የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2016(ኢዜአ)፡- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር ተፈራረመ።
ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋንፎል ተፈራርመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ስምምነቱን አስመልክቶ እንደገለጹት በርካታ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት በህገ ወጥ መንገድ ይሸጋገራሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ስደተኞች ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም ይተላለፋሉ ብለዋል።
በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች ለእንግልትና ለተባባሰ ችግር እንደሚዳረጉ ጠቅሰዋል።
መንግስት በዚህ ረገድ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ለዚህም በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የአምስት ዓመት እቅድ አንዱና ዋነኛው ሲሆን እቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የአጋር አካላት ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ከዓለም የፍልሰት ድርጅት ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ቀደም ሲል በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን ለማጠናከርና ለቀጣዩ የአምስት አመት እቅድ አተገባበር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው በየትኛውም አገራት የሚገኙ ሰዎች ህገ-ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ መጀመራቸውን ጥናቶች ማመላከታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ለመሸጋገሪያነት አመቺ ናቸው ተብለው በሚታመኑ አገራት የፍልሰተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመው በዚህም ስደተኞች ለተባባሰ ችግር የሚዳረጉባቸው እድሎች ሰፊ መሆናቸውን አክለዋል።
በመሆኑም በፍልሰትና የስደተኞች ደህንነት ማረጋገጥ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በርብርብ በመስራት ጉዳቱን መግታትና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ድርጅታቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።