በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው
አዳማ ፤ግንቦት 3/2016 (ኢዜአ)፡- በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ብዙ ወጪ ሳያወጡ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ምቹ እድልን እየፈጠረ ሲሆን ህክምና ባለማግኘት የሚያጋጥም ዘላቂ የጤና ችግርን ለመግታትም ዓይነተኛ ሚናን እየተወጣ ነው።
የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በአገልግሎቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ በአገልግሎት አሰጣጥና በአቅርቦት ማነስ ምክንያት ቅሬታ እየቀረበ ነው።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተካናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች በሁሉም ወረዳዎች እንዲከፈቱ ማድረግና በተለየ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ማበራከት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአባላት ቁጥር የመጨመር ስራ በሚጠበቀው ልክ አለመሰራቱ እንዲሁም ከማህበረሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ በጊዜ ወደ ባንክ አለማስገባት ሌላው ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የጤና መድህን አገልግሎት የሚመራበትን የአሰራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት በሁሉም ደረጃ ያለ አመራር ቀዳሚ ስራ እንዲሆን በጤና ሚኒስቴር በኩል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከጤና መድህን አባላት የሚሰበሰበው ገንዘብም ከማህበረሰቡ ከተሰበሰበ በኋላ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ባንክ ገቢ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለክልል ጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች የህክምና መሳሪያዎችና ተሽከርካሪ ማሟላት፣ ጽህፈት ቤቶች ማደራጀትና ምቹ የጤና አገልግሎት መስጫ አካባቢን በመፍጠር በኩልም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ቅሬታን ለመፍታት ያግዛል ተብለው በቀጣይ ከተያዙ እቅዶች አንዱ ለጤና ባለሙያዎቹ ምቹ የስራ አካባቢን የመፍጠር ስራ በትኩረት እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው የአገልግሎቱን ጠቀሜታ የማስረዳት ስራ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት በአገሪቷ በሚገኙ 3 ሺህ 631 ጤና ተቋማት የጤና መድህን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በህዝብ አቅም በተገነቡ 472 ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እየቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ አባላትን ቁጥር ለመጨመር ከተሞችን፤ የመንግስት ተቋማትና ጡረተኞችን የማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች አገልግሎቱ እንዲጀመር አስፈላጊ ድጋፎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡