አረንጓዴ ዐሻራ - ለዓየር ንብረት ለውጥ ላለመበገር የሚደረግ ትጋት - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ - ለዓየር ንብረት ለውጥ ላለመበገር የሚደረግ ትጋት
በኢዜአ ዐይን …!
በሙሴ መለሰ
አረንጓዴ ዐሻራ - ለዓየር ንብረት ለውጥ ላለመበገር የሚደረግ ትጋት
የዓየር ንብረት ለውጥ የምድራችን ፈተና ነው። ልብ መባል ያለበት ግን አፍሪካ ለዓየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዋ አነስተኛ ሆኖ ሳለ ጉዳቷ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ስለዚህ አኅጉሪቱ ዕጇን አጣጥፋ ወቃሽና ጠባቂ ከመሆን ይልቅ፤ በፈተና ውስጥ ሆናም በዘላቂነት የዓየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ለማምጣት መትጋት አለባት። የሩቅ መፍትሔ አይጨበጥም፤ አይዘልቅምና።
ከመፍትሔዎች አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ነው።በዚህ ሂደት ደግሞ የኢትዮጵያ ድንቅ ስራ የሚወደስ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፤ በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ለዓየር ንብረት ለውጥ ከተሰጡ ምላሾች መካከል በፊትአውራሪነት ይጠቀሳል።
መርሐ-ግብሩ የጋራ ነው በሚል ዕሳቤ በርካቶችን በንቃት አሳትፎ ለዓለም የሚደርስ የዓየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ዐሳይቷል።
የደን ሽፋን መጠንን አሳድጓል። ይህም በዓየር ንብረት ለውጥ ላይ የራሱን ሚና እያበረከተ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ ሚና ልቆ ይነሳል። ይህም የተራቆተ መሬትን ወደ ነበረበት ከመመለስ፣ የውኃ ሀብት አሥተዳደርን ምቹ ከማድረግ እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ጋር የሚያያዝ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሩ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በሥራ ዘርፎች፣ በኑሮ ደረጃ፣ በሐይማኖት ሳትለይ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉበት በማድረጓ በዘርፉ ስኬታማ ጉዞ ላይ ናት።
ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀት ከመሆን አልፎ ለጎረቤቶቿ ችግኝ በመለገስ መርሐ-ግብሩ እንዲስፋፋ እየተጋችም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ትላልቅ ነገር አስባ፣ ትላልቅ ነገር ተልማ፣ ትላልቅ ነገር አቅዳ እና ሕዝቦቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለሌሎቹ ማሳያ ነው ማለታቸውም ከላይ ያነሳነውን ሐሳብ ያዳብረዋል።
በተጨማሪም አረንጓዴ ዐሻራ በልዩ ትኩረት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሳይቆራረጥ እየተሠራ መሆኑን፤ በየዓመቱም በሚተከሉ ችግኞች ብዛት፣ በሚተከልበት መሬት ስፋት እና በሚሳተፉ ታታሪዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን ያመላክታል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች እየወጡ በችግኝ ተከላ መሳተፋቸው የሀገርን የጋራ ራዕይ ለማሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል።
#አረንጓዴ_ዐሻራ #ኢዜአ
#Ethiopian_News_Agency