የጤና ነገር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
በወቅቱ ካልታከመ ለኩላሊት መድከም፣ ለደም መመረዝና ለሞት የሚያደርሰው ኢንፌክሽን
· የሕጻናት የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዴት ይከሰታል?
ምንም እንኳን አልፎአልፎ አንድ ኩላሊት ኖሯቸው የሚወለዱ ሕጻናት ቢኖሩም፤ ጤናማ (ኖርማል) የሚባለው በግራና በቀኝ ሁለት ኩላሊት ኖሮት መወለድ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኩላሊት አንዱ ሥራም ሽንት ማጣራት መሆኑን የሚገልጹት ከፍተኛ የሕጻናት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሎዛ ኑርልኝ፤ በዚህ ሂደት የተመረተው ሽንት ከሰውነት (ወደ ውጭ) ይወገዳል ይላሉ።
በግራና በቀኝ ኩላሊት የተጣራው ሽንት ወደ ሽንት ፊኛ እንደሚተላለፍና በሽንት ቱቦ አማካኝነት ከሰውነት (ወደ ውጭ) እንደሚወገድ ያስረዳሉ። ይህ ሂደት (ስትራክቸር) በአግባቡ የሚከናወነው ከባክቴሪያ የጸዳ ሲሆን መሆኑንም ይገልጻሉ።
በአንጻሩ ሂደቱ (ኩላሊት፣ የሽንት ፊኛ እና ሽንት የሚወገድበት ቱቦ በባክቴሪያ ሲጠቃ) የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተከሰተ እንደሚባል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
· የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እነማንን ያጠቃል?
የሕክምና ባለሙያዋ እንዳሉት፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሕጻናትን በስፋት ያጠቃል። በሕጻናት ላይ የተለመደ የኢንፌክሽን ዓይነት ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በተለይም ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው ሁኔታውን በአኃዝ ሲያስረዱ፤ ከ100 ሕጻናት 7ቱ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በጾታ ደረጃ ወንዶችም ሴቶችም ተጋላጭ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያዋ፤ በተለይም ያልተገረዙና ከ3 ወር በታች ዕድሜ ያላቸው ወንድ ሕጻናት በስፋት እንደሚጠቁ ጠቁመው በዚህም ከ100 ሕጻናት 20ዎቹ እንደሚጠቁ የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ ብለዋል።
በአንጻሩ ከአንድ ዓመት በላይ በሆናቸው ሕጻናት ላይ ደግሞ በይበልጥ ሴቶች እንደሚጋለጡ ጠቁመዋል። ለዚህም ሴት ከመሆን ጋር ተያያዙ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች እንዳሉ አንስተዋል።
· የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ህመሙ (ኢንፌክሽኑ) እንደተከሰተበት ቦታ ምልክቶቹ እንደሚለያዩ አስገንዝበው፤ ለምሳሌ ኩላሊት ላይ ወይም የሽንት ፊኛ ላይ ወይም የሽንት ማስወገጃ ቱቦ ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን ቢኖር ምልክቱ የተለያየ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህን በምሳሌ ሲያስረዱም የሽንት ፊኛ ወይም ሽንት የሚወገድበት ቱቦ በኢንፌክሽን ሲጠቃ፤ ቶሎ ቶሎ ሽንት የመሽናት ሁኔታ፣ በሚሸኑበት ወቅት የማቃጠል ስሜት፣ የሽንት ቀለም መደፍረስ፣ አንዳንድ ጊዜ ሽታ ያለው ሽንት መኖር፣ ከእምብርት በታች የህመም ስሜት መኖር የሚሉትን አንስተዋል።
ኢንፌክሽኑ ኩላሊት ላይ ሲከሰት ደግሞ ይላሉ፤ በጣም ታምመው ወደ ሕክምና የመሄድ ሁኔታ መኖር (ከፍተኛ ትኩሳት መኖር፣ ማቅለሽለሽ (ማስመለስ)፣ በጎንና በጎን እንዲሁም በጀርባቸው የህመም ስሜት መኖር) የሚሉት ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
ከአንድ ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ደግሞ ከላይ የተገለጹት ሁሉም ምልክቶች ላይታዩባቸው እንደሚችሉ በመጠቆም፤ ትኩሳት ብቻ፣ ማስመለስ ብቻ፣ የሆድ ህመም ብቻ ሊከሰትባቸው እንደሚችል አስገንዝበዋል።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ጨቅላ ሕጻናትንም (ወዲያው በተወለዱበት ቅጽበት) ሊያጠቃ እንደሚችል ገልጸዋል። በዚህ ወቅትም ምልክቶቹ፤ መነጫነጭ፣ ክብደት መቀነስ፣ ጡት መጥባት መቀነስ፣ እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ቢጫ መሆን ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
· ወደ ሕክምና መቼ ይሂዱ?
ዶክተር ሎዛ እንደገለጹት፤ በተለይም ከአንድ ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ ሁሉም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ላይታዩ እንደሚችሉ ወላጆች (አሳዳጊዎች) መገንዘብ አለባቸው።
በዚህም መሠረት ይላሉ፤ ከሁለት ቀን በላይ የቆየ ከፍተኛ ትኩሳት (የሙቀት መጠኑ ከ39 እስከ 40ና በላይ የሆነ) ሲኖር የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊሆን ስለሚችል ወላጆች (አሳዳጊዎች) ሕጻናቱን ቶሎ ወደ ሕክምና እንዲወስዱ አሳስበዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ በሆኑ ሕጻናት ላይም ከላይ የተገለጹት ምልክቶች ሲስተዋሉ ቶሎ ወደ ሕክምና መውሰድ እንደሚመከር አስገንዝበዋል።
· የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል?
እንደ ሕክምና ባለሙያዋ ምክር፤ ወላጆች ልጆችን በሚያጸዳዱበት ወቅት ከኋላ ወደ ፊት አለማጽዳት (ከሰገራ መውጫ ወደ ሽንት መሽኛ አቅጣጫ አለማጸዳዳት)፣ ጥብቅ ያለ (እንደ ታይት ያለና መሰል) ልብስ አለማልበስ፣ ሽንት እንዳይቋጥሩ ማድረግ (ሽንታቸው መምጣቱን በመጠየቅ ወይም ሲመጣባቸው ቶሎ ቶሎ እንዲሸኑ ማበረታታት)፣ ድርቀት ካለባቸው ይህን መከላከል፣ በየ6 ወሩ የትላትል መድኃኒት እንዲወስዱ ማድረግ እና የሕጻናትን ጥፍር ማሳጠር ኢንፌክሽኑን ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።
· ሕክምናው
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ኬዙ (ኢንፌክሽኑ) እንደተከሰተበት ቦታ እና እንደ ልጆቹ ዕድሜ እንደሚለያይ በማስገንዘብ፤ ከላይ ምልክቶች ብለን ያስቀመትናቸው ሲከሰቱ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ በቀላሉ ታክመው እንዲድኑ ማድረግ እንደሚቻል ዶክተር ሎዛ አስገንዝበዋል።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ቶሎ ካልታከመ ከኩላሊት መድከም እስከ ደም ኢንፌክሽን (ደም መመረዝ) ድረስ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል እና ከዚህም ሲያልፍ እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ገልጸዋል።
#የጤና_ነገር #የሽንት_ቧንቧ_ኢንፌክሽን #ኢዜአ