ቀጥታ፡

በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለ "ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለ"ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና" ንቅናቄ በበይነ መረብ ባዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በፕሮግራሙ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሰፊው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ባካሄደችው በርካታ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያሳየው ከፍተኛ ድጋፍ በእጅጉ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል።


 

አያይዘውም ይህ ንቅናቄ የአገራችን ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ንቅናቄው ለአካባቢ ንጽህና እና ጤና ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በስብሰባው የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ታላቅ ዓላማ መሳተፋቸው ደስ የሚያሰኛቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መሳካት የሚቻላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በዕለቱ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ በአጠቃላይ በዓይነት 18 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 12 መጸዳጃ ቤቶችን ለመስራት ቃል የተገባ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ 17ሺህ 945 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም 74 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መሰብሰቡ ተጠቅሷል።

በኤምባሲው የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞችም ለንቅናቄው ከደመወዛቸው መለገሳቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም