ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02/2016 (ኢዜአ)፦ ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር እንደሚገባቸው ተገለጸ ።
ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ (ሜይ 12) እየተከበረ ይገኛል ፡፡
እለቱ በየዓመቱ የዘመናዊ ነርሲንግ እናት በምትባለው እንግሊዛዊት ፍሎሬንስ ናይንትንጌል የልደት ቀን ይከበራል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ59ኛ ጊዜ የሚከበረው የነርሶች ቀን በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል "የእኛ ነርሶች፤የእኛ የወደፊት ፤ የእንክብካቤ ኃይል "በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል ።
በመርኃ ግብሩ ላይ የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ደጉማ፣የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሆስፒታሉ ነርሶች ተገኝተዋል ።
ዶክተር ደረጀ ደጉማ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በበሽታ መከላከልና ጤና ማበልፀግ ፣ አክሞ ማዳንና በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች የማይበገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው መስኮች ናቸው ፡፡
ነርሶች ታካሚን በመንከባከብ ፣ቤተሰቡንና ቤተዘመዱን በማንቃትና በማስተማር ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ዕውቅናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል ፡፡
በዚህም ነርሶች የጤናው ስርዓት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ በበኩላቸው ነርሶች ታማሚው ከህመሙ በአካልም ሆነ በመንፈስ እንዲፈወስና የጤና ፖሊሲው ተግባራዊ እንዲሆን አበክረው የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለዚሁ ተግባራቸው ህብረተሰቡ ነርሶችን ማመስገን እንዳለበት በመናገር ነርሶችም የአኩሪ ሙያ ባለቤት በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባችኋል ብለዋል።
የዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን በበኩላቸዉ ነርስ ማለት ተንከባካቢ ፣ ፈዋሽ ፣ መንፈስ አዳሽ ፣ በሽታ እንዳይመጣ የሚከላከልና በፈውስ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ባለሙያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሆስፒታሉ ለረዥም ጊዜ በነርሲንግ ላገለገሉና በስራቸዉ ታታሪና ምሳሌ ለሆኑ ባለሙያዎች ዕውቅናና ሰርትፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተመሳሳይ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የነርሶችና የሚድ ዋይፎችን ሳምንት አክብሯል ፡፡
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር አንዷለም ደነቀ፤ባለሙያዎች ቀኑን ከማክበር በዘለለ ህክምና በቅን ልብና በትህትና የሚሰራ ስራ መሆኑን ተረድተው ህብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።
በመርኃ ግብሩ ተቋሙን ከ40 ዓመት በላይ ላገለገሉ ባለሙያዎች የዕውቅና ሽልማት በመስጠት ሶስት ሰራተኞችን በክብር ሸኝቷል።
የሚድ ዋይፎች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንቦት 5 የሚከበር ሲሆን በአገራችን ሚያዚያ 30 ''አዋላጅ መር ቀጣይነት እንክብካቤ''በሚል መሪ ቃል ተከብራል።
በተመሳሳይ የነርሶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ሜይ 12 የሚከበር ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ''ነርሶች ለወደፊት የኢኮኖሚ ሃይል ትልቅ አቅም ናቸው'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሮ ውሏል።