብ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤውን ዛሬ ተካሂዷል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ብዝሃ ማንነቶችና ባህሎችን እንደ ፀጋ በመጠቀምና የጋራ እሴቶችን በማጎልበት ዘላቂ ሠላምንና ልማትን ማረጋገጥ ይቻላል።   ዩኒቨርሲቲው ኢትጵያውያንን የሚያስተሳስሩ የጋራ እሴቶችን በምርምር በማጎልበት በዘላቂ ሠላም ግንባታና እድገት ላይ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በአካባቢው የሚገኙ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለመገንባት የሚጠቅሙ ባህሎችና ዕሴቶች ላይ ምርምሮችን ማካሄድና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻዎች እንዲወያዩ አውዶችን የመፍጠር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፊጮ፤ እንደሀገር ያሉንን ብዝኃ ባህሎችና ማህበራዊ መስተጋብሮች በማጥናት ጥቅም ላይ ከዋለ በሠላምና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።   ሀገር በቀል እውቀቶች በውስጣቸው የያዙትን የሠላምና ልማት ግንባታ እሴቶች በጥናትና ምርምር መለየት እንዲሁም በግኝቶች ላይ የሀሳብ ልውውጥ ማድረግ ከምሁራን የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል። ኮሌጁ እንደ ዛሬው ዓይነት ጉባኤዎችን በማዘጋጀት ግኝቶች በሀሳብ ዳብረው እንዲወጡ ብሎም ለፖሊሲ አውጪ አካላት በተገቢው መንገድ እንዲደርሱ የማድረግ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ብዝሀነት በራሱ የግጭት መንስኤ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር ዘለቀ፤ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ ስለመሆኑ የትስስራቸውን ፋይዳ በምርምር ማሳየትና የዕውቀት ክፍተቶችን መሙላት ይጠበቅብናል ብለዋል። ኮሌጁ በቅርቡ "ኢንዲጂኒየስ ስተዲ" በተሰኘ ትምህርት ክፍል በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል። ትምህርት ክፍሉ በተለይ በሀገር በቀል የግጭት አፈታት፣ የህክምና፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች ዕውቀቶች ላይ የሚመራመሩ ምሁራንን የማፍራት ዓላማ ያለው እንደሆነ ጠቅሰዋል። የጋራ በምንላቸው እሴቶችና ሀብቶቻችን ላይ በቂ ጥናት መደረግ አለበት ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን ትምህርት ክፍል ባልደረባ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ናቸው።   አሁን ላይ ጅምሮች ቢኖሩም መጠናከር አለባቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ጥናቶች የሚያስገኟቸው የመፍትሔ ሀሳቦችና አማራጮችን ለትውልዱ ማስተማር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። የጋራ እሴቶች አንዱን ከሌላው የሚያቀራርቡ በመሆናቸው ጎልብተው እንዲወጡ የትምህርት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት የማሳወቁን ስራ ሊወጡ ይገባል ብለዋል። በምርምር ጉባኤው ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን እንዲሁም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል።
ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
May 9, 2024 99
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፦ የጤና ሚኒስቴርና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ ከማስፈታት ጀምሮ መልሶ የማቋቋም ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል። የቀድሞ ታጣቂዎችን ለሰላምና ምርታማነት ለማዘጋጀትም ማህበራዊ ተሃድሶ፣ አዕምሯዊ ዝግጅትና ግንዛቤ መስጠት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም እንዲሁ፡፡ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫም የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው የተሐድሶ ሂደት ውስጥ በመቀላቀል የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዛሬው እለትም የጤና ሚኒስቴርና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ማህበረሰቡን የሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሥነ-ልቦና ምክርን ጨምሮ የተሟላ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚቻል ይሆናል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር)፤ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በሚሰማሩበት ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ የጤና ሁኔታ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል። የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ የቀድሞ ታጣቂዎች ተመልሰው ለሀገር የሚጠቅሙ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ የሁሉም እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ታጣቂዎች ጤናቸው ተጠብቆ የተስተካከለ ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችል ስለመሆኑ አንስተዋል።  
በሲዳማ ክልል የተተገበረው የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል እያገዘ ነው
May 9, 2024 97
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 1/2016(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደጊዜ እንዲሻሻል ማድረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቶ ማሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት የፍትህ አካላት ተቀናጅቶና ተናቦ በመስራት በኩል ክፍተት ነበረባቸው። በዚህም በመንግስት የተሰጣቸውን ተግባርና ተልዕኮ በፍጥነት፣ በቅልጥፍና፣ በጥራት እና በውጤታማነት ከማሳካት አኳያ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል። እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በመንግስት የተነደፈው የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በክልሉ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ በፍትህ ሥርዓቱ ውጤት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በዘርፉ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠትና ከውጤታማነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በባለሙያው ላይ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ችግሮችን ለይቶ የማጥራት ሂደት መከናወኑን ተናግረዋል። በዚህም ባለሙያዎች እንደየጥፋታቸው ክብደት በዲስፕሊንና በወንጀል እንዲጠየቁ መደረጉን አክለዋል። አቶ ማቶ እንዳሉት፤ የተከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎች በዘርፉ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ የህዝብ ተአማኒነትን ለማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው። ለዚህም የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ነባር አሰራሮችን በማሻሻል በዘርፉ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከጊዜ ወደጊዜ እንዲሻሻል ማድረጉን ጠቁመዋል። በፍትህ ተቋማትም መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነትን እንዲሰፍን እንዲሁም የዜጎችን መብቶችና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል እየፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል። በተለይ ዕቅዱን መነሻ በማድረግ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የልማትና የዕድገት እንቅፋት እንዳይሆን እና የፍትህ ስርዓቱ እንዲጠናከር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል። ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ ፍትህ ከመስጠት አኳያ በየጊዜው መሻሻል ቢኖርም የህዝብ ተአማኒነት የማግኘት ውስንነቶች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን አቶ ማቶ ጠቁመዋል። "በመሆኑም የህዝቡን ተአማኒነት ሙሉ በሙሉ ማግኘት የሚቻለው ሁላችንም በህዝብ አገልጋይነት ስሜት ጠንክረን ስንሰራ ነው" ብለዋል። የፍትህ መጓተትና የፍርድ ጥራትን የሚፈታተኑ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም